በሱዳን በጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 83 ደረሰ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 17 2014
ማስታወቂያ
በቅርቡ ሱዳን ዉስጥ በጣለው ከባድ ዝናብ እና ከዚያ በኋላ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 83 መድረሱን የሀገሪቱ ብሔራዊ የሲቪል መከላከያ ምክር ቤት ገለፀ። በሱዳን በተከሰተዉ ጎርፍ ከ18,000 የሚበልጡ ቤቶች የወደሙ ሲሆን ሌሎች 25,000 ቤቶች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ የሱዳን የሲቪል መከላከያ ምክር ቤት ትናንት በሰጠዉ መግለጫ አስታዉቋል።
የሀገሪቱ የመስኖና የውኃ ኃብት ሚኒስቴር በበኩሉ በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ በመጪዎቹ ሁለት ቀናት ከብሉ ናይል እና የነጭ አባይ ወንዞች የሚፈሰዉ የውኃ መጠን እንደገና ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ሲል አስጠንቅቋል። ሚኒስትር መስርያ ቤቱ በሁለቱ ወንዞች አካባቢ በተለይም በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚኖረው ህዝብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል። በሱዳን የሚገኙት እነዚህ ወንዞች ከጎርጎረሳዊዉ 1946 ዓ.ም. በኋላ በከፍተኛ መጠን ሲሞሉ ለመጀመርያ ጊዜ መመዝገቡን ሚኒስቴር መስርያቤቱ አስቃዉቋል።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ