«ህወሓት ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ ወረዳዎች አልወጣም»የብሔረሰቡ አስተዳደር
ዓርብ፣ ጥር 13 2014
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጦርነት የተካሄደባቸው አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።በጦርነቱ ምክንያት በግብርናው ዘርፍ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ አመልክቷል፤ በሌላ በኩል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ ወረዳዎች ከህወሓት ወረራ ሙሉ በሙሉ ነፃ አይደሉም ሲል የብሔረሰብ አስተዳደሩ ገልጧል፡፡ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ካሉት 24 ወረዳዎች መካከል በ12ቱ ወረራ ፈፅሞ እንደነበር የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ በዚህም ወቅት በዞኑ ህብረተሰብ ላይ በርካታ ግፎችና በደሎች ደርሰው እንደነበር የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ፃዲቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ወራሪ ያሉት ቡድን በጥምር ኃይሉ ከአካባቢው በኃይል እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ህብረተሰቡ ወደ መደበኛ ኑሮው እተመለሰ መሆኑን አቶ ታደሰ አመልክተዋል፡፡
በርካታ ወገኖች በተፈፀሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች የስነልቦና ጫና የደረሰባቸው በመሆኑ ጉዳቱን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ ወረዳዎች ጋር የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ከብሔረሰብ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር የጋራ ውይይቶች መደረጋቸውን ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ አበበ በወረራው ወቅት በግብርናው ዘርፈ ብዙ ወድመቶች መፈፀማቸውን ተናግረዋል፣ ህወሓት የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳዎችን እየቆፈረ ለምሽግነት አውሏቸዋል፣ የግብርና ጽ/ቤቶች ወድመዋል፣ ለግብርና ሥራ የሚውሉ የመስኖ ሞተሮች ተዘርፈዋል፣ የግብርና ማስልጠኛ ተቋናት ወድመዋል ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት 38 ሺህ ኩንታል የምርት ቅናሽ መታየቱን ጠቁመው የተጓደለውን ምርት ለማካካስ ሰፊ የመስኖና የመደበኛ ግብርና እየተከናወነ እንደሆነም አቶ ኤሊያስ አመልክተዋል፡፡ በዚህም 960 ሄክታር በማልማት 435 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት ታቅዷል ነው ያሉት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ኃይሎች ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ እንዳልተወገዱ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡ ህወሃት ከአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች እንዳልወጣ፣ በዝቋላ ወረዳ ደግሞ አንድ ቀበሌ ከህወሃት ነፃ አልወጣም ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ወቅት ተፈናቅለው በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተፈናቃዮች ሁሉም ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ያመለከቱት አቶ ተስፋዬ እየቀረበ ያለው የእለት ምግብ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሁንም ድጋፋቸውን እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ