1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሰሞኑ ውጤት «ህዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን» የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ መስከረም 16 2018

በጃፓን ቶኪዮ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንደሚጠይቅ አስታወቀ፡፡ፌዴሬሽኑ ዛሬ በጽህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ውጤቱ ከስኬታማው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ የማይጠበቅም ነው ብሏል፡፡ ዘርፉን ለመለወጥ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

 የፌዴሬሽኑ ፕረዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህን እና አትሌት መሠረት ደፋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ
በጃፓን ቶኪዮ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መግለጫ ሰጥቷል።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በሰሞኑ ውጤት «ህዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን» የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ባስመዘገበችበትና 198 አገራት በተሳተፉበት የጃፓኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 53 አገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተው አጠናቀዋል፡፡ ከወትሮውም በላቀ የአትሌቲክሱ ውጤት የምትጠበቀው ኢትዮጵያ ግን በዚህ መድረክ 22 ደረጃ ላይ በመቀመጥ ነው እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበችው፡፡

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ ጋዜጠኞችን ጠርቶ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተገኘው ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ልዑካን ቡድኑ ማዘኑን አስታውቋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕረዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህን በዚሁ ወቅት ፌዴሬሽኑ ህዝቡን ይቅርታ እንደምጠይቅም አስታውቋል፡፡ “ውጤታማነታችንን ባለማስጠበቃችን ህዝቡንም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስም ይቅርታ ለመጠየቅ እንወዳለን” ያለው ስለሺ ህዝቡ ከዚህ የተሸለ ውጤት ይጠብቅ እንደነበር አመልክቷል፡፡

የተገኘው ውጤት ዝቅተኛነት

ምንም እንኳን የተገኘው ውጤት ዝቅተኛ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ከሰራቸው አበይት ተግባራት አንዱና ዋናው ከአትሌቶች ምርጫ ጋር የተያያዘ አጨቃጫቂ ነገሮች መቅረታቸው ነው ያለው አትሌት ስለሺ ፌዴሬሽኑ እያከናወነ ያለው የአሰራር ለውጥ ስራ ግን ባለመጠናቀቁ ነባሩን አሰራር በመከተል ወደ ሻምፒዮናው አትሌቶችን መላካቸውንም ገልጸዋል፡፡ “የምርጫ መስፈርቶች በጊዜ ተዘጋጅተው ከዚህ በፊት የነበረው አጨቃጫቂ የምርጫ አሰራሮች እንዲወገዱ አድርገናል” በማለትም ወደ ሃላፊነት የመጣው አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር ግን ገና ስምንተኛ ወር ላይ በመሆኑ ወደዚህ መድረክ አትሌቶች ስላኩ በነባሩ የምርጫ እና የስልጠና ሂደት አሰራር እንደሆነ አስገንዝበዋልም፡፡

በጃፓን ቶኪዮ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት በተመለከተ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መግለጫ ሲሰጥምስል፦ Seyoum Getu/DW

የትራክ ችግር

አትሌቶች ልምምድ የሚሰሩበት ትራክበኢትዮጵያ ባለው የስታዲየም ችግር ምክንያት ፈተና ሆኖ መቆየቱን በዚሁ ወቅት ያመለከተው ፌዴሬሽኑ እንደ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁሉ ችግሩ ባሁን ወቅትም በመጉላቱ ውጤት በማሳጣትም በኩል ሚናው ከፍ ማለቱ ተጠቁሟል፡፡ ይህ የትራክ ችግር ደግሞ ለኢትዮጵያ

አትሌቶች ፈተና መሆኑን አትሌት ስለሺ አስታውቋል፡፡ “ባለፉት 5 ዓመታት ግድም ያው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የትራክ እጦት ነበረበትና አትሌቶቻችን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረን ክትትል በማድረግ አደአበባ ስታዲየም ማሟሟቂያ ለውድድሩ አንድ ወር ግድም የመጨረሻ ስልጠና አካህደናል” በማለት የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት አለመጠናቀቅ ከዚህ ከትራክ ስልጠና አኳያ ክፍተት መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡

ስልጠና እና ዝግጅ

ስልጠናና ዝግጅት በተመለከተ ግን አስፈላጊውን ግብዓት ፌዴሬሽኑ ለአትሌቶች ማሟላቱንም በመግለጽ በዓለም አትሌቲክስ በተሰጠው ጥብቅ አቅጣጫ መሰረት ለ23 ሴት አትሌቶች የጾታ ምርመራ መደረጉን አስረድተዋልም፡፡ አትሌቶችን ለማበረታታት ብሎም በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን ስልጠና ለመስጠት ጥረት መደረጉንም ፌዴሬሽኑ አመልክቷል፡፡ ወደጃፓን ያቀናው የአትሌትክስ ልዑክ ቡድን አንዱ ያሳከውንም ነጥም አትሌት ስለሺ ስያክል፤የዓለም አትሌቲክስ ከውድድሩ ሁለት ቀን ቀድሞ በሚያዘጋጀው መድረክላይ መሳተፋቸው ነው፡፡ “በየአራት ዓመቱ የሚቀርበውን ውድድር የማዘጋጅት ጨረታ በተለይም ኦብዘርቨር ቡድን አቋቁመን ዶክመንት አዘጋጅተን ከባህልና ስፖርትም ተሳትፈው አድረገዋል” በማለትም በተለይም ከዓለም አትሌቲክስ ኃላፊ ሰባስቲያን ኮ ጋር በኢትዮጵያ እየተደረገ ባለው የአትሌቲክስ ልማት ላይ ምክክር መደረጉን ብሎም ዋና ኃላፊው አዲስ አበባ በመምጣት የአትሌቲክስ ልማቱን በተለይም የአትሌቲክስ መሰረተ ልማትን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በግንባታ ላይ ያለውን የአደ አበባ ስታዲየም ለመጎብኘት እንደሚመጡ መገለጹንም አትሌት ስለሺ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

በጃፓን ቶኪዮ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሰጠው መግለጫ ዘርፉን ለመለወጥ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንወደ ጃፓን ያመራው ሶስት ወርቅ፣ አራት ብር እና አራት ነሃስ አግኝቶ ለመመለስ ቢሆንም ያለ ወርቅ የተመለሰው ልዑኩ ሁለት ብር እና ሁለት ነሃስ በአጠቃላይም አራት መዳሊያ ብቻ በማሳካት ነው የተመለሰው፡፡ ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአቋም በታች ሆነው የቀረቡበት፣ ማጣሪዎችን እንኳ ለማለፍ የተቸገሩበትና ውድድሮችን እያቋረጡ የወጡበት በሚልም በአሉታዊ ጎኑ ተነስቷል፡፡ አትሌቶች እና አሰልጣኖች ጋር የተስተዋለው የመታዘዝ ፍላጎት ማጣትና የቡድን ስራ መላላት ለውጡት ማሽቆልቆል አይነተኛ ሚና እንደተጫወተም በተገለጸበት በዛሬው መግለጫ ፌዴሬሽኑ እያከናወንኩ ነው ባለው የአሰራር ለውት ስራ እንደሚታረም ነው የተመላከተው፡፡

ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW