1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሶማሌ ክልል በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት

ዓርብ፣ ግንቦት 28 2018

የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ከሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ ተወካዮች ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር ጠቅሰው በየምርጫ ጣቢያዎች በወጡ ጊዜያዊ ውጤቶች መሠረትም ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል። #ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ ተወካዮች ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር ጠቅሰው በየምርጫ ጣቢያዎች በወጡ ጊዜያዊ ውጤቶች መሠረትም ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ ተወካዮች ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር ጠቅሰው በየምርጫ ጣቢያዎች በወጡ ጊዜያዊ ውጤቶች መሠረትም ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።ምስል፦ Private

በሶማሌ ክልል በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት

This browser does not support the audio element.

በሶማሌ ክልል በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም.  በኢትዮጵያ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና በአንፃሩ ፍትሀዊ በሆነ መልኩ መከናወኑን በሶማሌ ክልልበምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ ።

የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ከሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ ተወካዮች ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር ጠቅሰው በየምርጫ ጣቢያዎች በወጡ ጊዜያዊ ውጤቶች መሠረትም ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

ይፋዊ ባልሆኑ የምርጫ ጣቢያ ጊዜያዊ ውጤቶች መሰረት በክልሉ በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምክር ቤት ድምፅ ማግኘታቸው በቀጣይ የክልሉን ማህበረሰብ ችግር በመቅረፍ ረገድ የተሻለ ስራ እንዲሰራ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም  ጠቁመዋል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱላሂ አዶው በምርጫው ጊዜያዊ ውጤት ድምፅ ማግኘታቸውን እና ምርጫው ሰላማዊ እና ነፃ እንደነበር ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በክልሉ ምርጫ የተሳተፈው የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሶፌፓ) ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ ሁሴን የምርጫውን ሰላማዊነት ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው አሉኝ የሚላቸው ቅሬታዎች ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ዩሱፍ በምርጫው ጊዜያዊ ውጤት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፅ ማግኘታቸውን ገልፀዋል። 

ቀደም ሲል ሙሉ በሙሉ በገዢው ፓርቲ ይያዝ በነበረው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ተፎካካሪዎች ውክልና ማግኘታቸው ለኅብረተሰቡ ችግሮች መፈታት አስተዋፅኦ ያበረክታል የሚል እምነት እንዳላቸው የኦብነግ ስራ አስፈፃሚው አቶ አብዱላሂ አዶው እና የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲው አቶ ዩሱፍ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል መራጭ ድምጽ ሲሰጡ ምስል፦ Private

በሶማሌ ክልል የተካሄደው ምርጫ እና የፓርቲዎች አስተያየት

 ግንቦት ሃያ አራት ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫበሶማሌ ክልልከገዢው ብልፅግና ውጭ አምስት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች በምርጫው ተሳትፈዋል።

ሰላማዊ የትግል አማራጭን በመቀበል ከመንግስት ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ሀገር የገባው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በዚሁ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በክልሉ ተወዳድሯል።

ከአምስት አመት ቀደም ሲል በሀገሪቱ በተካሄደው ተመሳሳይ ምርጫ ተሳትፎ ምንም ድምጽ ሳያገኝ እንደቀረ ያስታወሱት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብዱላሂ አዶው በዚህኛው ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት መነሻነት ለክልሉ ምክር ቤት በለስ ሳይቀናቸው እንዳልቀረ ገልፀዋል።

በክልሉ ወረዳዎች በምርጫው ተሳትፎ ማድረጋቸውን ለዶይቼ ቬለ የነገሩት አቶ አብዱላሂ የክልሉ ምርጫ "ከፀጥታ አንፃር ሰላማዊ ከገዢው ፓርቲ ተፅእኖም ነፃ" ነበር ብለዋል።

ምንም እንኳን "የአብላጫ ድምፅ አሰራር" በስራ ላይ የሚውል ቢሆንም እርሳቸው የሚውክሉትን ኦብነግን ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ ምክር ቤት መወከል በኅብረተሰቡ ችግሮች ዙርያ መንግስትን ለመሞገት ይረዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ ሁሴንምስል፦ Private

ሌላኛው በምርጫው በሶማሌ ክልል የተወዳደረው የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ ሁሴን በክልሉ የተካሄደው ምርጫ ሰላማዊ እንደነበር ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በየምርጫ ጣቢያዎች በወጡ ጊዜያዊ ሪፖርቶች መሰረት የእርሳቸው ፓርቲ ለክልል እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ ሳያገኝ እንዳልቀረ ጠቅሰው የተወሰኑ ቅሬታዎች አሉን ባሏቸው ቦታዎችም በውይይት መፍትሄ እንደሚያገኙ እምነታቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ ምክር ቤት አለመኖሩን በድክመት የገለፁት አቶ ዩሱፍ በቀጣይ ፓርቲያቸው ከምርጫው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ እንደሚያወጣ አስታውቀዋል ።

እንደ ኦብነግ ሁሉ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤት መወከል በተለይ ለኅብረተሰቡ ማህበራዊ ችግሮች መፍታት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል እምነት እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

መሳይ ተክሉ

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW