1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በርካታ እጆች የተዘረጉበት የሱዳን ውጊያ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 14 2015

ሱዳን በሁለት ባላንጣ ጄነራሎች የሥልጣን ሽኩቻ የተነሳ ወደለየለት ውጊያ ከገባች ቀናት ተቆጥሯል ። ሱዳን በጦርነቱ የምትነደው ግን በሁለቱ ጄኔራሎቹ ሽኩቻ ብቻ አይደለም ። ከጄኔራሎቹ ባሻገር የጎረቤት ሃገራትን ጨምሮ በርካታ የውጭ ኃይሎችም የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ ።

Themenpaket - Sudan
ምስል፦ Omer Erdem/AA/picture alliance

ሃገራት ከሱዳን ግጭት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ተጠይቀዋል

This browser does not support the audio element.

ሱዳን በሁለት ባላንጣ ጄነራሎች የሥልጣን ሽኩቻ የተነሳ ወደለየለት ውጊያ ከገባች ቀናት ተቆጥሯል ። ሱዳን በጦርነቱ የምትነደው ግን በሁለቱ ጄኔራሎቹ ሽኩቻ ብቻ አይደለም ። ከጄኔራሎቹ ባሻገር የጎረቤት ሃገራትን ጨምሮ በርካታ የውጭ ኃይሎችም የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ ።

የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ካለፉት ጥቂት ቀናት አንስቶ በሚሳይሎች ጋይታለች፤ በጥይት አረሮችም ከላይ እስከ ታች ተደብድባለች ። የጦር ሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡራን ጦር ሠራዊቱን በአንድ ወገን አሰልፈዋል ። የቀድሞ ምክትላቸው እና ከግመል አጋጅነት በዳርፉር ጦርነት አስፈሪ ሆነው ብቅ ያሉት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሌላ ወገን የፈጥኖ ደራሹን ኃይል (RSF)አሰማርተዋል ። ባለፈው ቅዳሜ በሁለቱ ጄኔራሎች ሽኩቻ በፈነዳው ጦርነት እስከ ትናንት ብቻ ከ400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከሟቾቹ መካከል የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) አንድ ሠራተኛ ጭምር በተሽከርካሪያቸው እየተጓዙ ሳለ በሱዳኑ ውጊያ ትናንት መገደላቸው ተገልጧል ።   

ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት የማያጣት ደሀዪቱ ግን በከርሰ ምድር ነዳጅ የታደለችው ሱዳን ያለችበት የቀይ ባሕር መስመርም እጅግ ሥልታዊ ያደርጋታል ። ለአብነት ያህል ሩስያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በዚህ የቀይ ባሕር መስመር ለወደቦች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን አፍስሰዋል ። ያም ብቻ አይደለም የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በሚቆጣጠራቸው ሥፍራዎችም እነዚህ ሁለት ሃገራት በወርቅ ማእድን ቁፋሮ ላይ መሰማራታቸውን ተንታኞች ይናገራሉ ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ሰሞኑን ዘግቧል ። 

ካርቱም ሱዳን ውስጥ በውጊያው የተመታ መስተዋትምስል፦ Omer Erdem/AA/picture alliance

የሀገሪቱ እምቅ የወርቅ ክምችትም የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አዛዥ በአብዛኛው ሔሜቲ በመባል የሚታወቁት ጄኔራል ሞሐመድ ዳጋሎን ሐብታም አድርጓቸዋል ። የሩስያው «ቫግነር» በመባለው የሚታወቀው የግል ወታደራዊ አገልግሎት ተቋም ቡድን ቅጥረኞች ብሎም የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በዚህ የወርቅ ንግድ እጃቸው እንዳለበት ዩናይትድ ስቴትስ ጠቅሳለች ሲል የዜና ምንጩ ዘግቧል ።  የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በሱዳኑ ውጊያ የውጭ ኃይላት ዳፋው ከባድ መሆኑንበመግለጥ አስጠንቅቀዋል። «በሱዳን የቀጠለው ግጭት የቀጣናዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተሳታፊዎችን ማመላከቱ፤ ወደ ከፍተኛ የሰብአዊ እና የፀጥታ ቀውስ የሚያሽቆለቁል መሆኑ የምር አደገኛ ነው ።»

አቡ ዳቢ   በሱዳን የምትከተለው ፖሊሲ በሀገሪቱ ጣልቃ እስከመግባት የደረሰ ነው ሲሉም ተንታኞች ይናገራሉ ። በአንጻሩ የሱዳን ተጎራባቿ ግብፅ ሱዳን ውስጥ ተጽእኖዋ በወታደራዊው ዘርፍ መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። ከሰሞኑ ሁለቱ ጄኔራሎች ሱዳን ውስጥ የግብጽ ወታደሮችን ያስተናገዱባቸው መንገዶችም የሚታወስ ነው ። ከትናንት በስትያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የግብጽ ወታደሮችን ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ማስረከቡ ተዘግቧል ። ዜናው በተሰማበት ዕለት የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት በበኩሉ 177 የግብጽ አየር ኃይል አባላትን ወደ ሀገራቸው መሸኘቱን ገልጿል ።

በሱዳን ጦርነት በጦር መሣሪያ ተመትቶ ከጥቅም ውጪ የሆነ ተሽከርካሪ ምስል፦ Marwan Ali/AP/picture alliance

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ሱዳን ውስጥ የምትከተለው ፖሊሲ እንደ ሩስያ ሁሉ «ድብቅ ንግዶችን» በዱባይ በኩል በማጧጧፍ ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ ተንታኞች ። በገልፍ ባህረሰላጤ እንደምትገኘው ሀብታሟ ሣዑዲ ዓረቢያ ሁሉ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ከሱዳን ሁለቱ ባላንጣ ጄኔራሎች ለየትኛውም አታዳላም ። ሁለቱም ጄኔራሎች የገልፍ ባሕረሠላጤ ሃገራትን ፍላጎት በማሟላት ይታወቃሉም ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። ጄኔራል አብደል ፋታህም ሆኑ ጄኔራል ሔሜቲ የሣዑዲ መራሹ ጦርን ደግፈው የመን ውስጥ ሁቲዎችን በመውጋት ተሳትፈዋል ። ያም በመሆኑ ሣዑዲ ዓረቢያ ከሁለቱ ጄኔራሎች ለአንዱም ማድላቱን አትሻም ይላሉ በስምጥ ሸለቆ ተቋም ተንታኙ ኤሪክ ሪቬስ ። የባሕረ ሠላጤው ሃገራት ከሁለቱ ጄኔራሎች አሸናፊው የሆነውን ለመደገፍ ያአደፈጡ ይመስላሉም ብለዋል ። 

በዳርፉር ጦርነት ወቅት ሔሜቲ በምእራብ በኩል ከነበራቸው ጦር ሠፈር እየተወረወሩ ሊቢያ ውስጥ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ይሳተፉም ነበር ።  በጎረቤት ቻድ በኩልም በአሁኑ ወቅት የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የጠረፍ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ ነው ። በዚህ በኩል የጦር መሣሪያ ዝውውር እንደሚያደርጉም ተንታኞች ይናገራሉ ። 
 
እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2021 በአንድ የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ወቅት ሔሜቲ ጣልያን «ለምታደርግልን የቴክኒክ ድጋፍ» እናመሰግናለን ሲሉም ተደምጠዋል ። ሆኖም በሊቢያ በኩል ስደተተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይሻገሩ ከአውሮጳ ድጋፍ ተቀብለዋል ተብለው የተጠየቁትን አስተባብለዋል ። 

በሱዳን ጦርነት በጦር መሣሪያ ተምትቶ በከፊል የተደረመሰ ሕንጻ ካርቱም ከተማ ውስጥ ምስል፦ Marwan Ali/AP/picture alliance

በተቃራኒው የጦር ሠራዊቱ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡራን ከእሥራኤል ጋር የሱዳንን ግንኙነት በመመለስ ይታወቃሉ ። ከግብፅ ጋር ወዳጅ ብቻ ሳይሆኑ ድጋፍም ይደረግላቸዋል ። የጦር ልምምድ ሥልጠናቸውን የተከታተሉት የግብጽ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በሰለጠኑበት የጦር ኮሌጅ ውስጥ ነው ። ግብፅ እና ሱዳን 1,200 ኪሎ ሜትር ድንበር ይጋራሉ ። እናም ሁለቱም «የጋራ የሆነ የደኅንነት ፍላጎት አላቸው» ይላሉ በመካከለኛው ምሥራቅ ተቋም የግብፅ አጥኚዋ ሚሬቴ ማብሩክ ።

ሱዳን ሜሮዌ ውስጥ የግብፅ ወታደሮች መታየታቸው የሱዳን የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ወደ ርምጃ እንዲሻገር ሰበብ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ተንታኞችም አሉ ።  ምክንያቱም ሔሜቲ በግብፅ አደጋ እንዳንዣበበባቸው እንዲሰማቸው ሳያደርግ አልረምም ሲሉ አክለዋል ። ሰሞኑን በፈጥኖ ደራሹ ቁጥጥር ስር የወደቁ የጦር ጄቶች የሚታዩበት የተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል ። ሸራ የለበሱ ተዋጊ ጄቶቹ ጭራ ላይ የግብጽ ባንዲራ ያለባቸው መሆኑ ደግሞ ብዙዎችን አነጋግሯል ። ግብጽ የሱዳን የሽግግር ሒደት እንዲበላሽ እያደረገች ሳይሆን አይቀርም ያሉት ደግሞ በፓሪስ የሶርቦርኔ ዩኒቨርሲቲ የሱዳን ባለሞያው ክሌሞን ዴሻዬ ናቸው ። ሌላኛዋ ጎረቤት ኢትዮጵያ በውጊያው «ከሚገኘው ማንኛውም ውጤት ለማትረፍ ከሁሉም ቡድኖች ጋር ግንኙነት ገንብታለች » ያሉት ደግሞ መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው ሶፋን ማእከል ነው ። 

ጦርነቱን ሽሽት ሱዳናውያን ጓዛቸውን ሸክፈው በጎዳና ላይ ሲጓዙ ምስል፦ AFP

በጋቦን፤ ጋና እና ሞዛምቢክ የተባበሩት መንግሥታት ድጅት አምባሳደር ሐሮልድ አጌይማን የሱዳን ግጭት ለቀጣናውም ለዓለምም ጠንቅ ነው ብለዋል ። «አሁን ያለውን ሁኔታ የሚያወሳስብ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጥብቅ እንቃወማለን ። በዚያ ረገድ ሚያዝያ 8 በነበረው ቃለ ጉባኤ መሰረት የሱዳን ሪፐብሊክ ሉዓላዊነት፤ የግዛት አንድነት እና ነጻነት ስለመከበሩ ቁርጠኝነታችንን በድጋሚ እንገልጣለን ። የቀጣናው ሃገራት እና ሌሎች አካላት ሀገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደሚከበርበት ሽግግር ሒደት እንድታመራ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ እናሳስባለን ። »    

ከትናንት በስትያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፦ «ኢትዮጵያን ከሱዳን ወንድም ሕዝብ ጋርግጭት ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ» ሲሉ አሳስበዋል ። የጎረቤት ሃገራትንም ሆነ የሌሎችን ከፍተና ትኩረት የሳበው የሱዳን ግጭት መጨረሻው ምን ይሆን? 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW