1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርእሠ ብሔር ሹም ሽሩ ላይ የፖለቲከኛና የሕግ ባለሞያ አስተያየት

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2017

ላለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያን በርእሠ ብሔርነት ያለገሉት የሀገሪቱ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ በርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተተክተዋል ። የርእሠ ብሔር ሥጣንና ተግባራት ምንድን ናቸው?

Äthiopien Botschafter Taye Atske Silassie
ምስል Solomon Muchie/DW

የርእሠ ብሔር ሥጣንና ተግባራት

This browser does not support the audio element.

ላለፉት ስድስት ዓመታት  ኢትዮጵያን በርእሠ ብሔርነት ያለገሉት የሀገሪቱ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ በርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተተክተዋል ። ከስልጣናቸው የተነሱት የቀድሞዋም ሆኑ አዲስ የተሾሙት ርእሣነ ብሔር በዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፎች የዳበረ ልምድ ያላቸው አንጋፋ ባለሞያዎች ስለመሆናቸው ይነገራል ። ኢትዮጵያ በምትከተለው የምክር ቤት የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ምክንያት ርእሠ ብሔር ሆነው የሚሾሙ ሰዎች ከፖለቲካ ፓርቲ ውክልና ገለልተኛ እንዲሆኑ፦ ሀገርን፣ ሕዝብን እና መንግሥትን የሚወክሉ እንዲሆኑ ይደረጋል ። ይህም በመሆኑ ሰባት ኃላፊነቶች ያሏቸው ቢሆንም የፖለቲካ ሥልጣን ግን ለመንግሥት የአስፈፃሚው አካል የተሰጠ ነው ። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ በምን ሁኔታ ያደርጋል?

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት አይነት ስብሰባዎችን ያደርጋል። እነዚህም መደበኛ፣ አስቸኳይ፣ ልዩ እና ዝግ ስብሰባዎች ናቸው። በመርህ ደረጃ ስብሰባዎች በግልጽ መደረግ እንዳለባቸው የተደነገገ ቢሆንም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የምክር ቤቱ ስብሰባ በዝግ እንደሚደረግ የገለፁት የሕገ መንግሥት እና የአስተዳደር ሕግጋት የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አሮን ደጎል ምክር ቤቱ ትናንት የተሾሙትን ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዝግ ስብሰባ ዕጩነታቸውን ካፀደቀ በኋላ ለሹመት ማቅረቡ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ያለበት አለመሆኑን ገልፀዋል።

«ራሱ ምክር ቤቱ በአንድ ሦስተኛ የምክር ቤቱ አባላት ከተጠየቀ እና ከግማሽ በላይ አባላት ከደገፉት ሊካሄድ ይችላል። ወይም ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ከተጠየቀ እና የምክር ቤት አባሌት ከግማሽ በላይ ከደገፉት ሊካሄድ ይችላል።»

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ በምን ሁኔታ ያደርጋል?ምስል Solomon Muchie/DW

የርእሠ ብሔር ሥጣንና ተግባራት

ሀገር የሚወክሉት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ፖለቲካዊ ሥልጣን ባይኖራቸውም ተለይተው የተቀመጡ ሰባት ኃላፊነቶች እንዳሏቸውም የሕግ ባለሙያው ገልፀዋል። «ሴሬሞኒያል የሆነ አገልግሎት ነው ያለው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመታዊ የጋራ ስብሰባን ይከፍታል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ያፀደቃቸውን ሕጎች እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ ያውጃል።»

የኢትዮጵያ የቀድሞ ርእሠ ብሔር ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ግጭትና ጦርነቶችን መነሻ በማድረግ "ቀይ መስመር ተጥሷል" በሚል ንግግራቸው ነገሮች እንዲሻሻሉ ያስጠነቅቁ ነበር።

ስለ ቀድሞዋም ስለ አዲሱም ፕሬዝዳንቶች የፖለቲካኛ አስተያየት

ፖለቲከኛ ዶክተር ራሔል ባፌ ስለ እሳቸውና ስለ አዲሱ ተሿሚ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል። "ሁለቱም አንጋፋ ዲፕሎማቶች ናቸው። ሀገራቸውን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ከሀገር ውጭ እና በሀገር ውስጥ ያገለገሉ ናቸው እና ብቃቱም ሆነ ልምዱ አላቸው ብዩ አምናለሁ።»  የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ለሁለትኛ ዙር በኃላፊነት ለምን እንዳልቀጠሉ እስካሁን የተባለም፣ የታወቀም ነገር የለም። ፕሬዝዳንቷ ግን ከቀናት በፉት "ዝምታ ነው መልሴ" የሚል ብዙዎችን ያነጋገረ ጽሑፍ በኤክስ (X) አጋርተው ነበር። 

ፖለቲከኛ ራሔል ባፌ እንደሚሉት እንደ የሀገር ፕሬዝዳንት ይናገሩ የነበረው ስለ ሰላም በመሆኑ ስለሰላም በማውራት ሰላም የሚመጣበትን አማራጭ አይቶ በውይይት መፍታት ይሻላል ሲሉ የተስተዋለውን የግንኙነት ሁኔታ አዝማሚያ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የመንግሥት አወቃቀት ሥርዓት መሠረት የመንግሥት ሥራ የአስፈፃሚነትም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የምክር ቤት የሆነም ያልሆነም ሰው በፕሬዝዳንትነት ሊመረጥ ይችላል። ሆኖም አንድ የምክር ቤት አባል በፕሬዝዳንትነት የሚሾም ከሆነ የፓርላማ አባልነቱን ይለቃል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ርእሠ ብሔር ማን ናቸው?

አዲሱ ተሿሚ ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በተየያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠርተዋል። በውጭ ሀገራት በቆንስላ ጀኔራልነት እና ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆንም አገልግለዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ፣በስዊድን እና በግብጽ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እና አምባሳደር በመሆን እንዲሁም በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፦ ኒውዮርክ ምስል Eduardo Munoz/AP/picture alliance

ከዚያም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነውም አገልግለዋል። በዲፕሎማሲ መስክ እና በመንግሥት ሠራተኝነት ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ ላበረከቱት አገልግሎትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የረጅም ዘመናት የመንግሥት ሠራተኛ የክብር አገልግሎት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት መሆናቸው ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተነግሯል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW