1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሊያ ድርቅ ሕይወት እየቀጠፈ ነው፤ ሱዳን ውስጥ ደግሞ ተቃውሞው ቀጥሏል

ቅዳሜ፣ ኅዳር 17 2015

ሶማሊያ ውስጥ ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት የበርካቶችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል። ሱዳን ውስጥ ደግሞ ባለፉት ሳምንታት ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።

Somalia Mogadishu | Dürre und Hungersnot
ምስል Mariel Müller/DW

ትኩረት በአፍሪቃ

This browser does not support the audio element.

 

ሶማሊያ ውስጥ ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት የበርካቶችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል። በዋና ከተማ መቃዲሾ በሚገኘው ባንዳሪ ሆስፒታል ውስጥ የጽኑ ሕሙማን ክፍል የታማሚዎችን ሕይወት ለማሰንበት የተተከሉት የኦክስጅን ማሽኖች ንዝረት እንዲሁም የአስታማሚዎች ሹክሹክታ ይሰማል። የፀሐይ ብርሃንን ለመከላከል መስኮቶች ተጋርደዋል። በከፋ የምግብ እጥረት የተጎዱ ልጆች የሚላኩት ወደዚህ ሆስፒታል ነው። ብዙዎቹ ሕጻናት ወደዚህ እየመጡ ሳለ መንገድ ላይ እንደሞሞቱ ዶክተሮች ይናገራሉ። በሕይወት ለመትረፍ የምትታገለው የአራት ዓመቷ አሚና አብዲ አቅሏን በመሳቷ እራሷን አታውቅም። የሕጻናት ሀኪም የሆኑት ዶክተር አውይስ ኦሎው ሀሰን የሆስፒታሉ የሕጻናት ክፍል ኃላፊ ናቸው።

«አሚና አብዲ ሰባት ኪሎ ነች፤ በጤናዋ ቢሆን 16 ሊሎ መመዘን ነበረባት። ሊኖራት ከሚገባው ኪሎ 50 በመቶውን አጥታለች። እነዚህ በድርቅ የተጎዱ ሰዎች ናቸው፤ በከፋ የምግብ እጥረት ምክንያት ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ ሆና ነው ወደዚህ የመጣችው። እራሷን ስታለች።»

ዶክተር ሀሰን እንደሚናገሩት በርሀብ የተጎዳች እናት ልጇን ብታጠባም ወተት ልትሰጠው እንኳን አትችልም። እሳቸው እንደሚሉትም የጨቅላውን በርሃብ መጎዳት ከተዳከመ በኋላ ነው ወላጆች የሚያውቁለት። ይኽም የብዙዎቹን ሕይወት ይቀጥፋል። የአሚና እናት እና አክስት ካለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ ሦስት ልጆቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል።  የተመድ እንደሚለው ሶማሊያ ውስጥ በየቀኑ  በየደቂቃው በአማካኝ በምግብ እጥረት የተጎዳ አንድ ልጅ ሀኪም ቤት ይገባል። ሶማሊያ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባት ነው። ለአምስት ተከታታይ ጊዜ የዝናብ ወቅቱ ይስተጓጎላል የሚል ፍርሃት አሁንም አለ። ከሰባት ሚሊየን በላይ ሕዝብ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው። የአሚና ቤተሰቦች አርብቶ አደሮች ነበሩ።

«እርሻዎች እና ከብቶች ነበሩን። ሆኖም በድርቁ ምክንያት ሁሉንም አጣን። ለሦስት ዓመታት በድርቅ ውስጥ ነን። ድርቁ ሲከፋም አካባቢያችንን ትተን ወደከተማ መጣን።»

የሚሉት የአሚና አክስት አርዳ መሀመድ ኡስማን ናቸው። ድርቁ ብቻም አይደለም የሶማሊያ አርብቶ አደሮችን ለችግር የዳረገው። አሚና በተኛችበት ሀኪም ቤት ሌላ አንድ አባትም የሁለት ወር ጨቅላ ልጁን ሩቂዮን ይዞ ተቀምጧል። ስሙ እንዳይጠየቀስ የጠየቀው ይህ አባት ማዕከላዊ ጉልዱግ ግዛት ውስጥ በግብርና ኑሮውን ይገፋ ነበር። ሆኖም የአሸባብ ታጣቂዎች መሬቱን ስለነጠቁት ለመሰደድ ተገደደ።

የሕጻናት ሀኪም የሆኑት ዶክተር አውይስ ኦሎው ሀሰን የሆስፒታሉ የሕጻናት ክፍል ኃላፊ ምስል Mariel Müller/DW

«ሰዎች በጣም ያስቸግራሉ። ከብቶቻችን ወስደው ሲያበቁ ከእነሱ ጋር እንድንሰለፍ ይጠይቁናል። እንዲህ ያለ ችግርን ተጋፍጠናል። ከእነሱ ጎን ሆነን እንድንዋጋ ይነግሩናል። በሌላ በኩል ከብቶቻችን አልቀዋል፤ ይህም ሌላው ችግር ነው።»

ከአልቃይዳ ጋር ትስስር እንዳለው የሚነገርለት ይኽ ቡድን በሶማሊያ ገጠር ሰፋ ያለ ስፍራን ተቆጣጥሯል። የሩቅያ አባት እንደተናገሩት አካባቢያቸውን ለ13 ዓመታት በዚህ ቡድን ሥር ነው። ከዘመዶቻቸው እንደተረዱትም ድርቁ እየከፋ ሲሄድም ችግሩ እየተባባሰ ሰዎችም ለረሃብ እና ለውኃ እጥረት ተጋልጠዋል። እንዲህ ባለው ስፍራ ደግሞ እርዳታ እንደሌለ፤ መንግሥትም ወደዚያ እንደማይሄድ፤ ታጣቂው ቡድንም ማንንም እንደማይረዳም ተናግረዋል። ቤይ በሚባለው ግዛትም በድርቅ እና ግጭት ምክንያት 1,6 ሚሊየን ሶማሊያውያን በቅርቡ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው አቅራቢያቸው ወደሚገኘው ባይደዋ ተሰደዋል። የባይደዋ ከተማ ከንቲባ አብዱለሂ አሊ ዋቲን እንደሚሉት ለመጠለያነት የተዘጋጀው ስፍራ እስከ መጪዎቹ ሁለት ወራት ድረስ አንድ ሚሊየን ሕዝብ ሊያስጠጋ ይችላል። ሀዎ አይዛክ ሞአሊም ከአምስት ልጆቻቸው ጋር በዚህ ስፍራ በድንኳን ውስጥ ተጠልለዋል። የ50 ዓመቷ ወይዘሮ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱት ግመሎታቸው በውኃ ጥም በማለቃቸው ነው።

ድርቅ ያፈናቀላቸው በርካቶች የተጠለሉበት ስፍራ ባይደዋምስል Mariel Müller/DW

«በርሀብ ምክንያት ወደዚህ መጠለያ ከመጣን ቆየን፤ ሆኖም እስካሁን ምንም ያገኘነው እርዳታ የለም። አልፎ አልፎ ነው ምግብ ወይም ውኃ የሚሰጠን። እዚህም በእውነቱ እየታገልን ነው። »

ከጥቅት ሳምንታት በፊት ሀሰን አይዛክ የተባለው ልጃቸው በትክትክ ተያዘ፤ ወደላይ ወደታች ይለው ጀመር። በመጠለያው ስፍራ የተሰጠው ኪኒንም አልረዳውም እናም አረፈ።

«የሞተው በድርቁ ምክንያት ነው። ከተቀበረ አሁን 15 ቀን ሆነው። ስምንት ዓመቱ ነበር።»

እናም እኝህ እናት ለሞተው ልጃቸው ብዙ የሚያዝኑበት ፋታ አላገኙም ሌሎቹን ልጆቻቸውን ሞት እንዳይነጥቃቸው ዓይናቸውን በእነሱ ላይ አድርገው ለማትረፍ ይጥራሉ። የተመ የሕጻናት መርጃ UNICEF ባለፈው ጥር ወር አንስቶ እስካሁን ሶማሊያ ውስጥ 964 ልጆች ሕይወት መቀጠፉን አመልክቷል። ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከተከሰተው ይኽ ቁጥር እጥፍ እንደሚሆንም ነው የገለጸው። 

«በከፋ የምግብ እጥረት የተጎዱ ግማሽ ሚሊየን ሕጻናት አሉ፤ እነዚህ ተገቢውን እርዳታ በሰዓቱ የማያገኙ ከሆነም በቀላሉ ይሞታሉ።»

ይላሉ በሶማሊያ የUNICEF ተጠሪ ዋፋ ሰኢድ። የተመድ ሶማሊያ ውስጥ ሰብአዊ እልቂት እዳይደርስ ለእርዳታ ያስፈልገኛል ሲል ከጠየቀው 1 ቢሊየን ዶላር ያገኘው ግማሹን ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል። ምንም እንኳን አንዳንድ የረድኤት ሠራተኞች የረሀብ ይዞታው መክፋቱን ቢናገሩም የሶማሊያ መንግሥት ግን ሀገሪቱ አስከፊ ረሀብ ውስጥ መሆኗን አላወጀም። እንዲህ ያለው መግለጫ ወደ ሀገሪቱ እርዳታ እንዲጎርፍ በማድረግ የሰዎችን ሕይወት ሊያተርፍ እንደሚችልም የሚናገሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ። በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ,ም 260 ሺህ ህዝብ በረሀብ ምክንያት ሶማሊያ ውስጥ ያለቀው የከፋ ረሀብ መከሰቱ በይፋ ከመነገሩ በፊት መሆኑንም ያስታውሳሉ። ሆኖም ግን የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሀሙድ በቅርቡ፤ ምንም እንኳን እርዳታ ወደ ሶማሊያ ቢጎርፍም ለተቸገሩት እንዳይደርስ አሸባብ ያደናቅፋል ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል። በተጠቀሰው ዓመትም አብዛኛው የባይደዋ አካባቢ በአሸባብ ቁጥጥር ስር ነበር። አሁንም ተመሳሳይ እልቂት እንዳይከሰት የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት የሚችሉትን ለማድረግ ጥረታቸው ማጠናከራቸውን የUNICEF ተጠሪዋ ተናግረዋል። ግን በቂ አይደለም ባይ ናቸው።

ከድርቁ በተጨማሪ የአሸባብ ጥቃት ለሶማሌያውን መፈናቀል ዋነኛው ምክንያት ነውምስል Mariel Müller/DW
የውጭ ጣልቃ ገብነትን የተቃወሙ ሱዳናውያን በየተመድ ደጃፍ ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ባለፉት ሳምንታት ሱዳን ውስጥ ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። በአንድ ወገን ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል ቦታውን ለሲቪል አስተዳደር ለቅቆ ወደ ምሽጉ ይመለስ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በሌላ ወገን በሺህዎች የሚቆጠሩት የተቃውሞ ሰልፈኞች ይዘዋቸው ከሚወጡ መፈክሮችን ውስጥ «ፎልከር ይውጡ!» «የውጭ ጣልቃ ገብነት አንፈልግም!» የሚሉት ይገኙበታል። ጀርመናዊው ዲፕሎማት ፎልከር ፔርተዝ የተመድ በሱዳን የተቀናጀ የሽግግር ሂደት በሚል ያሰማራው ተልዕኮ መሪ ናቸው። ተልዕኮው በጎርጎሪዮሳዊው 2020ዓ,ም በመንግሥታቱ ድርጅት ውሳኔ ሱዳን የምታካሂደውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲረዳ የተዋቀረ ነው። የተልዕኮው መሪ የሆኑት ጀርመናዊው አምባሳደር ሱዳን ውስጥ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከወታደራዊው ኃይል እንዲሁም ከሌሎች ቡድኖች ጋር በመሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት የችግሩ አካል ተድርገው መታየታቸው እንደማይቀር ይናገራሉ። ምንም እንኳን ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ሃሳቡን በነጻነት መግለጹ የሚበረታታ ነው ቢሉም ትኩረታቸው መሠረታዊው ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ግለሰብ ላይ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

«እርግጥ ነው ሀሳብን ለመግለጽ አደባባይ መውጣቱ ምንም ችግር የለውም እኛም በተመድ ውስጥ ለዚህ  እና ለሰላማዊ ስብሰባዎች እና ሰልፎች መብት ነው የቆምነው። ይህ ጥሩ ነው፤ እንደትልቅ ጉዳይም አልወስደውም። እንደሆነው ግን ነገሮች ከግለሰብ ጋር መገናኘታቸው እኔን አላስደሰተኝም። እውነታው ግን በፖለቲካው ውስጥ መፍትሄ እንዲገኝ የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸው ነው።»

እሳቸው እንደሚሉት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ 2,500 የሚሆኑ ሰዎች በሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ውስጥ ከሚገኘው የተመድ ጽሕፈት ቤት ደጃፍ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በዚህ ሳምንት መጨረሻም ተመሳሳይ ሰልፍ ይኖራል ብለው ይጠብቃሉ።

በሱዳን የቀጠለው ተቃውሞ ምስል Marwan Ali/AP Photo/picture alliance

በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ዓ,ም የሱዳን የረዥም ዓመታት አምባገነን መሪ ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ሲወገዱ ሲቪሉን እና ጦር ኃይሉን ያካተተ የሽግግር መንግሥት ተመሥርቶ ነበር። በወቅቱ ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር ልትሸጋገር ነው በሚል ተስፋ ተጥሎበት ምርጫም በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 ለማካሄድ ታቅዶ ነበር። ሆኖም ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የሽግግር መንግሥቱን መንበር የገለበጠው ወታደራዊ ኃይል ዳግም ሥልጣኑን ያዘ። በዚህም መዘዝ በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ካቢኔ የሌላት ሱዳን የውጪ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት፤ የዕዳ ቅነሳም ሆነ የልማት እርዳታው በመቆሙ ኤኮኖሚዋ ከባድ ችግር ላይ ወድቋል። በዓለም የምግብ መርሃግብር ግምትም በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት አንድ ሦስተኛው የሱዳን ህዝብ የምግብ ዋስትና አይኖረውም።

የጦር ኃይሉ ሥልጣኑን ከያዘ ወዲህ በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚታገሉ ሲቪል ቡድኖች በአደባባይ የሚያደርጉት ተቃውሞ ቀጥለዋል። እንዲያም ሆኖ ወታደራዊው ኃይልም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሱዳን ውስጥ እንዲኖር የሚታገሉት ቡድኖች የተመድ በሱዳን የተቀናጀ የሽግግር ሂደት በሚል ያሰማራውን ተልዕኮ አልተቃወሙም ነው የሚሉት የተልዕኮው መሪ ጀርመናዊው ዲፕሎማት። አብዛኞቹ «የውጭ ጣልቃገብነት» ያሉትን የተቃወሙት ሱዳናውያን አንድም በጽንፈኛ ሙስሊምነት የተለዩ፤ አንድም ዳግም ወደ ሥልጣን ለመምጣት ያለሙ የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ አልበሽር ደጋፊዎች መሆናቸውን የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። 

ከሳምንት በፊት የሱዳን ዋነኛው የሲቪል ጥምረት የለውጥ እና የነጻነት ኃይሎች በእንግሊዝኛ ምህጻሩ FFC፤ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለመመለስ ከጦር ኃይሉ ጋር አዲስ ስምምነት ለመፈራረም ማቀዱን ይፋ እንዳረገ ሮይተርስ ዘግቧል። ፔርተዝም አሁን የተሻለ ነገር እየታየ ነው ይላሉ።

ተቃውሞ ከዋና ከተማ ውጪም እየተካሄደ ነውምስል AFP

«አሁን ያለውን ሁኑታ የዛሬ ዓመት ከነበረው ጋር ስናነጻጽረው ነገሮች አሁን ተሻሽለዋል። ለአንድ ዓመት ያህል ሁሉም ባለበት ደርቆ እና አንደኛው ሌላኛውን ቡድን ይገፋ ነበር። አሁን የሆነ ነገር እየሆነ ነው እናም ነገሮችን ወደማቻቻል እየተደረሰ ነው።»

ምንም እንኳን ከሆነ ስምምነት ላይ መድረስ ቢቻልም ሱዳን ከአንደኛው የፖለቲካ አጣብቂኝ ወደ ሌላኛው እየገባች መሆኑ ነው ኮህሎድ ካሂር መቀመጫውን ኻርቱም ላይ ያደረገው የፖለቲካ ተንታኞች ቡድን አማካሪ እና የሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጉዳይ ምሁር የሚናገሩት።

«አሁን በጉዳዩ ላይ አዲስ ዓይነት አጣብቂኝ እየታየ ነው። በአንድ ወገን የFFC እና የጀነራሎቹን ስምምነት የሚደግፉ ሰዎች አሉ። በሌላው በኩል ደግሞ ይኼ የጁባ የሰላም ውል ፈራሚዎች የሚባሉት እንደ ጅብሪል እና ቲጃኒ እንዲሁም ከምሥራቅ ሱዳን የሆኑት ሰዎች ይህንን ስምምነት አልፈረሙም። እዚያ ላይ ነው አዲሱ አጣብቂኝ፤ ይህ ደግሞ የአጣብቂኙን ባህሪ ሁሉ ይለውጠዋል። ምን ማለት ነው፤ ስምምነቱ በራሱ አስተማማኝ ነው ማለት አንችልም። በነገራችን ላይ ከሰኔ ወር ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስም አቋም ነው። ለዚህም ነው የአጣብቂኙ ባህሪ ተለውጧል ማለት የምንችለው።»

የቀጠለው የሱዳናውያን ተቃውሞ በኤል ኦቢድ ምስል AFP

ካሂርም ሆኑ ጀርመናዊው አምባሳደር ፔሬትዝ፤ ሱዳን ውስጥ አሁን የፖለቲካ ተዋናዮቹ የተስማሙበትን ሃሳብ የሚንድ ነገር እንዳለ ያስባሉ። ይህም ለምሳሌ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ማን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ይያዝ እና የጦር ኃይሉን እንዴት ይሁን የሚሉት ጥያቄዎችን ያጠቃልላል ባይ ናቸው። አሁን ባለው ዕቅድ የሚመሠረተው የሽግግር መንግሥት የሁለት ዓመት ዕድሜ እንዲኖረው ነው የታሰበው። ካሂር ግን የታሰበውን ሁሉ ለማሳካት ጊዜው አጭር ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። በዚያም ላይ የሱዳንን ጦር ኃይል መሪዎች ሚና በቀላሉ ማየት እንደማይገባም የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የጦር ኃይሉ ቀደም ሲል ሱዳን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመጣ እንደሚሻ ሲገልጽ ቢቆይም ዋል አደር ብሎ ሲቪሎች የተካተቱበትን የሽግግር መንግሥት በኃይል ከሥልጣን ማስወገዱ ይታወሳል። የሱዳን ፖለቲካ ተለዋዋጭ መሆኑን የሚናገሩት ካሂር በበኩላቸው ባለሥልጣናት ህዝብ እያማከሩ ለመሥራት ካልሞከሩ የሚደረገው ውልም ሆነ ማንኛውም የፖለቲካ ሂደት የትም አይደርስም ባይ ናቸው። FFC ምንም እንኳን የዴሞክራሲ ደጋፊ ኃይሎችን ያሰባሰበ ቢሆንም ቀድሞ የነበረውን አይነት ድጋፍ የለውም ነው የሚሉት። በዚህም ምክንያት ከተለያየ ወገን የህዝቡን ሃሳብ ለማዳመጥ ካልሞከረ የተጀመረው ሂደት ሩቅ እንደማይጓዝ እቅጩን ተናግረዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW