በሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ሞቱ - የዐይን እማኞች
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2015
በሱዳን በቀጠለው ጦርነት የተነሳ ዋና ከተማ ካርቱም አንድ ግቢ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ «አራት ወይም አምስት» ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተገለጠ ። ኢትዮጵያውያኑ ከሱዳን ተፋላሚ ኃይላት በተተኮሱ ከባድ ጦር መሣሪያዎች ፍንጣሪ መገደላቸውን በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ። አራተኛ ቀኑን በያዘው የሱዳን ጦርነት እስካሁን 200 ግድም ሰዎች ሲገደሉ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል ። በሱዳን የጦር መሪዎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ዛሬም በከባድ መሣሪያ ታግዞ መቀጠሉንም የዐይን እማኞች ከስፍራው ገልፀዋል ።
ከፍተኛ ጉዳትና ውድመት እያደረሰ መሆኑ እየተነገረለት ባለው የሱዳን የጦር አበጋዞች በሚፋለሙበት ጦርነት ሱዳን ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም የሞት ጉዳት ሰለባ መሆናቸውን ካርቱም የሚኖሩ የዐይን እማኞች አረጋግጠዋል።
"የተጎዱ አሉ። አራት ነው አለኝ አንደኛው። አንደኛው አምስት ነው አለኝ። አንድ ቦታ በነበሩበት ነው ከባድ መሣሪያ ነው የመታቸው ነው ያለኝ"። በማለት የጠይቅናቸው እማኝ ገልፀዋል። ሌላኛዋ የዐይን እማኝ ደግሞ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ሲያስረዱ፦ «ጎረቤት ነው የነገረን ደውሎ። ቦንብ ገብታባቸው አራት ሞቱ አለ። ወደዚህ ወደ አርኮይት የሚባል ሰፈር አለ። ይሄው ፌስቡክም እየለቀቋቸው ነው ልጆቹን። ሁለት ባልና ሚስት ሞተዋል አሉ። የተጎዳ ልጅም አለ። ቀብርም እየቀበሩ ነው» ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በአንድ ግቢ ውስጥ እንደሚኖሩ የገለፁ ኤልሳ የተባሉ የሁለት ልጆች እናት ኢትዮጵያዊት የካርቱም ከተማ ነዋሪ ጦርነቱ የተጀመረበት እለት የመሣሪያ ፍንጣሪ የቤታቸውን መስኮት መምታቱን ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
«እዚ አንድ ግቢ ያለን ፣ ኤርትራውያን አሉ ኢትዮጵያውያን አሉ። አንድ አሥር አለን እዚህ ግቢ ውስጥ። ሕፃናት ሁለት ልጆች አሉኝ። ተኩሱ በላያችን ላይ አለ። ልጆቹ ፈርተው እስካሁን ምግብ አይበሉም። መብራት ራሱ አራት ቀናችን ነው ዛሬ። እኛ መስኮታችን ጋር ፍንጣሪ ገብቶ መስኮቱን ቀዶ እግዚአብሔር ይመስገን ማንንም ሰው አልነካም። ፍንጣሪዋ ራሱ አለች» በማለት የሚገኙበትን በፍርሃት የተሞላ አስጊ ሁኔታ አስረድተዋል።
ሱዳን ውስጥ በሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩም የጠበቀ መሆኑን ሌላኛው ያነጋገርነው ኢትዮጵያዊ አስረድቷል። «አዲስ ነኝ የመጣሁት። ስድስት ወር ሰባት ወር ነው የሚሆነኝ ወደ ሱዳን ከገባሁ። ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው እዚህ ያሉት። በሚሊየን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ነው ያለው። አርባ ዓመት ፣ አምሳ ዓመት የኖረም አለ። በተለያየ ምክንያት መጥቶ ንብረት አፍርቶ የሚኖር አለ። በሕጋዊ መንገድ መጥቶ የሚኖር አለ ፣ በሕገወጥም መንገድ ጥገኝነትም ሳይጠይቅ የሚሠራ አለ። ከዚያም ባሻገር ሱዳን ትልቅ ትስስር ነው ያለው ከኢትዮጵያ ጋር» ብለዋል።
ሌላኛው የዐይን እማኝ «በጣም አስከፊ እና አስፈሪ» ሲሉ የገለፁት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሱዳኑ ጦርነትበዚያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ስላደረሰው ጉዳት፣ እየተደረገ ያለ ድጋፍ ካለ ለማጠየቅ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም የእጅ ስልኮች ላይ ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ አይሰጡ።
በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሁለት ቀናት በፊት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ብሎ ባሰራጨው ጥሪ «ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የሱዳ ግዛቶች ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም ከሚችል አደጋ እራስን መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ ከግጭት አካባቢዎች በመራቅና ከእንቅስቃሴ በመቆጠብ እራሳችሁን ከአደጋ እንድትጠብቁ እናሳስባለን» ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
የጦርነቱ ዋነኛ ተፋላሚ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ የሆኑት ጀነራል መሀመድ ሐምዳን ዳጋሎ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ከተወያዩ በኋላ የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን ዛሬ በትዊተር አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ አስቸኳይ ጉባኤ ያደረገው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (IGAD) ወደ ካርቱም ሊልካቸው የነበሩት የሦስት ጎረቤት አገራት ፕሬዝዳንቶች ማለትም የጅቡቲ ፣ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ጦርነቱ አይሎ መቀጠሉን ተከትሎ ለጊዜው ከጉዟቸው መታቀባቸው ተነግሯል ።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ