በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ህልፈት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተያየት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2017
“እግዚአብሔር አምላክ የሚወዳቸውን እኚህን ታላቅ አባታችን በጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ማግስት ወደዘለዓለማዊ ማረፊያው ወስዷቸዋል” ያለችው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲን ቅዱስነታቸው ባለፉት ወራት በደረሰባቸው ከባድ ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው፤ በቫቲካን በሚገኘውም “ቅድስት መንበራቸው” ተመልሰው ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ትናንት ሰኞ ማለዳውን ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል ብላለች፡፡
በህመማቸውም ወቅት “በጾሎት ህብረት አብሬናቸውቸው ነበርን” ያለችው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን “የቅድስት መንበር እረኛ” ያለቻቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ (ፖፕ) ፍራንሲስ “ሕይወታቸውን በሙሉ ለጌታ እና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ” በማለት በህልፈታቸውም ሀዘኗን ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሎካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫም እሁድ በመላው ዓለም በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ በተከበረው የትንሣኤ በዓል ምዕመናን በተሰበሰቡበት በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው መልካም ምኞታቸውንና ለዓለም ሰላም ያላቸውን ፍላጎት ባሰሙበት ማግስት ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ህልፈታቸውን መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡
“የርዕሰሊቃነ ጳጳሳት አቡኔ ፍራንቼስኮስን ሞት በታላቅ ሀዘን የሰማነው ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የምወዳቸውን ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ስለሚወዳቸውም ነው በዚህ በትንሳኤ ማግስት ወደራሱ የወሰዳቸው፡፡ በመላው ዓለም ክርስቲያኖች የጌታችን የመዳኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሳኤ ስናከብር እሳቸው ምንም ብያማቸውም ከመኝታቸው ተነስተው ሄደው በመንበረ ጴጥሮስ ምዕመናን በተሰበሰቡበት እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል” ሲሉም አስታውሰዋል፡፡ ብጹዕነታቸውን ፈጣሪ በመንግስቱ ይቀበልልን በማለትም ለመላው የዓለም ክርስቲያኖች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
ፖፕ ፍራንሲስ እንዴት ይታወሳሉ?
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲን የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሃዋሪያዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም በአውሮፓ የምትገኘው የቫቲካን ቅድስት መንበርን በመወከል የተለያዩ ቤተክርስቲያናትን የሚጎበበኙ አባ ጴጥሮስ በርጋ ፖፕ ፍራንሲስ የሚታወሱት ለወንጌል አገልግሎት ህይወታቸውን የሰጡ በሚል ነው ሲሉ ገልጸውአቸዋል፡፡ “በህይወታቸው የክርስቶስን ወንጌል ያንጸባረቁና በተግባር የኖሩ” በሚል ገልጸውአቸዋልም፡፡
ለደሆች ትልቅ ስፍራ የነበራቸው፣ በትህትናቸው ብዙዎችን ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት የመለሱ፣ ሰላም ላይ በነበራቸው ጽኑ እምነት በሰላም ላይ በሰሩት ስራ እና ከዓለም መሪዎች ጋር የሚሰሩበትም መልካም ዲፕሎማሲ እሳቸውን ከሚስታውሳው ተግባሮቻቸው ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለችው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲን የብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ህልፈትን ተከትሎ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ የሚቆይ የሀዘን መግለጫዎችን እየተቀበለች እሳቸውንም በጸሎት እያሰበች በመቆየት ቅዳሜ ጠዋት የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ስርዓተ ቅዳሴ እና ፍትሃት አንደምታከናውንም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ያለቻቸው ፖፕ ፍራንሲስ ላሳዩት የሕይወት ምሳሌነት ታላቅ ምስጋና እንደምትሰጥና
የብፁዕ ወቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስን ነፍስ ለአንዱና ለቅድስት ሥላሴ ማለቂያ የሌለው መሐሪ ፍቅር በአደራ እንሰጣለንም ብላለች። ፖፕ ፍራንሲስ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ምዕመናን ያሏትን ቤተክርስቲያን በክህነት፣በሊቀጳጳስነት፣ በካርዲናልነት እንዲሁም በቅድስት መንበር እረኝነት ስለማገልገላቸውም ከህይወት ታሪካቸው ተሰምቷል።
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ