1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሱዳን ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ 3 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

ሐሙስ፣ ግንቦት 10 2015

በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ራምሽ ራጃሲንግሃም እንዳሉት ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ከሱዳን ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው እርዳታ እና ጥበቃ ያስፈልገዋል።ድርጅቱ ሰሞኑን እንዳስታወቀው በሱዳን ለአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ የሚውል 3 ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር ያስፈልጋል።

Sudan Situation Konflikt
ምስል፦ JOK SOLOMUN/REUTERS

የተባባሰው የሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ

This browser does not support the audio element.


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  እንዳስታወቀው በሱዳን በተከሰተው ግጭት ለችግር ለተጋለጡ  ሰዎች አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚውል  3 ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር /€ 2.7 ቢሊዮን/ ያስፈልጋል።

በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ራምሽ ራጃሲንግሃም እንዳሉት ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ከሱዳን ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው እርዳታ እና ጥበቃ ያስፈልገዋል ።ይህም በሀገሪቷ እስካሁን ከታየው ከፍተኛው ቁጥር  መሆኑን ሀላፊው አመልክተዋል። 

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት በጋራ ባወጣው መግለጫ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሱዳናውያን ስደተኞች ተጨማሪ 470 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ ገልጿል።ይህም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ዩጅን ባያን እንደሚሉት የሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ለጎረቤት ሀገራትም ተርፏል። 
«ወደ ጎረቤት ሀገር ስትመለከት ድንበር አቋርጠው የሄዱ ስደተኞችን እያስተገዱ ነው።አሁን፣ኢትዮጵያ፣ደቡብ ሱዳን፣ቻድ እና ግብፅ እጅግ በጣም ብዙ ስደተኞችን እያስተናገዱ ነው። ነገር ግን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የውስጥ ችግር አለባቸው። አስበው፤የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችን እና  አስተናጋጅ ሀገራት በአሁኑ ስዓት እያስተናገዱት ያለውን  የሰብዓዊ ቀውስ መጠን።»

ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP

የተባበሩት መንግስታት ከጥቂት ወራት በፊት በሱዳን ለሰብዓዊ እርዳታ 1.75 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተንብዮ የነበረ ሲሆን፤ በጎርጎሪያኑ  ሚያዝያ 15 ቀን 2023 ዓ/ም በሱዳን ደም አፋሳሽ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ድርጅቱ በወጣው እቅድ ግን በሀገሪቱ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች እርዳታ የሚሆን 2.56 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጿል።በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ 3 ቢሊዮን ማሻቀቡን አመልክቷል።ይህ የድጋፍ ፍላጎት  የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ራምሽ ራጃሲንግሃም  እንዳሉት፣ ለሱዳን ከምንጊዜውም ጊዜ በላይ ከፍተኛው የሰብአዊ ድጋፍ ጥያቄ  ነው።
በሱዳን በጦርነቱ የሚጎዱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው በሱዳን እየተካሄደ ባለው ግጭት የሟቾች ቁጥር ወደ 604 የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር  ደግሞ ከ5,000 በላይ ደርሷል።
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ አንድ ወር በተጠጋው ጦርነት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 700,000 ከፍ ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው ይህ አሃዝ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት ቀደም ሲል ተፈናቅለው ከነበሩት 3.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ውጭ ነው።
በግጭቱ በርካቶች ወደ ጎረቤት ሀገራት እየተሰደዱ ሲሆን፤ በቻድ ብቻ 400,000 ሱዳናውያንን ስደተኞች ገብተዋል።በዚህ የተነሳ የእርዳታ ድርጅቶችም ፈተና እያጋጠማቸው መሆኑን ዩጅን ባዩን አስረድተዋል።
 «መሬት ላይ መዋቅር እና ስርዓት አለን ።ነገር ግን  ከመጠን በላይ የተለጠጠ ነው።ጫና ውስጥ ነው። የገንዘብ ድጋፍ እጥረት አለ። ይህም ቀደም ሲል በመሬት ላይ ባለው የሰብዓዊ ምላሽ ላይ ተጽዕኖ አለው። ስለዚህ አዲስ ለሚመጡት ብዙ ድጋፍ እንፈልጋለን። ከመንግስት እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበለጠ ድጋፍ እና ተሳትፎ እንፈልጋለን።»

ምስል፦ AFP

ድንበር አቋርጠው  ከሚሄዱት ስደተኞች መካከል በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናት ህጻናት መሆናቸውን ያስረዳሉ።ለዚህም የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል ብለዋል።

ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP

«በአሁኑ ወቅት ከምንስተናግዳቸው ስደተኞች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ሴቶች እና ህፃናት ናቸው።በጣም ለችግር የተጋለጡ ሴቶች እና ልጆች ናቸው።ብዙ ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆች አይተናል።ብቻቸቸውን ሶስት እና አራት ልጆቻቸውን የሚንከባበከቡ እና 24 ስዓት የሚደክሙ እናቶች አሉ። ወደ  ድንበር አካባቢ የመጡት ያለ መጠለያ፣ ያለ ልብስ፣ ያለ ምግብ እና ውሃ ነው። የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል። መጠለያ ያስፈልጋቸዋል። ምግብ እና ውሃም የሚያስፈልጋቸዋል።»

ሱዳን ከጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 15 ቀን 2023 ዓ/ም  ጀምሮ በግጭት ስትናጥ የቆየች ሲሆን ፤ ግጭቱ በአብዱል ፈታህ አልቡርሀን ታማኝ በሆነው የሱዳን ጦር ሃይል እና  በተቀናቃኛቸው መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል ነው። 
በጎርጎሪያኑ ታህሳስ 2022 ወታደራዊ ኃይሎች እና የሲቪል ተወካዮች የመሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን ፈጥኖ ደራሽ ጦር  በሱዳን ጦር  ውስጥ ለማስገባት የሽግግር ስምምነት ተፈራርመዋል።ያም ሆኖ ከ100,000 በላይ ጦር እንዳላቸው የሚነገርላቸው ዳጋሎ ፣ እንዲህ ዓይነቱን መልሶ ማዋቀር አልወደዱትም። ይህም ሁለቱን ወገኖች ወደ ቅስቀሳ እና ውንጀላ ከዚያም ወደ ግጭት እንዲያመሩ አድርጓል። 

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW