በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች «ግጭቱ ተባብሷል» ነዋሪዎች
እሑድ፣ መስከረም 18 2018
በአማራ ክልል በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መባባሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ። ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ከትናንት በስትያ አንስቶ የነበረው ውጥረት ዛሬ መቀዛቀዝ ቢያሳይም በዙሪያው ባሉ የገጠር ከተሞች ቀጥሎ እንዳለ ተናግረዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አንድ የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪ እንዳሉት ትናንት የ ኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከተማዋን ለቆ ከወጣ በኋላ የፋኖ ኃይሎች ለአንድ ቀን ያህል ተቆጣጥረውት ነበር ። ነገር ግን ለዛሬ አጥቢያ የፋኖ ኃይሎች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል » ብለዋል።
«ዛሬ በከተማው የመንግስት የጸጥታ ኃይል መከላከያ ገብቷል። ከጠዋት ጀምሮ የጸጥታው ሁኔታ ወደ ቀድሞው ሰላም ተመልሷል። ትናንት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ነበር ችግሩ የተፈጠረው ፤ ችግሩ የተፈጠረውም በሙሉ የመከላከያ ኃይል እና የመንግስት አመራሮች ከተማዋን ለቀው ወጥተው ስለነበር የፋኖ ኃይሎች በቅርብ ርቀት ስለነበሩ መረጃው ስለደረሳቸው ከተማዋ ገብተው እስከ ሌሊት ድረስ ከተማዋን ተቆጣጥረው እንደገና ሌሊት ተመልሰው ወጥተዋል። ይህንንም ሁላችንም በአይናችን ያየነው ነው ። ደስ የማይል ሴራ ነገር ያለበት እስኪመስል ነው የደረሰው ለሁላችንም። …. አላግባብ መሰዋዕትነት ተከፍሏል፤ መሞት ያልነበረባቸው ሰዎች ሞተዋል። አንዱ የሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ ነው ፤ ነገ ነው የሚቀበረው ፤ የሚሊሻ ምክትል የነበረውም ሞቷል፤ እሱ ዛሬ ተቀብሯል። ብዙ ወጣቶችም ሞተዋል።»
ሌላ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ በከተማዋ የነበረው ውጥረት እየተረጋጋ ቢመጣም አሁንም መደበና እንቅስቃሴ ወደ ቦታው አለመመለሱን ተናግረዋል።
«ድባቡ ዛሬ ምንም አይልም ብቻ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ ብዙ ሱቆች አልተከፈቱም ፤ ከዚያ ውጭ ያለው ምንም አይልም፤ አሁን ላይ ዞሮ ዞሮ ከተማይቱ ሰላም ናት »
ከሰሞኑ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ሰፊ ቦታ የሸፈነ ግጭት እየተደረገ መሆኑን ዶይቸ ቬለ አረጋግጧል። የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ በሆነችው የወልድያ ከተማን ጨምሮ በዙሪያዋ ባሉ የገጠር ከተሞች ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለማጣራት ለተለያዩ ግለሰቦች ስልክ ለመደወል ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመስራቱ ሊሳካልን አልቻልንም። ወደየዞኖቹ የአስተዳደር ኃላፊዎች በተመሳሳይ ስልክ ለመደወል ያደረግነው ጥረት የስልክ ጥሪ ባለመመለስ እና ባለመነሳት ሳይሳካልን ቀርቷል።