የአውሮጳ ህብረት የአገር ውስጥ ሚኒስትሮች ስብሰባ
ዓርብ፣ መጋቢት 1 2015
የአውሮጳ ህብረት የአገር ውስጥ ሚኒስትሮች እስከዛሬ ድረስ በዘለቀው የሁለት ቀን ስብሰባቸው እንደተለመደው የስደተኖች እና ፈላስያን አጀንዳ ላይ ትኩረት ሰተው በመወያየት ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።
የስደተኖች ጫና፣ ስደተኖች በሚገቡባቸው የደቡብና ምስራቅ አውሮጳ አገሮች ማየሉና፤ አንዳንዶቹ አባል መንግስታት ለስደተኖች ድንጋጌዎችና አለማቀፍ ህጎች ታማኝ አለመሆን ችግሩን ውስብስብ፤ ልዩነቱንም ሰፊ አድርጎታል። ህብረቱ በስደተኞች ጉዳይ ወጥ አሰራር እንዲከተል የጋራ የስደተኖች ፖሊሲ የሚያስፈልግ መሆኑ ቢታመንበትም፤ በችግሩ ውስብስብነትና በአባል መንግስታቱ ፍላጎት ልዩነት ምክንያት እስከአሁን እውን ሊሆን እንዳልቻለ ነው የሚታወቀው።
በአሁኑ ወቅት ግን የደንበርን ቁጥጥር ጥብቅ በማድረግና ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙትን ስደተኖች አስገድዶ መመለስ በሚቻልበት፤ እንዲሁም አባል አገሮች ወጥ የሆነ የስደተኞች የአቀባበልና የመስተንግዶ ስርዓት እንዲኖራቸው የሚያስችል የጋራ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ላይ እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን፤ የወቅቱን የህብረቱን ፕሬዝዳንሲ የያዘቸው ሲዊድን በዚህ አጀንዳ ላይ ትኩረት ሰታ እየሰራች እንደሆነ ተገልጿል። ስብሰባውን በጋራ የመሩት የስዊድን የስደተኖችና የፍትህ ሚኒስትሮች ከኮሚሽኑ የአገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ወይዘሮ ይልቫ ዮሃንሶን ጋር ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፤ የስዊድን የስደተኖች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ማሪያ ማልሜር ስቴኔግራድ በመግለጫቸው፤ የፈላስያንና ስደተኞች ጉዳይ የአውሮጳ የጋራ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለችግሩ የጋራና አውሮጳዊ መፍትሄ ለመፍለግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። “ በውጭ በኩል ትኩረት የተደረገው አባል አገሮች ከሶሥተኛ አገሮች ጋር የሚኖራቸው የፖለቲካና የኤኮኖሚ ግንኙነት ችግሩን ለመቅረፍና በተለይም ተመላሽ ስደተኞችን እንዲቀበሉ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሆን በመስራት አንድ ቁንቋ መናገር የሚያስፈልግ መሆኑንና በዚህ በኩል ሁሉንም አይነት ዘዴ፣ የማግባቢያና መሳመኛ ስልቶችን መጠቀም የሚያስፈልግ መሆኑን ሚኒስትሮቹ አምነውበታል” ብለዋል።
ሚኒስትሯ ስብሰባው የተሳካና ተስፋ ሰጭ የነበር መሆኑንም፤ “ ውይይቱ በጣም ገንቢ ነው የነበረው። በፈላስያንና ስደተኖች ጉዳይ በጋር መስራት የሚያስፈልግ ስለመሆኑ በአባል አገሮች መካከል መግባባት አለ” በማለት ከውጭ ጋር ያለውን ግንኑነት ማጠናከርና በውስጥም የህግ ማዕቀፍ ዝግጅቱን ማሳለጥ እንደሚገባ የታመንበት መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስትሮቹ በህብረቱና በተለይም አብዛኞቹ አባል በሆኑበት የሸንገን ቪዛ ስርዓት ላይ በመወያየትም አላግባብ ቪዛ የሚሰጡትንም ሆነ የመግቢያ ቪዛውን ለሌላ ህገወጥ ተግባር የሚያውሉትን ለመቆጣጠር የሚይስችል ስልት እንዲዘጋጅ ውሳኔ የተላለፈ መሆኑም ተገልጿል።
የአውሮጳ ህብረት ግን ስደተኖችና ፈላሳያን ወደ ኅብረቱ እንዳይገቡ ደንበር ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር ኢሰብዓዊና ህገወጥ እንደሆነ ነው በብዙዎች ዘንድ የሚነገረው። በአስቸጋሪ ሁኔታና በባህር ጭምር ውደ ህብረቱ የባህር ዳርቻ የሚደርሱትን ሳይቀር ማረፊያ የሚከለክሉ መሆኑን የሰብዊ መብትና የስደተኖች ድርጅቶች ይናገራሉ።
ይህ በዚህ እንዳለ ከጥቂት ቀናት በፊት ብርታኒያ ይፋ ያደረገችው የስደተኖች ህግ ከሁሉም በላይ የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው። አዲሱ የብራታኒይ የስደተኖች ህግ በተለይ በጀልባና በሌላ እነሱ ህገወጥ በሚሉት ዘዴ ወደ ብርታኒያ መግባት በራሱ ወንጀልና የሚያሳስር ብሎም ያለምንም ጥያቄ ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር የሚያስጠርዝ ነው ተብሏል።
ይሁንና የአውሮጳ ኅብረትም ሆነ ብሪታኒያ በስደተኞች ላይ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ኢ-ሰብዓዊና የአለም አቀፍ ህግን የሚጥሱ መሆናቸውን ነው በርካታ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚያስረዱትና የሚከራከሩት። ስደት ዋና ምክንያቶች ድህነት፤ ጦርነትና ጭቆና መሆናቸው የታወቀ ሆኖ ሳለ፤ በነዚህ ችግሮች ላይ በመስራት ችግሩን ለዘለቄታ ለማቃለል ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን ነው እነዚሁ የሰብዓዊ መብት ተክራካሪዎች የሚናገሩት። በቅርቡ በዶሀ ካታር ላይ የተደረገው ያዳጊ አገሮች ጉባኤ ላይ በመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽሀፊ ሚስተር ጉቴሬሽ ሳይቀር የተነገረውም፤ የበለጸጉ አገሮች የፋይናንሥ ስርዓትና የኤኮኖሚ ግንኑነት ድሆቹን አገሮች የበለጠ ድሀ የሚያደርግ ብሎም ህዝቦቻቸውን ለስደትና ችግር የሚዳርግ መሆኑን ያስረገጠ እንደነበር አይዘነጋም።
ገበያውንጉሴ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ