1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሱዳን ጦርነቱን ያቀጣጠሉት የውጭ ኃይሎች ጦርነቱን ማስቆም ይችሉ ይሆን?

ፀሀይ ጫኔ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 29 2018

የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ድጋፍ በውጭ ሀገራት ላይ የተመሰረተ ነው።በጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሀይል የሚደግፈው በግብፅ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ኢራን መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ።የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ይደገፋል። ለመሆኑ ሀገራቱ ከሱዳን ምን ይፈልጋሉ? ጦርነቱን ማስቆም ይችሉ ይሆን?

ሱዳን ፖርት ሱዳን
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከ140,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ባለሙያዎችና የእርዳታ ድርጅቶች ይገምታሉ።ምስል፦ AFP

በሱዳን ጦርነቱን ያቀጣጠሉት የውጭ ኃይሎች ጦርነቱን ማስቆም ይችሉ ይሆን?

This browser does not support the audio element.


የውጭ ሀይሎች ድጋፍ ባይኖር ሱዳን ውስጥ የትኛውም ተፋላሚ ሀይል ጦርነቱን ማራዘም አይችልም ነበር።በቅርቡ በዳርፉር ክልል ርዕሰ መዲና ኤል ፋሸር የተፈፀመውን የሰላማዊ ዜጎች የጅምላ ግድያ እና ሌሎችን ጨምሮ ሱዳን አስከፊ የሰብዓዊ አደጋ እና የጭካኔ ቦታ ሆናለች።  ጦርነቱ መጀመሪያ የተቀጣጠለው በጎርጎሪያኑ ሚያዝያ 2023 የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የተባለው የአካባቢ ሚሊሻ፣ ​​ወይም በእንግሊዥናው ምህፃሩ (RSF)ን፣ ከመደበኛው  የሱዳን ጦር ጋር ለመዋሃድ የተደረገ ሙከራ ባለመሳካቱ ነበር። 

በዳርፉር እየተካሄደ ባለው ጦርነት የሟቾች ቁጥር ግምታዊ ነው። የእርዳታ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ140,000 በላይ እንደሆነ ገልፀዋል። ከ51 ሚሊዮን የሱዳን ህዝብ ግማሽ ያህሉ በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የተመሰረተ ነው። ረሃብና በሽታ ተስፋፍቷል፣ አብዛኛው የአገሪቱ መሰረተ ልማቶችና የእርሻ መሬቶች ተጎድተዋል።በጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራው  እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የሱዳን መንግስት የሚደግፈው በግብፅ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ኢራን መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ። 

ግብፆች እና ሳዑዲዎች ሱዳንን በመሳሪያ  መደገፋቸውን ይክዳሉ። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ይደገፋል ተብሏል።ኢሚሬትስም  ይህንን ደጋግማ አስተባብላለች። ሀገር አሊ የተባሉ  የጀርመን የአለም አቀፍ እና አካባቢ ጥናት ተቋም (GIGA) ተመራማሪ ግን መደገፏን ያረጋግጣሉ።«የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች በጦርነቱ ወቅት በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ነዳጅ አቅራቢዎች ነበሩት። ነገር ግን ዋና አቅራቢው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ነው» ሲሉ ገልፀዋል።

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አወዛጋቢ አጀንዳ በሱዳን

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ  የሱዳንን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል አለመደገፏን ደጋግማ ገልፃለች። ውንጀላዎቹም የሱዳን ጦር  የመገናኛ ብዙሃን ዘመቻ ነው በማለት፤ ይቅርታ እንዲጠይቋት ስታሳስብ ቆይታለች።አቡ ዳቢ ያለፈው ሐሙስ  የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል  በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰውን ግፍ አውግዛ 100 ሚሊዮን ዶላር (86 ሚሊዮን ዩሮ) የሚገመት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደምትለግስ አስታውቃለች።
ሆኖም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ወታደራዊ አቅርቦትን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በተደጋጋሚ አግኝተዋል። ገለልተኛ ተንታኞች ታጣቂ ሀይሉ የሚጠቀማቸው የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች ከኢሚሬትስ የመጡ ናቸው ብለው ይደመድማሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ መረጃ ኤጀንሲ እና የስቴት ዲፓርትመንት የስለላ ቢሮ ምንጮች በዚህ ሳምንት ዎል ስትሪት ጆርናል ለተባለ የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጣ እንደተናገሩት ድጋፉ «በቻይና የተሰሩ የላቁ ድሮኖችን ከትናንሽ እና ከባድ መሳሪያዎችን ጋር፣ ተሽከርካሪዎች፣መድፍ ሞርታር እና ጥይትን ያካትታል።በተጨማሪም፣በጎርጎሪያኑ ጥር 2024 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከሊቢያዊው ጄኔራል ካሊፋ ሂፍታር ጋር የተቆራኙ ሚሊሻዎች ቀደም ሲል የነበሩ የኮንትሮባንድ ግንኙነቶችን በመጠቀም ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ነዳጅ፣ ተሽከርካሪዎች እና ጥይቶችን ያቀርባሉ።ሃገር አሊ እንደሚሉት የኢመሬትስ ድጋፍ ከሱዳን ወርቅ ጋር ይይዛዛል።«ኤመሬትስ  የጦር መሳሪያዎችን በቀጥታ በሊቢያ ድንበር በኩል ወደ ሱዳን፣ እንዲሁም በቻድ እና በኡጋንዳ በኩል እንደምታስገባ እናውቃለን። በምላሹም፣ ኤመሬትስ በባህላዊ መልኩ ትልቋ የሱዳን ወርቅ አስመጪ እንደመሆኗ መጠን የሱዳንን ወርቅ የማግኘት መብቷን ለማስጠበቅ የራሷ የሆነ ፍላጎት አላት።»ሲሉ ገልፀዋል።

ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች ፤ በዋናነት በተቆጣጠሩት ግዛት ውስጥ የሚገኙትን የሱዳን የበለፀገ የወርቅ ሀብቶች የጦር መሳሪያ ለመግዛት እና ማዕቀቦችን ለማምለጥ ቁልፍ የገንዘብ ምንጭ ሆኗቸዋል።ሀገር አሊ እንደሚሉት፤ በሱዳን ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎች ከጥቂት አቅራቢዎች ብቻ ሳይሆን ፤በመላው ሳህል ውስጥ ከሚዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎች ነው። አሊ አያይዘውም፣ የጦር መሳሪያ ማጓጓዝ ብዙውን ጊዜ የሚካሄደው ፣ የሩሲያ ዋግነር ግሩፕ የአፍሪካ ኮርፕስ ብሎ በሰየመው የአፍሪካ ክፍል ጭምር መሆኑን ገልፀዋል።

በጥር ወር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚመራው የአሜሪካ መንግስት በሁለቱም ወገኖች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። በወቅቱ የአሜሪካ የግምጃ ቤት መምሪያ በሰባት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የጦር መሳሪያ፣ የገንዘብ  እና ሌሎች ድጋፎችን ሰጥቷል ሲልም ሀገሪቱን ከሷል።

የተለያዩ አገሮች ለሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ድርንን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ይሰጣሉ።ምስል፦ Sudanese Ministry of Culture and Information/Xinhua/picture alliance

በሱዳን ውስጥ ያሉ ሌሎች ፍላጎቶች

ግብፅ የሱዳን ጦር SAF ቁልፍ ደጋፊ ስትሆን የቡርሃንን መንግስት ይፋዊ የሱዳን አስተዳደር አድርጋ ትቀበላለች። ገለልተኛ የጦርነት ተቋም ባወጣው አጠቃላይ እይታ መሠረት ግብፅ የ የሱዳን ጦር  አብራሪዎችን አሰልጥናለች ድሮኖችንም አቅርባለች። ካይሮ ግን አስተባብላለች።ግብፅ ፤ግጭቱን በሱዳን ድንበር ላይ ለማቆየት ትጥራለች። በመጨረሻም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሱዳን ስደተኞችን ለመመለስ ተስፋ ታደርጋለች።ሌላዋ የሱዳን ጦር  ደጋፊ ኢራን ስትሆን ፤ድሮኖችንም አቅርባለች። ቴህራን በየመን የሁቲ ሚሊሻዎችን ለመደገፍ የሚረዳውን የቀይ ባህር  የባህር ኃይል ለማስጠበቅ ተስፋ ታደርጋለች። ሱዳን የሁቲ አማፂያን የሎጂስቲክስ ማዕከል ሆና ታውቃለች።

ቱርክ ለሱዳን ጦር ሀይል ድሮኖችና ሚሳኤሎችን ሰጥታለች። የአንካራ ፍላጎት ደግሞ ወደ ቀይ ባህር የሚያደርሰውን መዳረሻ ደህንነት ማረጋገጥ ነው።የሱዳን ጦር ሀይል ስም በሩሲያ የሚደገፈው የአፍሪካ ኮርፕስ ተሳትፎ ቢኖርም፣ ሩሲያ በሱዳን ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ሚና ትጫወታለች ይላሉ፤ በጀርመን ፍሪድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን የዩጋንዳ እና የሱዳን ዳይሬክተር አቺም ቮግት።«በወርቅ የውጭ ንግድ እና በፖርት ሱዳን ወደብ ረገድ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አላቸው፣ ነገር ግን ውስጣዊ ግጭት ብለው በሚጠሩት ነገር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በአንጻራዊ ሁኔታ ግልጽ አድርገዋል።»ብለዋል።

በኤል-ፋሸር በተፈፀመው ጭካኔ እና የጅምላ ግድያ ምክንያት፣ የRSF አባላት አቡ ሉሉ የተባለ ተዋጊ (በስተግራ) በቁጥጥር ስር አውለዋል ተብሏል።ምስል፦ Rapid Support Forces (RSF)/AFP

 ኳድ፤ ሰላም ለማስፈን ሊያግዝ ይችላልን?

በቮግት አመለካከት፣ ‹ኳድ ተነሳሽነት› እየተባለ የሚጠራውን አራቱ አገሮች ማለትም ዩኤስ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ - ከሁለቱም ወገኖች ጋር የተለያዩ ቁርኝት ቢኖራቸውም በሱዳን ላይ እውነተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ መንግሥታት ይሆናሉ። የእንቅስቃሴው አላማ ጦርነቱን ለማስቆም ወይም ቢያንስ ሰብአዊ እርቅ ለማውረድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ነበር።

ቮግት እንዳሉት እነዚህ ሀገራት ከተሰባሰቡ እና ምናልባትም በአውሮፓ ሀገራት ድጋፍ ካገኙ ወደ አለም አቀፉ የሰብአዊ ህግጋት መመለስ ይችላሉ። ፣የሰብአዊ መብት ረገጣ ማቆም እና የስቪክ ማኅበረሰብ  ሰብዓዊ ሁኔታን ማሻሻል ይችላሉ።ገር ግን፣ በዚህ አመት ጥቅምት 26፣በዋሽንግተን የተካሄደው ፤ ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ንግግር ለማምጣት እና ለሶስት ወራት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ታስቦ የነበረው የኳድ ውይይት ያለ ውጤት ተጠናቋል። በዚያው ቀን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ኤል ፋሸርን ተቆጣጥሮ የጅምላ ግድያ እና ሌሎች አሰቃቂ ድርጊቶችን እንዲባባሱ አድርጓል።

በሱዳን ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋልምስል፦ Mohammed Jammal/UNICEF/AP Photo/picture alliance

በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር፣ በኤል ፋሸር እና አካባቢው እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰት መጠን እና ክብደት አሁን “የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ አመራር እና ደጋፊዎቻቸው በተለይም የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ድጋፍ በመስጠታቸውን የቀጠሉ መዘዞች ናቸው።እነዚህ ወንጀሎች ግልጽ ማስረጃ ቢቀርብባቸውም ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋልም ሲሉ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።እናም ተጠያቂነት እንዲኖር ጥሪ ያደርጋሉ።
«የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በአስቸኳይ በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል  እንፈልጋለን።የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የፖለቲካ እና የወንጀል ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ጥሪ እናደርጋለን።»ብለዋል።

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW