በሶማሌ ክልል ድርቁና የርዳታ አቅርቦት
ረቡዕ፣ ግንቦት 2 2009የሶማሌ ክልል ነዋሪ መሆናቸዉን የገለፁልን ቀደም ሲል ድምጻቸዉን የሰማችኋቸዉ እማኝ እንደሚሉት ድርቁ አጠቃላይ ክልሉን ነዉ የጎዳዉ። እንዲያም ሆኖ ክልሉን ተዘዋዉረዉ የመመልከት ዕድል ያገኙ ጋዜጠኞችም ሆኑ እኝህ የአካባቢዉ ነዋሪም ድርቅ ጉዳት ላስከተለበት የሶማሌ ክልል ነዋሪ ከመንግሥት የሚደረግ ርዳታ ቢኖርም በቂ እንዳልሆነ ነዉ የሚናገሩት።
የሶማሌ ክልልን የአደጋ መከላከል ጉዳይ ባለስልጣናት ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደዉልም በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድሏል ስለተባለዉ የእርዳታ አቅርቦት ጉዳይ ማብራሪያ ለዛሬ ሊሰጡን አልቻሉም። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ ግን ከፌደራል መንግሥት ተገቢዉ እርዳታ እየቀረበ ነዉ ይላሉ።
እሳቸዉ እንደገለፁት የሦስተኛዉ ዙር የምግብ ርዳታ አቅርቦት የሚያዝያ ወር እና ግንቦትን ያጠቃልላል። ከእርዳታዉ መካከልም 35 በመቶዉ አልሚ ምግብ ነዉ። የርዳታ አቅርቦቱም በመኸር የተደረገዉን ቅኝት መሠረት ያደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።
ከሚመለከተዉ የክልሉ አካል ጋር ያላሰለሰ ግንኙነት መኖሩን ያመለከቱት አቶ ደበበ ዛሬም ደዉለዉ የተጎጂዉን ሕዝብ ቁጥር መሠረት ያደረገ የምግብ ርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ማረጋገጣቸዉንም ተናግረዋል። ስለሶማሌ ክልል የድርቅ ተጎጂዎች የሚነገረዉ ሌላዉ ጉዳይ በአካባቢዉ ድንበር ተሻግረዉ ለገቡት የጎረቤት ሀገር ስደተኞች የሚሰጠዉ የዉኃ፣ የጤናም ሆነ የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ያለመሆናቸዉ ጉዳይ ነዉ። ጉዳዩን መሥሪያ ቤታቸዉ ይከታተል እንደሆነ አቶ ደበበን ጠይቀናል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባዉ ይከታተሉ፤
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ