በሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) በባለሥልጣን ላይ ያነጣጠረዉ ግድያ ቀጥሏል
ዓርብ፣ የካቲት 14 2017
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን (ሰላሌ) የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ በታጣቂዎች እየተገደሉ ነዉ።ካለፈዉ ከታህሳስ ወር 2017 ወዲህ ብቻ የወረዳዎች አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።ሰሞኑን ደግሞ በዞኑ የግራር ጃርሶ ወረዳ ሁለት ባለስልጣናት በአማጽያን መገደላቸው ተነግሯል፡፡
በጊራር ጃርሶ የአመራሮች ግድያ
ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በሰሜን ሸዋ ዞን (ሰላሌ) ግራር ጃርሶ ወረዳ ዝናቡ በለጠ የተባሉ የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ እና የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ተፈሪ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መገደላቸውን ወረዳው በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡ ዛሬ ስርዓተ ቀብራቸው የተከናወነው አመራሮቹ ግድያቸው ለአከባቢው ማህበረሰብ ሀዘኑ መሪር ነው ሲል የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን በገጹ አስፍሯል፡፡ አመራሮቹ ረቡዕ የተገደሉት በወረዳው በሚገኝ አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምልከታ አድርገው ሲመለሱ ‘ሲልሚ' በሚባል ስፍራ ታጣቂዎች የደፈጣ ጥቃት ፈጽመውባቸው እንደሆነ ታውቋል፡፡ ግራር ጃርሶ ወረዳ በዞን ከተማ ፊቼ ዙሪያ የሚገኝ ወረዳ ነው፡፡
ዶይቼ ቬለ በወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ የእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል ስለጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ብጠይቅም በቀብር ስነስርዓት ላይ በመሆናቸው መረጃ ማጋራት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ደግሞን ስንደውልላቸውም ስልካቸው አይነሳም፡፡
ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በአከባቢው የተፈጠረው ውጥረት
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የአከባቢው ነዋሪ እንዳሉን ግን ታጣቂዎች በእለቱ ከጸጥታ አካላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ውጥረት ፈጥረውም ነበር፡፡ “በአማጺ ታጣቂዎች በተፈጠረው ውጥረት ተመተው ጉዳት የደረሰባቸው አሉ፡፡ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ነበር፡፡ የአከባቢውን ማህበረሰብ የሚረብሽ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ተኩስ ነው፡፡ ለፊቼ ከተማ ቅርብ በሆኑ ኤጄርሳ ካዎ እና ቦሶቄ በሚባሉ የገጠር ቀበሌያት በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ታይተውም ነበር፡፡ ከመንግስት ባለስልጣናት እስካሁን ህይወታቸው ማለፉ የተረጋገጠው የጊራር ጃርሶ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የወረዳው ፓርቲ ኃላፊ ሲሆኑ በህክምና ላይ ያሉም መኖራቸውን ሰምተናል” ብለዋል፡፡
በዞኑ የተደጋገመው የአመራሮች ግድያ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ይህ የአመራሮች ግድያ በአከባቢው በምንቀሳቀሱ አማጺያን ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከታህሳስ ወር ወዲህ ብቻ በርካታ የዞኑ አመራሮች መንግሥት በሽብርተኝነት በፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃቶች መገደላቸው ተደጋግሞ ተዘግቧል።
ለታጣቂዎቹ ጥቃት ተደጋጋሚ ኢላማ የሆነው ይህ ዞን ከመዲናዋ አዲስ አበባ እጅግ ቅርብ ስፍራ ላይ የሚገኝ የኦሮሚያ ክልል መዓከላዊ አካባቢ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ውስጥም የሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳዋና አስተዳዳሪው አቶ አበበ ወርቁ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በተፈጸማቸው ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል። በዚህ ግድያ ላይ ወዲያውኑ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ለጥቃቱ ሃላፊነት ወስዶ የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ አበበ ወርቁን መግደሉን እዲሁም የወረዳው ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊን ከሌሎች ሰዎች ጋር መወሰዳቸውን ገልጾም ነበር፡፡ የአቶ አበበ ወርቁ ግድያን በተመለከተ መንግሥት በፊናው “የለውጡን ጉዞ የተቃወሙ” ያሏቸው ታጣቂዎች የአመራሩን ህይወት ማጥፋቱን ባለፈው ሳምንት ኃሙስ ነው ያረጋገጠው። ግድያውም የመንግሥት ባለሥልጣኑ ለሥራ ስንቀሳቀሱ በታጠቁ ኃይሎች እንደተፈጸመም የወረዳው አስተዳደር በይፋ አሳውቋል።
ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ያያ ጉሌሌ ወረዳ ሶስት የዞን ባለስልጣናትን ጨምሮ አምስት ሰዎች ከዞን ከተማ ፊቼ 28 ኪ.ሜ. ብቻ ከምትርቀው ከወረዳ ከተማ ፊታል ወደ ፊቼ በመመለስ ላይ ሳሉ ባደፈጡ ታጣቂዎች ድንገተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸው የዞን ባለስልጣናት፤ ማለትም የሰሜን ሸዋ ዞን የገቢዎች ኃላፊ፣ የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የዞኑ ሎጂስቲክ ኃላፊ መገደላቸው አይዘነጋም፡፡ በዚያው ጥቃት ከሶስቱ አመራሮች በተጨማሪ የባለስልጣናቱ አሽከርካሪ እና የአከባቢው ቀበሌ አመራርም የጥቃቱ ሰለባ ነበሩ፡፡
በዚሁ ተመሳሳይ ወር የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ማዕከላዊ አመራር ከመንግስት ጋር ያደረገውን ስምምነት ተከትሎ የእርቅ ስምምነቱን ተግባራዊ እናደርጋለን በማለት አመራሮችን ለአቀባበል የጠሩ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሱሉልታ ወረዳ ላይ የፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሁለት ሰዎች መግደላቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
በዚሁ ዓመት ጥቅምት ወር በዞኑ የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ንጉሤ ኮሩን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች የሚሆኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውንም በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ እና የአለልቱ ወረዳ ኮሙኒኬሽን “የሕዝብ መሪን በመግደል የሚሳካ ሕልም የለም” በማለት ለግድያው “ሸነ” ያሉትን ታጣቂ ቡድን ከሰዋል። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም በወቅቱ ለጥቃቱ ኃላፊነት መውሰዱ የሚታወስ ነው፡፡
የተወሳሰበው የማህበረሰብ ህይወት
በጸጥታ ችግሩ ክፉኛ የሚፈተነው ይህ ዞን በመንግስት አመራሮች ላይ ከሚያነጣጥረው ጥቃት በተጨማሪ ሰላማዊ የሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላትን እና ዞኑን በሚያቋርጠው መንገድ ላይ በመንገደኞች ላይ በሚፈጸም ተደጋጋሚ እገታም ስሙ በስፋት ተነስቷል፡፡
አስተያየት ሰጪ የፊቼ ነዋሪም የማህበረሰቡ ችግር ጥልቅ መሆኑን ሲያስረዱ፤ “አሁን ትልቁ ችግር ጥያቄ የሚያስነሱ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ ህዝቡ በሁሉም ወገን ተስፋ እያጣ ነው፡፡ በሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች በኩል ለሰላማዊ ሰዎች መብት ጥበቃ ተብሎ የሚሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፡፡ እረፍት የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ የትም ብትሞት ተጠያቂ ማግኘት አዳጋች እየሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ