1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች

ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2016

የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ ግድያን ጨምሮ እየደረሰባቸው ነው የተባለ አፈና፣ ጥቃት፣ የተሸከርካሪ ንጥቂያ እንዲሁም በመጋዘን የሚገኝ የዕርዳታ አቅርቦት ዝርፊያ መፍትሔ እንዲበጅለት የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጠየቀ።

Symbolbild Äthiopien Ankunft des Konvois mit Hilfslieferungen in Tigray
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

በሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች

This browser does not support the audio element.

የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች  

የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ ግድያን ጨምሮ እየደረሰባቸው ነው የተባለ አፈና፣ ጥቃት፣ የተሸከርካሪ ንጥቂያ እንዲሁም በመጋዘን የሚገኝ የዕርዳታ አቅርቦት ዝርፊያ መፍትሔ እንዲበጅለት የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጠየቀ። የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች ክልሎች በሰብአዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መበራከቱን በሥሩ ካሉ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት አንድ የረድዔት ሠራተኛ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ሰሞኑን ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

የሲቪክ ድርጅት ሠራተኞች ግድያ፣ አፈና እና ሌሎች ጥቃቶች እየደረሰባቸው ነው 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ደህንነት እንዲጠበቅ የጠየቀው የሚፈፀሙት ድርጊቶች "የእርዳታ አገልግሎቶችን እና የሰብአዊ እንቅስቃሴዎችን እያደናቀፉ" መሆኑን በመጥቀስ ጭምር ነው። 

ምክር ቤቱ በሰብዓዊ ድጋፍ  ሠራተኞች ላይ የግድያ እና የአፈና ጥቃቶች፣ ተሸከርካሪዎችን መንጠቅ እና በመጋዘን የሚገኙ የዕርዳታ አቅርቦቶች ላይ ዝርፊያዎች እንደተፈፀሙ በማዕቀፉ ሥር ያሉ የሲቪክ ድርጅቶች እንደገለፁለት ጠቅሷል። 

ኦሮምያ ክልል ውስጥ የተቃጠለ አምቡላንስምስል Solomon Muchie /DW

እንደነዚህ ያሉት ክስተቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ሲስተዋሉ የነበሩ ቢሆንም "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል ውስጥ ጎልተው እየታዩ" መሆኑን ያመለከተው ምክር ቤቱ፣ መሰል ድርጊቶች ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሱ ይገኛሉ ብሏል።  

መሰል ጉዳዮች የቀይ መስቀል ማህበርም የሚጋፈጣቸው ናቸው 

የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች እና ድርጅቶች ችግሮችን ተቋቁመው ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አቅመ ደካማ እና ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያደንቅ የገለፀው ምክር ቤቱ በየአካባቢው የሚገኙ ዜጎች በበጎ ሥራ ላይ ለተሰማሩት ሰዎች ከለላ እንዲያደርጉ ጠይቋል። 

እንዲህ ያለው ችግር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርንም የሚያሳስብ መሆኑን ድርጅቱ ደጋግሞ ገልጿል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሠራተኞቹ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚሰጡ አባላቶቹና ለነፍስ አድን ሥራ አጋዥ በሆኑት አምቡላንሶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተደጋግመው የደረሱበት መሄኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰብአዊ ዲፕሎማሲ እና ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መስፍን ደረጄ ይህ አሁንም እየገጠማቸው ያለ አደጋ መሆኑን ተናግረዋል። 

"ማንነታቸው በማይታወቁ ታጣቂ ኃይሎችየተለያዩ ሠራተኞቻችን፣ በጎ ፈቃደኞቻችን ሕይወት አልፏል። ባለፉት አራት አምስት ዓመታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አምቡላንሶቻችን ላይ ውድመት ደርሷል።" 

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ ግድያን ጨምሮ አፈና፣ ጥቃት፣ የተሸከርካሪ ንጥቂያ እንዲሁም በመጋዘን የሚገኝ የዕርዳታ አቅርቦት ዝርፊያ ይካሄዳል ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የፀጥታ መናጋቶች ያስከተሉት እገታ እና የጥቃት አዝማሚያ  

ሰሞኑን አንድ የረድዔት ድርጅትሠራተኛ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ያልታወቁ በተባሉ ታጣቂዎች ከታገተ በኋላ መገደሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቃል። 

ይህንን ግድያ ጨምሮ በኢትዮጵያ ከጥር ወር ወዲህ ብቻ ስምንት የረድዔት ሠራተኞች መገደላቸውን እንዲሁም ሌሎች 14 ሰዎች ለገንዘብ በሚል ምክንያት እገታ እንደተፈፀመበቸው ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ያሳያል። የሲቪክ ድርጅቶች በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራት አዳጋች እንደሆነባቸው የአንድ ድርጅት መሪ ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ ገልፀው ነበር። 

"ዛሬ መንቀሳቀስ አንችልም። ይሄ በሥራችን ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮብናል። በመኪና ሄዶ ተንቀሳቅሶ መሥራት የማይታሰብበት ሁኔታ ነው።" 

ግጭት ባልተለያቸው በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች  ንፁሃን ዜጎች፣የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች፣ ተጓዥ ተማሪዎች እና ሌሎችም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ እገታ እየተፈፀመባቸው ማስለቀቂያ ገንዘብ - ቤዛ ሲጠየቅባቸው መመልከት እየተለመደ ነው።  

ሀገሪቱ የገባችበት የፀጥታ መናጋት እና የሚደረጉ የእርስ በርስ የትጥቅ ግጭቶች መሠል ድርጊቶች እንዲበራከቱ ስለማድረጋቸው ይነገራል። 

 

ሰለሞን ሙጨ
ሂሩት መለሰ
ፀሀይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW