በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ መተግበሪያዎች እና የመረጃ ስርቆት ስጋት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ተክቶ በመስራት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው።ይህም ጊዜን እና ወጭን በመቆጠብ ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ይገኛል።ከዚህ አንፃር በAI ላይ የተመሰረቱ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር በመላው አለም በፍጥነት እያደገ ነው።ለምሳሌ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተው እና ቻትጂፒቲ /ChatGPT/ የተባለው መተግበሪያ ከጎርጎሪያኑ ከጥር 2025 ጀምሮ በግምት 122.58 ሚሊዮን ዕለታዊ ንቁ ተጠቃሚዎች አሉት።ይህም በዓለም ዙሪያ ከ65 ሰዎች ውስጥ አንዱ በየቀኑ ይህንን መተግበሪያ ይጠቀማል ማለት ነው።ለመሆኑ እነዚህ መተግበሪያዎች እንዴት ነው የሚሰሩት።የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብሩክ ወርቁ ማብራሪያ አላቸው።
በዚህ መንገድ የ AI መተግበሪያዎች የሚሰጡት ጥቅም ፣ ምቾት እና አቅም የማይካድ ቢሆንም፣ ባለሙያዎች በግል መረጃዎች ላይ ስጋቶች መኖራቸውን ያስጠነቅቃሉ። የ AI መድረኮች የተጠቃሚ ውሂብን የሚሰበስቡበት፣ የሚያከማቹበት እና የሚጠቀሙበት መንገድ ላይም ጥያቄዎች ይነሳሉ።ይህም በውሂብ ጥበቃ እና በተጠቃሚዎች ፈቃድ ላይ አሳሳቢነቱ እንዲጨምር አድርጓል።እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ ቴክኖሎጂው አዲስ መሆኑ እና በተጠቃሚዎች ዘንድ ስለአጠቃቀሙ በቂ እውቀት አለመኖር ደግሞ ስጋቱን የበለጠ አድርጎታል።
የግል መረጃን ከተጠቃሚዎች መሰብሰብ
በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ መተግበሪያዎች በርካታ መረጃን ከተጠቃሚዎች በመሰብሰብ ሞዴሎቻቸውን ለማሠልጠን ጥቅም ላይ ያውሉታል። ማለትም ተጠቃሚዎች በፎቶ ወይም በፅሑፍ የሚሰጡት መረጃ በመተግበሪያዎቹ የመረጃ ቋት ውስጥ በማከማቸት እና በመተንተን ተጠቃሚዎች ለሚጠይቁት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሊያገለግል ይችላል ።ከዚህ አንፃር ተጠቃሚዎች በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ መተግበሪያዎችን ሲጠቀሙ ስለሚያገኟቸው መረጃዎች ብቻ ሳይሆን ስለሚሰጧቸው ግላዊ ወይም ሚስጥራዊ መረጃዎችም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ባለሙያው ያስጠነቅቃሉ።ያ ካልሆነ ግን በግለሰብም ሆነ በተቋማት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ተጠቃሚ መረጃዎቻቸውን ከመስጠታቸው በፊት መረጃው እንዳይከማች የሚያደርጉ አማራጮች እና የመቆጣጠሪያ መንገዶች መኖራቸውን የሚገልፁት አቶ ብሩክ ነገር ግን ይህንን ባለማወቅ ተጠቃሚዎች ራሳቸውን እንደማይጠብቁ ይገልጻሉ።ይህ በሚሆንበት ጊዜ በቂ የመረጃ ጥበቃ ባለመኖሩ ማንኛውም የስርዓቱን ቁጥጥር አልፎ የገባ አካል የተጠቃሚን መረጃ ሊያገኝ እንደሚችል ያስረዳሉ።
ተጋላጭነትን ለመቀነስ መደረግ ያለባቸው የመፍትሄ ርምጃዎች
ስለሆነም ይህንን መሰሉን የመረጃ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ከመጀመራቸው በፊት እያንዳንዱ መተግበሪያ የራሱ የሆነ የግል መረጃ ጥበቃ ፖሊሲ /privacy policies/ ስላለው ፖሊሲውን በዝርዝር መመልከት እና መረዳት ይጠበቅባቸዋል።በተጨማሪም የግላዊነት ቅንብሮችን /privacy settings/ ማንበብ እና መቆጣጠር የሚያጋሩትን መረጃ መምረጥ፣ በጂሜይል ውስጥ ያሉ እንደ ስማርት አሲስታንስ /smart assistants/ ያሉ የውሂብ መሰብሰቢያ መንገዶችን አለመጠቀም ይመረጣል። እንደ ግል አድራሻ ፣ፎቶ እንዲሁም የጤና ፣ የገንዘብ ነክ እና እንደ ህጋዊ ሰነዶች ያሉ ሚስጥራዊ የግል መረጃዎችን ከማጋራት መቆጠብያስፈልጋል።እነዚህ ዲጅታል መድረኮች ሲጠቀሙ ስም አድራሻ እና ማንነታቸውን መደበቅም ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ከዲጅታል መድረኮቹ ከተገኙ መረጃዎችን በቀጥታ ከማጋራት ይልቅ ተገቢ ማጣራት ማድረግ ፣ምንነታቸው ለማይታወቅ መሳሪያዎች መረጃ አለመስጠት፣እና ባለብዙ ደረጃ የይለፍ ቃሎችን በመጠቀም ተጠቃሚዎች መረጃን መጠበቅ እንደሚችሉ መክረዋል።
ዓለማቀፋዊ የአጠቃቀም ህግ እና መመሪያ ማውጣት
ችግሩን ለመካላከል በተጠቃሚዎች ከሚወሰዱ የጥንቃቄ ርምጃዎች ባሻገር በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ገዢ የሆነዓለማቀፋዊ የአጠቃቀም ህግ እና መመሪያ ማውጣትአስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ያሳስባሉ።ጉዳዩ ያሳሰባት ቻይናም ሰሞኑን በሻንጋይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኮንፈረንስ (WAIC) መክፈቻ ላይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ደንብ ላይ ዓለም አቀፍ 'ስምምነት' እንዲደረግ ጠይቃለች።እንደ ሁዋዌ እና አሊባባ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች እንዲሁም እንደ ቴስላ፣ አልፋቤት እና አማዞንን የመሳሰሉ የአሜሪካ እና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ ከ800 በላይ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በተሳተፉበት እና በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ በመከረው በዚህ ስብሰባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽም የኤ አይ ደንብ "የአለም አቀፍ ትብብር ፈተናን የሚፈታ ነው” ሲሉ በኮንፍረንሱ የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።አቶ ብሩክ በበኩላቸው ህግ መውጣቱ መልካም ቢሆንም የህግ ማዕቀፉ ሲወጣ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ