1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሸገር ከተማ የመንገድ ዳር ቤቶች መፍረስ

ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017

ከቤቶቹ መፍረስ በኋላም መዳረሻቸውን እንደማያውቁ የሚገልጹ ነዋሪዋ ለልማት ይፈርሳል በተባሉት መኖሪያቸውና መተዳደሪያቸው ምትክ ሌላ መኖሪያ አለመመቻቸት አሊያም ስለ ካሳ መከፈል አለመከፈልም እርግጠኛ አደሉም።

የሸገር ከተማ ባለሥልጣናት በርካታ ቤቶችን እንደሚያፈርሱ ለነዋሪዎቹ አስታዉቀዋል
በሸገር ከተማ መስተዳድር በየመንገድ ዳሩ የሚገኙ ቤቶች ይፈርሳሉ መባሉ ነዋሪዎችን ለሥጋት አጋልጧልምስል Seyoum Getu/DW

በሸገር ከተማ የመንገድ ዳር ቤቶች መፍረስ

This browser does not support the audio element.

          

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር በርካታ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑን ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡እንደነዋሪዎቹ እንደሚሉት ለኮሪደር ልማት በሚል በሚፈርስባቸው ቤቶች ምትክ የሚከፈላቸው ካሳ እና ምትክ ቦታ ስለመመኖር አለመኖሩ በውል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡የአዲስ አበባዉ ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ የከተማ አስተዳደሩን ባለስልጣናት ለማነጋገር ቢሞክርም አልተሳካለትም።

በሸገር ከተማ አስተዳደር የሰበታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ70 ዓመት አዛውንት ጎጀብ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ላለፉት 42 ዓመታት ኖረዋል፡፡ ከሰሞኑ ግን የከተማ አስተዳደሩ ለመንገድ ዳር ልማት ላለው ፕሮጀክት በርካታ ቤቶችን እያፈረሰ በመሆኑ የእሳቸውም ቤት ከነዚህ ከሚፈርሱ ቤቶች መሆኑ ስነገራቸው በቀጣይ ማረፊያ መውደቂያቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አዕምሮን የሚያሳርፍ በቂ ማብራሪያ ሳይሰጣቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ “ዝም ብለው ነው ለክተው የሄዱት፡፡ እንዲፈርስ ግን ምልክት አኑረዋል፡፡ ከጎነ ያለውም እየፈረሰ ነው” ያሉት አዛውንቷ በከፊል እየኖሩበት እያከራዩ መተዳደሪያቸው ያደረጉት ቤቱ መጦሪያቸውም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አሁን ላይ በዚህ መኖሪያ ቤታቸው ላይ የመፍረስ ምልክት ተደርጎ እንደሚፈርስ ማረጋገጫ ስሰጣቸው፤ ከአጠገባቸውም ያሉ በርካታ ቤቶች እየፈረሱ መሆን በመግለጽም ለ42 ዓመታት የኖሩበት መኖሪያቸውና ቀዬያቸውን ጥሎ መውጣት ኑሮያቸውን እንደማናጋት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከቤቶቹ መፍረስ በኋላ የሚያሳስበው የተፈናቃዮች እጣፈንታ

ከቤቶቹ መፍረስ በኋላም መዳረሻቸውን እንደማያውቁ የሚገልጹ ነዋሪዋ ለልማት ይፈርሳል በተባሉት መኖሪያቸውና መተዳደሪያቸው ምትክ ሌላ መኖሪያ አለመመቻቸት አሊያም ስለ ካሳ መከፈል አለመከፈልም እርግጠኛ አደሉም፡፡ “ሌላውም ተነስቶ እየሄደ ነው ወዴት እንደምሄድ አላውቅም፤ መጦሪያም ይህ ቤት ነበር” ያሉት ነዋሪዋ ከአጠገባቸው ቤታቸውን ያፈረሱ ነዋሪዎች ተነስተው ሌላ ቦታ ቤት እየተከራዩ  ከመኖር ውጪ የተሰጣቸውን አማራጭ አለመመልከታቸውን በስጋት አንስተዋል፡፡

ከጥንትም በይዞታ ማረጋገጫ ለ70 ዓመታት ግድም እናታቸው በሰሩት መኖሪያ ላይ ከእናታቸው ጋር በጥገኝነት እየኖሩ እንደሚገኙ አስረድተው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት ሌላኛዋ የዚያው የሰበታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ፤ “ከሰባ ኣመት በላይ የአቅመ ደካማ እናታቸው ንብረት የነበረው ይዞታ ካርታ እና ዬዞታ ማረጋገጫ ባለመብት የሆንበት” ነው ይላሉ፡፡ እስለከ መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ቤቱን እንዲያፈርሱ መጠየቃቸውንም ገልጸው ከዚያ ግን የተዘጋጀላቸው ምንም ኤነት አማራጭ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

በሸገር ከተማ መስተዳድር በየመንገድ ዳሩ የሚገኙ ቤቶች ይፈርሳሉ መባሉ ነዋሪዎችን ለሥጋት አጋልጧልምስል Seyoum Getu/DW

ለሚፈርሰው ቤትም ካሳ ይከፈላቸው እንደሆን የተጠየቁት አስተያየት ሰጪ ነዋሪዋ፤ “መጀመሪያ ካሳ እንሰጣለን የሚል ቃል የከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን አሰባስቦ ባወያየበት ወቅት ቃል ብገባልንም አሁን ላይ ምንም የተሰጠን ማረጋገጫ የለም” ሲሉን ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቤቶቹ መፍረስ፤ የኢኮኖሚ  መናጋት

ስማቸውን እንዳንጠቅስ እና ድምጻቸውን እንዳንጠቀም ጠይቀው ከዚያው ከሰበታ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አስተያየት ሰጪ፤ እየፈረሱ ባሉት የንግድና መኖሪያ ቤቶች የበርካታ ሰዎች የኑሮ መሰረት ተንዷል ብለዋል፡፡ የቤቶች ፈረሳው በሰበታ፣ በጎጀብ፣ ዲማ፣ ፉሪ፣ ወለቴ እና ኬንቴሪ በሚባሉ አከባቢዎች ከጥቃቀን ሱቆች እስከ ትላልቅ ህንጻዎች መፍረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ በከተማው በቡራዩ እና ሌሎች ክፍለ ከተሞችም ጭምር ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

በልማት እቅዱ፣ የሚፈናቀሉ ነጋዴዎችና ነዋሪዎች ቀጣይ እጣፈንታ ብሎም ከህብረተሰቡ ጋር ስለተደረገው ውይይት ከሸገር ከተማ ከንቲባ እና ምክትላቸው ማብራራዎችን ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት የእጅ ስልካቸው ስለማይመልስ ጥረቱ ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የከተማው ህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ኤልያስም መረጃውን ልሰጡን ተደጋጋሚ ቀጠሮ ብሰጡንም በሰኣቱ ደጋግመን ስንደውልላቸው ስልካቸውን አያነሱም፡፡

በአዲስ አበባ በቅርቡ ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በጠቅላ ሚኒስትር አብይ አህምድ ይፋ ስደረግ ሸገር ከተማን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ስራውን እንዲያስቀትሉ አቅጣጫ መቀመጡን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW