በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ድርቅ “የከፋ ረሐብ” እንዳስከተለ ነዋሪዎች ተናገሩ
ረቡዕ፣ መስከረም 27 2019
በአማራ ክልልሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ደጃች ሜዳ ወረዳ በወረዳው የተለያዩ ቀበሌዎች በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ወረዳው ከተማ ቢመጡም ምንም ዓይነት የምግብ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ተገለጸ። በወረዳው ከረዋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደሴ ተፈራ የክረምቱ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመመጣቱ ባስከተለው ድርቅ ምክንያት የቀበሌው ነዋሪዎች ለስደት መዳረጋቸውን ይናገራሉ።
በአካባቢው የተከሰተው "በጣም ከባድ ድርቅ ነው" የሚሉት አቶ ደሴ የቸገረው ሕዝብ ለወረዳው አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርብም "የሚቀመስ የለንም" የሚል ምላሽ እንደተሰጠ አስረድተዋል። "ህዝቡ አሁን በስደት ላይ ነዉ ያለዉ፤ አብዛኛው ወደ ዲማና ማይጸብሪ አካባቢ ሔዷል" ሲሉ ተናግረዋል።
በድርቅ ምክንያት "በጣም የከፋ ረሐብ" መከሰቱን የገለጹት አቶ ደሴ "እንደዚህ ዓይነት ዘመን አይተን አናውቅም። በ1977 አካባቢ እንደዚህ ዓይነት ድርቅ ነበር ይሉናል አባቶቻችን፤ በጣም በዚህ ዓመት ያለው ድርቅ በጣም የከፋ ነው" በማለት ሁኔታውን አብራርተዋል።
"መታመምም... መሞት ነው በቃ"
በዚያው በደጃች ሜዳ ወረዳ የአገጣ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ቄስ መብራቱ በበኩላቸው "ጎንበስ ብንል ምድር ነው፣ ቀና ብንል ሰማይ ነው፣ ምንም በቃ ህዝቡ መሄጃ ጠፋው" ሲሉ ይናገራሉ። "ሰዎች እየሞቱ ነው፣ እንስሳዎች እየሞቱ ነው! መታመምም... መሞት ነው በቃ" የሚሉት ቄስ መብራቱ ከመስከረም 16 ቀን 2019 ጀምሮ "ስምንት ሰው ሞቷል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሰዎቹ የሞቱት በረሐብ ነው፣ ሌላ ምንም የለም፤ ሌላ ምንም የለም። ጦርነት የለም እኛ አካባቢ፤ በረሐብ ነው" በማለት አስረድተዋል። የረን ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ እሸቴ በረከተአብ "ሰው በራብ እየሞተ ነው" ሲሉ ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተዋል። የምግብ እህል መወደዱን የገለጹት አቶ እሸቴ በድርቅ ምክንያት "በዚህ ምንም አዝመራ የሚባል የለም" ሲሉ በአካባቢው የተፈጠረው ድርቅ ያስከተለውን ተጽዕኖ አብራርተዋል።
እህል የመሸመት አቅም ያለው ሰው ቢኖር እንኳ የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ስደትን ምርጫ ለማድረግ ምክንያት ሆኖ የረን ቀበሌ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን አቶ እሸቴ ይናገራሉ።
"ወደ ዲማ እያለ ማይጸብሪ አካባቢ... ወደ እሱ ነው መሄድ ያለው። ደግሞ ትግራይ ተሻግሯል። እዚያ አሁን ጦርነቱ ገባ እንጂ አዝመራ ያላት ሀገር ነበረች። እዚያ የቀን ሥራ ብናገኝ እያልን ነው፤ ወደ እሱ መሄድ ነበረ። በእዚያው የሄደው እንጃ፤ በጦርነቱ እንዴት እንደሆነ በጣም ከብዷል አዎ። እየተፈናቀለ ነው ከሀገሩ" ሲሉ አስረድተዋል።
ለበርካታ ወራት ዝናብ ያላገኙ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ደጃዝማች ሜዳ ወረዳ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ተማሪዎች ለትምህርት ቢመዘገቡም ወደ ስደት እየሄዱ በመሆኑ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ ሆኗል ይላሉ።
"እስካሁን ባለው ደረጃ የቀረበ ነገር የለም"
"ማህበረሰቡ አትመዝግቡ፤ ምን እየበላን እናስመዘግባለን? አትመዝግቡ እስክትሄዱ ድረስ እያለ አብዛኛው በስደት እየሄደ እንጂ... ዞሮ ዞሮ አብዛኛው ተመዝግቧል። የተወሰነ ቢቀርም፣ ቢመዘገብ ባይመዘገብም ምን ዋጋ አለው? ምክንያቱም የምግብ አቅርቦት ሰዓት ካልተገኘ፣ የሚቀመስ ከሌለ ቢመዘገብ ባይመዘገብ ምን ዋጋ አለው?"
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የጠለምት ደጃዝማች ሜዳ ወረዳ ነዋሪም ከተለያዩ ቀበሌዎች በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በወረዳው ከተማ የተጠለሉ ህፃናት ለህመም መጋለጣቸውን ይናገራሉ።
"እስካሁን ድረስ ምንም ነገር የለም፤ ዞሮ ዞሮ መንግሥት ይቀርባል እያለ ነው ያለው። ግን እስካሁን ባለው ደረጃ የቀረበ ነገር የለም። እንጂ ሰዎቹ ያው ስደቱ እየጨመረ ነው ያለው፣ በጣም አሰጋሪ ነው። ሰዎች እግራቸው አብጦ፣ ሰውነታቸው ቆስሎ... እንግዲህ ብታዩአቸው በጣም ያሳዝናል። ምንም ማድረግ አንችልም። እሱ መንግሥት አዳራሽ ተጠልለው ነው የሚገርምህ፤ ያዩአቸዋል። በየቀኑም ያዩአቸዋል። ግን ደጃዝማች ሜዳ ያሉ በቃ እንዳለ ታያለህ ህዝብ በቃ አንድ ላይ... በጣም ብዙ ሰው ታያለህ። ህፃናት ብታያቸው እዚያ እግራቸው አብጦ ብታያቸው በጣም ያሳዝናሉ በቃ። ትላንት አሁን የመጡ ነበሩ፤ በቃ በጣም ያሳዝናል፣ ለማየት ራሱ ይዘገንንሃል።"
በዚህ ዜና ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ ለሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ እና ለአማራ ክልል አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ስልክ በመደወልና መልዕክት በመላክ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ባላመስጠታቸው በዚህ ዜና ላይ ማካተት አልተቻለም። በጠለምት ወረዳ ሥር የሚገኘው አካባቢ በ2017 ክረምት ተመሳሳይ ድርቅ ተከስቶ የቤት እንስሳት ለሞት ዳርጓል።
ኢሳያስ ገላው
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ