1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
መቅሰፍትአፍሪቃ

በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከሀገር ተሰድደዋል

ሐሙስ፣ ጥቅምት 7 2017

የከፋ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በተዘፈቀችው ሱዳን ከ1 ዓመት ከ6 ወራት ባነሱ ጊዜያት ውስጥ ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሀገር መሰደዳቸው ተዘግቧል ። ምናልባት ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ሳምንታት ውስጥ የተፈናቃዩ ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሊሆን እንደሚችልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥጋቱን ገልጧል ።

Sudan | Zusammenstöße in Khartum
ምስል AFP

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የስደተኛ ቁጥሩ ይጨምራል ተብሏል

This browser does not support the audio element.

የከፋ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በተዘፈቀችው ሱዳን ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ባነሱ ጊዜያት ውስጥ ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሀገር መሰደዳቸው ተዘግቧል ምናልባት ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ሳምንታት ውስጥ የተፈናቃዩ ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሊሆን እንደሚችልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥጋቱን ገልጧል

በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከ18 ወራት ባነሱ ጊዜያት ውስጥ ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)ዐሳወቀ ። ተመድ በእርስ በእርስ ጦርነቱ ወቅት ተባብሷል ሲል የጠቀሰው «ጭካኔ» ለገፍ ስደቱ ዋነኛ ሰበብ ነው ብሏል ። የተመድ የሱዳን የስደተኞች አስተባባሪ ማማዱ ዲያን ባልዴ በቀጣይ ሁለት እና ሦስት ሳምንታት የተፈናቃይ ስደተኞች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮንም ሊበልጥ እንደሚችል ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP)ተናግረዋል ። 

«ለሱዳናውያን፦ በግጭቱ መክፋት፤ በእርግጥም በግጭቱ እጅግ መባባስ የተነሳ 18 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተፈናቅሏል እነዚህ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች ናቸው፥ ለአብነት ያህል ወደ አገራቸው የተመለሱ ደቡብ ሱዳናውያን ይገኙበታል ስለዚህ አሁን የገጠመን ምናልባትም በቅርብ ዐሥርተ ዓመታት ውስጥ ካየነው ከለላ የማጣት ቀውስ የከፋውን ነው የሚያሳዝነው ነገር፦ ያቺ የዛሬዋ ሱዳን ነች »

ከነዚህ የሱዳን ስደተኞች  መካከል 25,000 ያህሉ ባላፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ቻድ የገቡ ናቸው ሲሉም አክለዋል ።  ድንበር እየተሻገሩ ከሚሸሹት ተፈናቃዮች መካከል 80 በመቶው ሕጻናት እና ሴቶች መሆናቸውም ተገልጧል ። እነዚህ ተፈናቃዮችም በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ሲጓዙ የድንበር ኬላዎችን፤ መሰናክሎችን እና ሚሊሺያዎችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ለማለፍ ይገደዳሉም ተብሏል ። ሰሜን ዳርፉ በሚገኘው የአቡ ሾክ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ሣላኅ አደም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን ተናግረዋል ።

«ሁኔታው እየተበላሸ፤ በጣም እየተበላሸ ነው ላለፉት ዐሥር ቀናት አሁን ይህች ከተማ ማለቴ እኔ የምኖርበት አቡ ሹክ መጠለያ ከቀን ቀን ቀስ እያለ በቦንብ እየተደበደበ ነው ።»

በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በአብዛኛው ተጎጂዎች ሕጻናት እና ሴቶች ናቸውምስል Thomas Mukoya/REUTERS

በሱዳን ጦር ሠራዊት (SAF) እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (RSF) መካከል በቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት ተፈናቅለው የሸሹት ተፈናቃዮች በአካባቢያቸው ርዳታ የሚያቀርብላቸው ለጋሽ ድርጅት እንደሌለ ተናግረዋል ። «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲል ደግሞ የገበያ ሥፍራዎች በየጊዜው እየተደበደቡ መሆናቸውን ተፈናቃዮች ገልጠዋል። 

«የቦንብ ድብደባው በዋናነት የሚያተኩረው በርካታ ሰዎች የዕለታዊ መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመግዛት ወደሚያቀኑባቸው የገበያ ሥፍራዎች ነው በአካባቢው አንድም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድርጅት የለም ያለ ሰብአዊ ድርጅቶች መኖር ደግሞ አስቸጋሪ ነው ሰዉ ደግሞ ልጆቹን እና ቤተሰቡን ለመመገብ በገበያ ሥፍራዎች ላይ ጥገኛ ነው »

የሱዳን የርስ በርስ ግጭት በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞት ዳርጓል ። ጠኔ መግባቱ የታወጀበት የሱዳን ምዕራባዊ ዳርፉር ግዛት የዛምዛም የመፈናቀያ ጣቢያን ጨምሮ 26 ሚሊየን ግድም ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት መዳረጋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP)ዘግቧል ። ከእነዚህ መካከል የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ባወጣው መረጃ መሰረት ወደ 2.95 ሚሊዮን የሚጠጉት የሀገሪቱን ድንበሮች አቋርጠው ተሰድደዋል ። በአጠቃላይም እስካሁን 11.3 ሚሊዮን ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገልጧል ። ሱዳን ከእርስ በእርስ ውጊያው ባሻገር ለከፋ የምግብ ቀውስ መዳረጓም ተዘግቧል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW