1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ የታገዘው የአውሮፓ የስደት ቁጥጥር

ረቡዕ፣ መስከረም 15 2017

በጦርነት፣ በድህነት ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች በግዳጅ የተፈናቀሉ እና የተሻለ ህይወት ፈልገው ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሜዲትራኒያን ባህር አደገኛውን የጀልባ ጉዞ የሚያደርጉ ስደተኞች አሁን የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ዒላማ ሆነዋል።ምክንያቱም የአውሮፓ ህብረት ስደትን ለመቆጣጠር የተለያዩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎችን እየተጠቀመ ነው።

Panama Klimawandel Meeresspiegel
ምስል Matias Delacroix/AP Photo/picture alliance

በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ የታገዘው የአውሮፓ የስደት ቁጥጥር

This browser does not support the audio element.

ድንበርን የሚቆጣጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀምን ጨምሮ  በአውሮፓ ስደተን ለመከላከል በርካታ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ቴክኖሎጅዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት የነዚህን ቴክኖሎጅዎች አጠቃቀም፣ ተግዳሮት እና በስተደተኞች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ይቃኛል።
በጦርነት፣ በድህነት ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች በግዳጅ የተፈናቀሉ እና የተሻለ ህይወት ፈልገው ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሜዲትራኒያን ባህር አደገኛውን የጀልባ ጉዞ የሚያደርጉ ስደተኞች አሁን የአዲሱ የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ዒላማ ሆነዋል።
ምክንያቱም የአውሮፓ ህብረት ስደትን ለመቆጣጠር የተለያዩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎችን እየተጠቀመ ነው። ከነዚህም  መካከል፣ ድንበርን የሚቆጣጠሩ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚንቀሳቀሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ይገኙበታል።

ድንበርን የሚቆጣጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች

ድንበርን የሚቆጣጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የውጭ ድንበሮችን በቅርብ ለመከታተል የአውሮፓ ህብረት ጥቅም ላይ ይውላሉ።በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙት እነዚህ አውሮፕላኖች በቀጥታ መልዕክትን የሚያስተላልፉ ሰዎችን እና መኪናዎችን የሚለዩ እና የሚከታተሉ ዘመናዊ ካሜራዎችን የተገጠመላቸው ናቸው።በዚህ ሁኔታ እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ አውሮፓ ድንበር የሚመጣ ማንኛውንም ሰው ለአካባቢው ባለስልጣናት ያሳውቃሉ።  
ጀርመናዊው የሰው አልባ አውሮፕላን ተመራማሪው ክርስቲያን ካይዘር፤  ስለአሰራሩ እንዲህ ይላሉ።
«ሰው አልባ አውሮፕላኑ እንዲነሳ ትእዛዝ ይቀበል እና በጊዜ ሰሌዳ የታቀደለትን መንገድ ይጓዛል። ከዚያም አንድ ነገር ሊያገኝ ይችላል።ለምሳሌ ሶፍትዌሩ በ1.5 ኪሎሜትር ርቀት በአካባቢው ሰው ካገኘ። ሰው አልባ አውሮፕላኑ “አቁም” የሚል ትእዛዝ ይሰጣል።ለቁጥጥር ማዕከሉም በቀጥታ በምስል ያሳውቃል።»
ምንም እንኳ ይህ ቴክኖሎጅ ለሀገራት የድንበር ቁጥጥር ጠቃሚ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ግን ስደተኞችን ይገፋል ሲሉ የመብት ተሟጋቾች ይተቹታል።ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳምኒ ሳቲያ ይህ ቴክኖሎጅ ተገን ጠያቂዎችን ይገፋል ከሚሉት መካከል ናቸው።
«እነዚህ መሳሪያዎች ስደትን ባልተመጣጠነ ሁኔታ አስቀድሞ  ወደ ኋላ ለመግፋት እና በጉዞ ላይ ያሉ ሰዎች ወደ አዳዲስ ግዛቶች መድረስ እንዳይችሉ መብታቸውን  ለመከልከል ያገለግላሉ።»

ድንበር ጠባቂ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ አውሮፓ ድንበር የሚመጣ ማንኛውንም ሰው ለአካባቢው ባለስልጣናት ያሳውቃሉ።  ምስል Sofiia Bobok/AA/picture alliance

የስደት እና የሰብዓዊ መብት ጠበቃዋ ፔትራ ሞልናርም ከግል መረጃ ጥበቃ አንፃር ሌላ ስጋት ያነሳሉ።
«እንደ የፊት ለይቶ ማወቂያ ስካን ያሉ እና የተለያዩ የባዮሜትሪክ መረጃዎችች በድንበር ላይ የሚሰበሰብ ማንኛውም  አይነት መረጃ፣ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል። እና ደግሞ መረጃው ወዴት እንደሚሄድ ወይም ለምን ዓይነት ዓላማዎች እንደሚውል አናውቅም። ይህ ዓይነቱ ነገር በስደት ውስጥ ብዙ ጊዜ ይከሰታል። ለምሳሌ ለአንድ አላማ መረጃን ትሰበስብ እና በድንገት ለህግ አስከባሪ አካላት ወይም ለሌላ አካል እንደተጋራ ትገነዘባለህ።»

የስደተኞችን እውነታ የሚመረምረው ቴክኖሎጅ 

የተገን ጠያቂዎችን  እውነታ የሚመረምረው  በሰውሰራሽ አስተውሎት የታገዘው ሶፍትዌር የአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው ቴክኖሎጅዎች አንዱ ነው። ይህ ቴክኖሎጅ አንድ ተገን ጠያቂ  የተናገረው እውነት ስለመሆኑ የፊት ገጽን በማጥናት መረጃ ይሰጣል።
ከአውሮፓ በከፍተኛ ደረጃ ፍልሰተኞችን የምትቀበለው የጀርመን የፍልሰት ባለሥልጣናት፤ በተወሰነ መጠንም ቢሆን  ያለ መታወቂያ ወደ አገሪቱ የሚመጡትን ተገን ጠያቂዎች አመጣጥ ለመፈተሽ ይህንን ቴክኖሎጅ በረዳትነት በመጠቀም ላይ ናቸው። ሶፍትዌሩ የአንድን ሰው የአነጋገር ዘዬ በመተንተን ከአንዳንድ አካባቢዎች ጋር ያዛምዳል። ይህም ማለት አንድ ሰው ከየት እንደመጣ የሰጠው ዝርዝር መረጃ ትክክል ስለመሆኑ ለማረጋገጥ እና ጥገኝነት ለመጠየቅ የተነሳበት ምክንያት አሳማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
በስዊዘር ላንድ የሶፍትዌር ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት ዓለሙ እንደሚሉት የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ በስልጠና ከተሰጠው  መረጃ ውጭ  ልክ እንደ ሰዎች ስሜት እና ርህራሄ ስለሌለው እንዲሁም ግራ እና ቀኝ በማየት በአመክንዮ ነገሮችን ስለማያገናዝብ የሚሰጠው ውሳኔ ትክክል ላይሆን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ የሰዎች የፊት ገፅታ ላይ የሚታይ ስሜት እና እንቅስቃሴ ከየመጡበት ሀገር ባህል፣ ልማድ እና ወግ እንዱሁም ከሚከተሉት ከሀይማኖት አንፃር የተለያዬ ትርጉም ሊኖረው ስለሚችል ፤ ጉዳዩ ማሽኑ ከሚረዳው በላይ ይሆናል።ከዚህ አኳያ ቴክኖሎጅውን ለቀላል ክንውኖች እንጅ ለእንዲህ አይነት ወሳኝ ነገሮች መጠቀም ጉዳት አለው ባይ ናቸው።
ስለሆነም በዚህ ሁኔታ የሚወሰነው ውሳኔ ስደተኞችን ላልተገባ ችግር ሊዳርግ የሚችል በመሆኑ ቴክኖሎጅው እስኪዳብር ጊዜ ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው።

አቶ ዳዊት ዓለሙ፤ የሶፍትዌር መሀንዲስምስል Privat

ምን ያህል ሰዎች እንደሚሰደዱ የሚተነብየው ቴክኖሎጅ 

ሌላው ስደትን በተመለከተ በአውሮፓ ጥቅም ላይ የሚውለው የሰውሰራሽ አስተውሎት መሳሪያ ምን ያህል ሰዎች በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ይገደዳሉ? በሚል ትንበያ የሚያስቀምጠው በዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል የተዘጋጄው «ፎርሳይት»/Foresight/ የተባለው ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ  ከአንድ እስከ ሶስት ባሉት አመታት  ውስጥ ምን ያህል መፈናቀል እና ስደት ሊከሰት እንደሚችል ለመተንበይ ይውላል።
የዴንማርክ የስደተኞች ምክር ቤት፡የአለማቀፋዊ ትንበያ  ሀላፊ፣ አሌክሳንደር ኪጄረም እንደገለፁት ለትንበያው ግብዓት በተለያዩ መንገዶች መረጃ ይሰበሰባል።
«ጥቅም ላይ የሚውሉትን ይፋዊ የዊሂብ ምንጮች፤  ከታማኝ የመረጃዎ ምንጮች፣ በተለይም የተባበሩት መንግስታት እና የዓለም ባንክን ከመሳሰሉት ድርጅቶች ይጠቀማል። የተወሰኑ ታሪካዊ መረጃዎችንም ይጠቀማል። የ25 ዓመታት ታሪካዊ መረጃዎችን ከ140 በላይ ከሆኑ ጠቋሚዎች ላይ ይወስዳል።»ብለዋል።
ይህ የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ካለፉት ግጭቶች ታሪካዊ' መረጃን በመጠቀም የሰለጠነ ነው። አሁን፣ በመካሄድ ላይ ያሉ ግጭቶችን ተመልክቶ በሚቀጥሉት ከአንድ እስከ ሶስት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ሰዎች በግዳጅ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ይተነብያል። በአሁኑ ጊዜ መሣሪያው በ 26 አገሮች ውስጥ ሁኔታዎችን ይከታተላል።

በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሰዎችን ተክቶ የሚሰራ ቢሆንም፤እንደ ሰው ስሜትን መረዳት እና ማገናዘብ ስለማይችል ውስንነት አለበት።ምስል Dado Ruvic/Illustration/File Photo/REUTERS

ቴክኖሎጅው ውስንነቶች አሉበት

ይህ ዘዴ ከጎርጎሪያኑ በ2019 ዓ/ም ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ በዴንማርክ የስደተኞች ምክር ቤት የትንበያ ባለሙያው እንደሚሉት፤ ውስኑነቶች አሉበት።
«ከእነዚህ መሳሪያዎች ውሱንነቶች አንዱ እንደ ጋዛ ያሉ ሁኔታዎችን የመተንበይ ችሎታ ነው።በጥቅምት 7 ቀን የተከሰተውን ነገር ተከትሎ የመጣውን ጦርነት መተንበይ ለእነዚህ መሳሪያዎች በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ከእነዚህ ከመጀመሪያዎቹ ድንጋጤዎች በኋላ፣ በሁኔታው ላይ ያሉ ዋና ዋና ለውጦችን እና መፈናቀል እንዴት ሊፈጠር እንደሚችል  ለመረዳት በጣም ጥሩ ስለሚሆን ግን መጠቀም የተሻለ ወይም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።»ሲሉ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በርካታ ውስኑነቶች ያሉት ቴክኖሎጅ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ የገሃዱን ዓለም አድልዎ የሚደግምበት እና የሚያባዛበት መንገድ አንዱ ነው።ለዚህም «ማሽን ለርኒግ» የሚባለው የስልጠና ሂደት  ክፍተት ያለው መሆኑ በዋናነት ይነሳል።የሶፍትዌር ባለሙያው አቶ ዳዊት ዓለሙ ችግሩን በምሳሌ ያብራራሉ።

ከዚህ አንፃር ስደተኞችን በሚመለከት በአውሮፓ ጥቅም ላይ የሚውሉ በሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጅዎችም በመብት ተሟጋቾች ዘንድ እየተተቹ ነው።
በድሮን በእንቅስቃሴ መለያ ሴንሰር እንዲሁም በጣት አሻራ ከስደተኞች የሚሰበሰብ መረጃ እነሱን ሊጎዳ ለሚችል ተግባር ሊውል ይችላል እና፤ መንግስታት እና የአውሮፓ ህብረት የስደተኖችን የግል መረጃ  እንዲጠብቁ እና በመደብ፣ በፆታ እና በዘር  የሚፈፀሙ አድሎአዊነቶችን እንዲያስቀሩ  የመብት ተሟጋቾች በማሳሰብ ላይ ናቸው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW