በሶማሌ ክልል በጎርፍ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 28 አሻቀበ
ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2016በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ እና የወንዞች ሙላት ሳቢያ እስካሁን ከአርባ ስድስት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እንዲሁም በደራሽ ጎርፍ ሳቢያ ሃያ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ አስታውቋል። አደጋው በሰብል ፣ በእንስሳት እና በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሱም ተገልጧል።
በጉዳቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብ እና ሌሎች ድጋፎች በጀልባዎች እና በሄሊኮፕተር በመታገዝ የማድረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ከዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።
በአካባቢው ዛሬም ድረስ እየጣለ ያለው ዝናብ ተጫማሪ ጎርፍን ጨምሮ ህብተረተሰቡ አስቀድሞ በሚገለገልበት ውሀ ላይ ብክለት በማድረስ ሌላ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ጋርጧል ።
የሶማሌ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ መሀመድ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ በክልሉ እየጣለ ባለው ዝናብ በበርካታ ዞኖች የተከሰተውን ጎርፍ እና የወንዞች ሙላት ተከትሎ እስካሁን ሃያ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መፈናቀላቸውን እንዲሁም በሰብል እና በእንስሳት ላይ ስለደረሰው ጉዳት አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በጎርፍ እና የውሀ መጥለቅልቁ ሳቢያ መንገዶች ፣ ጤና ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቆሙት አቶ አብዱልፈታህ ዛሬም ድረስ በአካባቢዎቹ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ ሌላ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የክልሉ እና የፌደራል መንግስት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለተጎጅዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው በበጎ ፍቃደኞች እና በሄሊኮፕተር የታገዘ የተለያየ ድጋፍ የማድረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ወገን ድርቅ በሌላው ጎርፍ ያስከተለው የአየር ሁኔታ
ህብረተሰቡ ለመጠጥ እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚጠቀምበት ውሃ በጎርፉ ሳቢያ ተበክሎ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የጠቀሱት አቶ አብዱልፈታህ በመንግስት በኩል ያለውን ዝግጅት አብራርተዋል።
የጎርፉ ጉዳት
በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ የገናሌ እና ሸቤሌ ወንዞች ባሉባቸው ዞኖች የተከሰተ የውሀ መጥለቅለቅ እንዲሁም ወንዝ በሌለባቸው አካባቢዎች በመጣ ደራሽ ጎርፍ ሳቢያ በአጠቃላይ በሰላሳ ሶስት ወረዳዎች እና በአንድ መቶ አርባ ቀበሌዎች ጉዳት መድረሱን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ አስታውቋል ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ መሀመድ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት ተፈጥሯዊ በሆነው በዚህ አደጋ ሃያ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አርባ ስድስት ሺህ ሶስት መቶ ሰባ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ይህም ካለፋው ዘገባችን በኃላ ቁጥሩ መጨመሩን የሚያመልክት ነው።
በሌላ በኩል አስር ሺህ አምስት መቶ አርባ ስድስት ሄክታር እርሻ ተጎድቷል ያሉት ኃላፊው እስካሁን ባለው መረጃ ከሶስት ሺህ ስድስት መቶ በላይ እንስሳት መሞታቸውን ፤ የጉዳቱ ትክክለኛ መጠን ባይታወቅም በመንገድ ፣ በጤና እና ትምህርት መሰረተ ልማት ላይም ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል።
ዶሎ አዶ እና ጎዴ ላይ ለተጎጅዎች ድጋፍ ማከፋፈል የሚያስችል ማዕከል ተቋቁሞ የተለያዩ ስራውን የሚመሩ ኃላፊዎች መመደባቸውን የተናገሩት አቶ አብዱልፈታህ "እስካሁን ከአስራ ስድስት ሺህ በላይ አባወራዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ደርሰዋል" ብለዋል።
በሶማሌ ክልል ጎርፍ ሰዎች ገደለ፣ ሺዎችን አፈናቃለም
የክልሉ እና የፌደራል መንግስት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው ህብረተሰቡ እርስ በእርስም እየተረዳዳ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮምሽን ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት አቶ አብዱልፈታህ ከኮምሽኑ የተገኘ አንድ ትልቅ ጀልባን ጨምሮ በሄሊኮፕተር ሰዎችን ለማትረፍ እና እርዳታ ለማድረስ እንጠቀማለን ብለዋል።
በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ለመጠጥ እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚጠቀምበት ውሃ በጎርፉ ሳቢያ ተበክሎ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ጋርጧል። በክልሉ ዛሬም ድረስ እየጣለ ነው የተባለው ዝናብ ተጫማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ስጋት አለ።
መሳይ ተክሉ
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ