በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት የተቀሰቀሰዉ የጎሳ ግጭት
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 16 2014
ባለፈው ሳምንት በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት በሃዉሳ እና በርታ ጎሳዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ከ100 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ወደ 200 የሚጠጉ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እየጠበቁ ነዉ። የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት በተቀናቃኞቹ ጎሳዎች መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አካባቢው አስፍረዋል። ይህ አመፅ በመላው ሱዳን በሚገኙ የሃውሳ ጎሳዎችና ሴቶች ላይ ቁጣ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና መፈናቀል አሳሳቢ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ተፋላሚዎቹ ወገኖች በውይይት እንዲሳተፉና እርስ በእርሳቸው ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል። በብሉ ናይል ግዛት በኧል ሩሳሪስ አካባቢ የሃዉሳ ጎሣ ሁለት ገበሬዎች በመገደላቸው የተነሳው አመጽ ተቀሰቀሰና ወዲያው ወደ ጎሳ ግጭት ሰፍቷል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በካርቱም ፣ በካሳላ ፣ በጋዳሪፍና በሌሎች ከተሞች በጎሳ ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት በመቃወም የተቃዉሞ ሰለፍ ተካሂዷል ። ፖሊሶች ተቃዉሞዉን ለማበተን አስለቃሽ ጢስ ተጠቅመዋል። የሱዳን የህክምና ዶክተሮች ጥምረት ወደ መንግሥት በኧል ዳማዚን ግዛት ከተማ ላይ በተዛመተው የሦስት ኃይል የቀላቀለ ዉዝግብ ወደ 105 ሰዎች እንደተገደሉ እና ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች እንደተጎዱ ተናግሯል።
የዶቼ ቬሌ ዘጋቢ ሚሻኤል አቲቲ ከካርቱም እንደዘገበዉ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተቀሰቀሰዉን የጎሳ ግጭት ተከትሎ በካርቱም በተካሄደው የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ ያነጋገራቸዉ የሃዋሳ ጎሳ መሪ የታወቁ አዛዉንት መሐመድ ሰኢድ ኧል አሚር ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ጥሪ አድርገዋል። «የሐዋሳ ቤተሰብን የምንወክል ነን እናም በውስጥ ጉዳይችን ላይ ማንኛውንም አይነት ጣልቃ ገብነት አንቀበልም። ይህ የማህበራዊ ውሳኔያችን ሲሆን ከአላህ ሸሪዓ፣ ከሰው ሞራልና መርሆዎች ጋር እንዲሁም በሱዳን ህግ መሰረት መሰረት እየሰራን ነው።»
ይሁን እንጂ የሰላሙን መፍትሔ ማግኘት ፈታኝ ይመስላል። በኧል ናይላይን ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና የፖለቲካ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አሽራፍ አድሃም እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የጎሳ መሪዎች እንደ ፖለቲከኛ እየሰሩ በመሆናቸዉ በህብረተሰቡ መካከል የሚደረገውን ዉዝግብ ለመፍታት ባህላዊ የእርቅ ሂደቶች ውጤታማ አይደሉም ብለው ያምናሉ።
ባለፉት «ቀናት በሱዳን በሚገኙ የተለያዩ ጎሳዎች መካከል አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል የተለመደ ዘዴ ነበር ። ባለፉት አስርት ዓመታት ግን ፖለቲከኞቹ ባህላዊ መሪዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ወደ ፖለቲካው ጎራ እየጎተቱ ነው። ስለሆነም፤ ባህላዊ የእርቅ ሂደቶች ጥረት ትርጉማቸውን አጥተዋል።»
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሱዳን ባለስልጣናት በሁለቱ ተቀናቃኝ ጎሣዎች መካከል ያለውን ውጥረት ለማስወገድ ተጨማሪ የፀጥታ ኃይላትን ወደ አካባቢው ልከዋል። በአሁኑ ወቅት 14 ሺህ ያህል ሰዎች፣ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት በኧል ዳማዚን ግዛት ዉስጥ በሚገኙ የህዝብ ህንጻዎች እና ተቋማት ውስጥ ተጠልለው በተጨናነቀ ሁኔታ እና አካባቢዎች እየኖሩ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምቱን አስቀምጧል።
በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ካርዲያታ ሎ ንዴዬ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች እርስ በእርስ ተቀባይነት ያለው መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል። ሁኔታው በጣም አስጨናቂ እንደሆነም ነዉ የገለፁት።
«ነገሩ እጅግ በጣም አሳስቦኛል፤ ምክንያቱም ውድ የሆነዉ ሕይወት ጠፍቷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፤ በተለይ ሴቶችና ልጆች የፀጥታ ጥበቃና መጠለያ ማግኘት ነበረባቸው ። ወላጆች እና ህፃናት በትምህርት ቤቶች ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ከለላ ማግኘት ሲፈልጉ ማየት በጣም የሚያሳዝን ነው።»
ሎ ንዴዬ እንደተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ ድርጅቶች በብሉ ናይል ግዛት ውስጥ ለሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎች እርዳታ እየሰጠ ነዉ። የእርዳታ ድርጅቶች በዚህ የጎሳ ጥቃት ለተጎዱ ሰዎች አስቸኳይ የጤና ቁሳቁሶች፣ መድኃኒቶችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆም ተናግረዋል።
በሱዳን የተለያዩ ከተሞች የታየዉ ተቃዉሞ የተቀሰቀሰዉ በሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር አዋሳኝ ላይ በሚገኘው በብሉ ናይል ግዛት በሃዉሳና በበርታ ጎሳዎች መካከል በተነሳ የመሪት ይገባኝል ጥያቄ ነዉ። ግጭቱ የተቀሰቀሰዉ የሃዉሳ ጎሳዎች "የመሬት ይዞታን የመቆጣጠር መብት ለሲቪል ባስልጣናት" እንዲሰጥ ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ የበርታ ጎሳዎች ውድቅ ካደረጉ በኋላ መሆኑን የዓይን እማኞች ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ መግለፃቸዉ ተዘግቧል።
የሱዳን መንግሥት ባለፈዉ ቅዳሜ በብሉ ናይል ግዛት የፀጥታ ኃይላትን ካሰማራ በኋላ በሌሎች ቦታዎች ውጥረት ቢባባስም ሁኔታዉ የመረጋጋት ሁኔታ ይታይበታል ተብሎዋል። ካሰላ በምትባለዋ በምስራቃዊትዋ የሱዳን ከተማ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሃዋሳ ጎሳ ማኅበረሰቦች የመንግስት ህንጻዎችንና ሱቆችን በእሳት ካቃጠሉ እና ከከበቡ በኋላ መንግስት አካባቢዉ ላይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማገዱን የዓይን እማኞ ገልፀዋል።
ይህ የጎሳ ግጭት በሱዳን የተነሳዉ በሃገሪቱ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ነው። በሱዳን ከ14 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልገዉ ተገልጿል። .
የሱዳን በትረስልጣን ይዘዉ ለረጅም ዓመታት የገዙት ኦመር ኧል በሽር በጎርጎረሳዉያኑ ሚያዝያ 2019 ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በዳርፉር፣ በኮርዶፋን እና በምሥራቅ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭቶች ተስፋፍተዋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ