በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደረሰ የተባለው ጥቃት
ሐሙስ፣ መስከረም 24 2016
ሱዳን ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰሞኑን የደረሰበትን የጦር መሣሪያ ድብደባ ጥቃት አውግዞ ድርጊቱ በማን እንደተፈጸመ የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራ እንደሚያደርግ ገለፀ። ኤምባሲው «የተፈጸመው ድርጊት ሰብአዊ ጉዳት ባያደርስም፣ ተግባሩ የዓለም አቀፍ ሕግና የቪየና ስምምነትን የጣሰ» ሲል በተረጋገጠ የፌስቡክ አድራሻው ትናንት ምሽት ዐስታውቋል። ሆኖም ይህንን መግለጫ ከገጹ ላይ አንስቶታል። በዚሁ ክስተት ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩን የዲፕሎማሲ እና ዓለምአቀፍ ሕግ ተንታኞች የ1961ዱ እና 1971ዱን የቪዬና ኮንቬንሽን እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግና ሥርዓትን በማጣቀስ አብራርተዋል ።
የኤምባሲዎች ከለላ እና ጥበቃ እና አለም አቀፍ ሕጎች
በእርስ በርስ ግጭት የጦርነት ቀጣና በሆነችው የሱዳን ርእሠ ከተማ ካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መስከረም 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የከባድ መሳሪያ ጥቃት እንደተፈፀመበት ኤምባሲው ትናንት ምሽት በታወቀ የፌስቡክ ገጹ አረጋግጦ የጥቃቱን ፈጻሚ ለመለየት የሚደረገውን ምርመራ ውጤት በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር። ኤምባሲው "ድርጊት ሰብዓዊ ጉዳት ባያደርስም፣ ተግባሩ የአለም አቀፍ ሕግና የቪየናን ስምምነት የጣሰ" መሆኑን የጠቀሰበትን መግለጫውን ዛሬ አንስቶታል።
ኤምባሲው መግለጫውን ለምን እንዳነሳው ባይታወቅም ተጥሷል ያለው ሕግ ግን ተቀባይ ሀገራት በዲፕሎማሲያዊ ተልእኮዎች ግቢ ውስጥም ሆነ የእለት ተእለት ሥራቸው ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ ክልከላ የሚጥሉት የ1961ዱ እና የ1971ደ የቬየና ኮንቬሽኖችን ነው።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዲፕሎማሲ እና አለም አቀፍ ሕግ ተንታኝ በሱዳኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ተቀባይዋ ሀገር ወይም ሱዳን ለዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎች ጥበቃ የማድረግ የፀና ግዴታዋን መወጣት ያልቻለችበት ክስተት መሆኑን ገልፀዋል።
ኤምባሲው ካወጣው በኃላ ያጠፋው መግለጫ
በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አውጥቶት በነበረው መግለጫ "የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግሥት እና ሕዝብ ጋር ያለውን የቆየ ወዳጅነትና መልካም ጉርብትና ታሳቢ በማድረግ በካርቱም የሚገኘው ኤምባሲ ከገዳሪፍ ሆኖ ሥራውን እንዲያከናውን በማድረግ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማስቀጠል፣ እንዲሁም በሱዳን ያለው ችግር ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያደርገውንም ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል" ጠቅሶ ነበር። የዲፕሎማሲ ተንታኙ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ያልተለየው ሥራ ልትከውን ይገባል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋ እና የሥነ ምግባር መምህር የሆኑት ዶክተር ነጋ ሰለሞን እንዲህ ያሉ ጥቃቶች የዓለም አቀፍ ሥርዓት መላላት እና ሉዓላዊነት የሚባለው ጽንሰ ሀሳብ ኃይል ባላቸው ሀገራትና ቡድኖች እየተሸረሸረ የመምጣቱ ጉልህ ማሳያ ያደርጉታል።
የጥቃቱ ፈፃሚ ማን ይሆን ?
በሱዳን በቀጠለው ጦርነት በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ የተባለው ኃይል በትዊተር (ኤክስ) ባወጣው ጽሑፍ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የተሰነዘረው "ጥቃት" መሆኑን በመግለጽ ይህንን ያደረገእ በጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራውን የሱዳን መንግሥት የጦር ሠራዊት መሆኑን ጠቅሷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ክፉ ሌላ ወገን የተባለ ነገር የለም። በካርቱም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሩሲያ ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በደቡብ አፍሪካ እና በተባበረት አረብ ኤሚሬቶች ኤምባሲዎች ላይም ጥቃት መድረሱ ተነግሯል።
ለመሆኑ እንዲህ ያለው ጥቃት በኤምባሲዎች ላይ ለምን ይቃጣል? ያልናቸው ሀሳባቸውን ያጋሩን ሰው በኢራን አብዮት ወቅት አብዮተኞች በቴህራን የሚገኘውን የአሜሪካን ኤምባሲ እና የዲፕሎማሲ አባላትን በቁጥጥር ሥር ያደረጉበትን፣ ለንደን ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥሰው የገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከቅርብ አመታት በፊት ያደረጉትን ክስተት በማስታወስ ምክንያቶች የተለያየ ዓላማ እና ግብ ሊኖራቸው እንደሚችል ገልፀዋል።
ስለ ጉዳዩ የበለጠ ለማጣራት በሱዳን ለኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ እና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ