1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጃራ ስደተኞች መጠለያ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት

ዓርብ፣ ኅዳር 27 2017

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ወሲባዊ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ ተገለፀ። በባለፉት ሁለት ወራት 12 ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን ጥቃቱ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ባለፉት ሁለት ወራት 12 ወሲባዊ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተመዘግቧል። ፎቶ ከማኅደር፤ ምስል Alamata City Youth League

በጃራ ስደተኞች መጠለያ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት

This browser does not support the audio element.

 

 

ለኑሮ እጂግ አስቸጋሪ እንደሆነ የሚነገርለት የጃራ የስደተኞች መጠለያ የመኖሪያ ቦታ ያልተመቻቸለትና ሰብአዊ ድጋፍ በወቅቱ ለስደተኞች የማይደርስበት እንደሆነ ስደተኞቹ ይናገራሉ። በስደተኞች ማዕከሉ ውስጥም ከባለፈዉ መስከረም ወር በኋላ በታጠቁና ማንነታቸዉ በማይታወቁ ሰዎች እየተፈፀመ ያለዉ ፆታዊ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን በማዕከሉ የሴቶች ተወካይ የሆኑት ወይዘሮ ማሬ አለነ ይናገራሉ። ጥቃቱ ዕድሜንና የጤና ሁኔታን ያለየ ነው የሚሉት ወይዘሮ ማሬ ሴቶች ለሞት ጭምር ተጋልጠውበታል ይላሉ።

ለደህንነታቸዉ ሲባል ስማቸዉ ያልተገለፀ የጥቃቱ ሰለባ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ጥቃት ፈፃሚዎቹ ፊታቸዉን በጭንብል የሸፈኑና የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው። በጃራ የስደተኞች ጣቢያ ጥቃት የተፈፀመባቸዉ ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ዳግም ላለመጠቃታቸዉ ዋስትና እንደሌላቸውና በጭንቀት ውስጥ እንዳሉም ያስረዳሉ።

 መጠለያ ጣቢያዉ አጥር የሌለዉና ደህንነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ ከዚህ ቀደም ማንነታቸዉ ባልታወቀ ታጣቂዎች ሰባት ሰዎች መገደላቸዉን አቶ ፀዳሉ አበራ የስደተኞቹ ተወካይ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኘው ጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች መበራከታቸው ተገልጿል።ፎቶ ከማኅደር፤ ጃራ የስደተኞች መጠለያ ምስል Alamata City Youth League

የሰሜን ወሎ ዞን ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ምን ይላል?

በዞኑ እየተፈፀመ ያለዉ ፆታዊ ጥቃት የጨመረ መሆኑን ገልፆ ህግ የማስከበርና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ተግባሩ ግን አሁን በአካባቢዉ ካለዉ ጦርነት ጋር ተያይዞ አስቸጋሪ መሆኑን ወይዘሮ እመቤት ደሳለ የሰሜን ወሎ ዞን ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ይገልጻሉ።

በጃራ መጠለያ ጣቢያ ያሉ ሴቶች ምግብ ለማብሰል እንጨት ለቀማ በአካባቢዉ ወዳለ ጫካ በሚንቀሳቀሱበት ወቅትም ጥቃት የሚፈፀምባቸው ሲሆን እስካሁን ጥበቃ የሚያደርግላቸዉ አካልም አላገኙም።

እየተፈፀመ ያለዉን የሴቶች ጥቃት ለማስቆም ከፍተኛ የሕግ ክፍተት ስለመኖሩ

በየጊዜዉ እየተፈፀመ ያለውን የሴቶች ጥቃት ለማስቆም ከፍተኛ የሕግ ክፍተት መኖሩን የሚናገሩት የሰሜን ወሎ ዞንሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ደሳለ አጥፊዎች በዋስ እየተለቀቁ ከሀገር የሚወጡበት ሂደት መኖሩን ይናገራሉ።

የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ በጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሴቶች ላይ እየተፈፀመ ስላለዉ ወሲባዊ ጥቃት የማውቀው ነገር የለም ነው ያለው።

በቢሮዉ የሴቶች ንቅናቄ ግንዛቤ ማደራጃ ዳይሬክተር ወይዘሮ ደስታ ፈንታዉ እንደገለፁት የጃራ መጠለያ ጣቢያ በርካታ ለሴቶች ያልተሟሉ ግብአቶች እንዳሉ ብናዉቅም ስለተፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ግን የደረሰን መረጃ የለም ይላሉ።

ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW