1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የከፋዉ ግጭት

ረቡዕ፣ ጥር 8 2016

ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የሚደረገዉ የታጣቂዎች ውጊያና ግጭት እየከፋ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ። የኦሮሚያና የአማራ ክልሎችን የሚያዋስነዉ የደራ ወረዳ ለተከታታይ ዓመታት በታጣቂዎች መካከል ግጭት ይደረግበታል። ግጭቱ ትናንትም አገርሽቶ ሰዎች መገደልና መቁሰላቸዉን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

Äthiopien | Oromiya Region
የኦሮሚያ ክልል ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የከፋዉ ግጭት

This browser does not support the audio element.

ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ  የሚደረገዉ የታጣቂዎች ውጊያና ግጭት እየከፋ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ። የኦሮሚያና የአማራ ክልሎችን የሚያዋስነዉ የደራ ወረዳ ለተከታታይ ዓመታት በታጣቂዎች መካከል ግጭት ይደረግበታል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ተደጋጋሚዉ ግጭት ሕይወት እያጠፋ፣ ሐብት ንብረታቸዉን እያወደመ እነሱንም እያፈናቀለ ነው። ግጭቱ ትናንትም አገርሽቶ ሰዎች መገደልና መቁሰላቸዉን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል። የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ባለሥልጣናት ግን እስካሁን ሥለ ግጭቱ ያሉት ነገር የለም።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የደራ ወረዳ ጉንዶ መስቀል ከተማ ነዋሪ እንዳስረዱት በተለይም በጤፍ ምርቷ እጅጉን በምትታወቀው ደራ ወረዳ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጠፋው ሰላም የነዋሪዎችን እንግልት አጽንቶ መከራቸውንም እንዳከፋው አመልክተዋል። ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ አማራ ክልልን አዋስና የምትገኘው ይህቺ ወረዳ ከአዲስ አበባ 230 ኪሎ ሜትር ከዞን ከተማ ፊቼ ደግሞ 120 ኪሎ ሜትር ግድም ርቃ ነው የምትገኘው። ይህቺ ወረዳ ባላት 40 ቀበሌያትና በህዝብ ብዛቷ ብሎም በምርታማነቷ ከሰላሌ ቀዳሚዋ በሚል ትጠቀሳለች።

ይህቺ ወረዳ ምንም እንኳ አስተዳደራዊ ወሰኗኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይገኝ እንጂ በሦስት አቅጣጫዎች የምትዋሰነው በአማራ ክልል ነው። የጉንዶመስቀል ከተማው አስተያየት ሰጪያችን በ2010 ዓ.ም. የደራ አስመላሽ ኮሚቴ በሚል ወረዳውን ወደ አማራ ክልል የመቀላቀል ውጥን የነበራቸው ሰዎች መንቀሳቀስ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ ወረዳዋ ሰላም ርቋት መቆየቱንም አስተያየት ሰጪው አመልክተዋል። በትናንትናው ዕለት እንኳ በኦሮሚያ ክልል በኩል ሚዳ ኦሮሞ በሚባል እና በአማራ ክልል በኩል ዓለም ከተማ በተባለ አከባቢ የፋኖ ታጣቂ ያሏቸውና በኦሮሚያ በኩል በነበሩ ታጣቂዎች መካከል ብርቱ ውጊያ እንደነበር ነው ያመለከቱት።

የኦሮሚያ ገጠር አካባቢ ምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

በዛሬው ዕለት በአከባቢው ውጥረት ቢነግስም አንጻራዊ ሰላም ተስተውሎ መዋሉን ያስረዱን እኚህ አስተያየት ሰጪ በትናንቱ ውጊያ የሞቱትን ሰው ባያገኙም የቆሰሉትን ግን በዓይናቸው መመልከታቸውንም ገልጸዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪም በወረዳው ኢሉ ጎዳ ጨፌ ከተባለ ቀበሌ መሆናቸውን ገልጸው ተከስቷል ያሉትን ለዶቼ ቬለ ሲያስረዱ፤ «በዚህ የሆነው የጸጥታው መደፍረስ አሁን እየከፋ ነው። በዚህ በአማራ ክልል በኩል የታጠቁ አካላት ወደዚህ እየተሻገሩ ተደጋጋሚ ጥቃት ይከፍታሉ። የአከባቢው ማኅበረሰብ ይህን ጥቃት በሚመክትበት ወክት በአከባቢው ባለሥልጣናት የሸነ የሽብር ቡድን የሚል ስም ነው የሚለጠፍብን። ከዚህ የተነሳ ብዙውን ጊዜ የጸጥታ ከለላ እየተነፈግን ለስጋት ተዳርገናል» ነው ያሉት።  

እኚህ አስተያየት ሰጪም ሃሳባቸውን አከሉ፡ «ትናንት የፋኖ ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው በመግባት ቆር በሚባል ስፍራ ብርቱ ውጊያ ነበር። በኦሮሚያ በኩል ራቾ የሚባል እና በአማራ በኩል ኮሉ በሚባል አከባቢም ውጊያ ነበር። አስከፊ በሆነ መንገድ ህዝባችን በከፋ በመፈናቀል ላይ ነው። ወደ ከተማ እና አጎራባች አከባቢዎች ይሰደዳል ወዴት እንደምንሄድ ግራ ገብቶናል» በማለትም ስጋታቸውን ዘርዝረዋል። ዶቼ ቬለ በአከባቢው ጥቃት ይፈጽማሉ በተባሉት በኩል እንዲሁም ከሌላ ሦስተኛ ወገን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልሰመረም። የአከባቢው ነዋሪዎቹ ያቀረቡትን ምሬት በመያዝ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ እንዲሁም ለአማራ ክልል አቻቸው ዶ/ር መንገሻ ፈንታው ደውለንም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም።

በአማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ መሰል የጸጥታ ስጋቶች ሲጫሩ ግን ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዚሁ ወረዳ ቀደም ሲል ከተከሰተው አለመረጋጋት በተጨማሪ በዚያው ሰሜን ሸዋ መንዲዳ በተባለ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በኩልም ተመሳሳይ ግጭቶች መስተዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።     

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW