በሺናሻ ማህበረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዜዴ
ሰኞ፣ ሰኔ 23 2017
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኙት የሺናሻ ማህበረሰብ የራሳቸው ‹‹ነሞ›› የተባለ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት አላቸው፡፡ የብሔረሰቡ ምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች እንደሚሉትም ይህ የግጭት አፈታት ዜዴ የማህበረሰብ ቀውስ በማስቀረት ከፍተኛ ሚና አበርክቷል፡፡ በስርዓቱ የተጣላ ታርቆ፣ በዳይ ካሳ የሚከፍልበት እና ወደ ዘመናዊ ህግ ወይም ፍርድ ቤት ጉዳዩ ሳይደርስ መፍትሄ የሚያግኝበት ስርዓት እንደሆኑ ያነጋገርናቸው አንድ የሀገር ሽማግሌ እና በብሄረሰቡ ላይ ጥናት የሰሩ አንድ ምሁር ገልጸዋል፡፡
ግጭት ሳይባባስ መፍትሄ ለማበጀት ‹‹ነሞ›› ከፍተኛ ድርሻ አለው
የ‹‹ነሞ›› ባህላዊ ስርዓት
በክልሉ መተከል ዞን ውስጥ በስፋት የሚኖሩት የሺናሻ ብሔረሰብበግለሰብ ደረጃ ሆነ በቡድን የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚፈቱበት ‹‹ነሞ›› የተባለው ባህል በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነቱ የጎላ ነው፡፡ አቶ ከከበደ ጉደያ የመተከል ዞኑ ዳንጉር የተባለ ወረዳ ተወላጅ ሲሆኑ የብሔረሰቡ ሀገር ሽማግሌ ናቸው፡፡ ይህ ባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እንደ ጥፋት መጠን እና ክብደት ቅጣቱ እንደምለያይ አቶ ከበደ ጉደያ ተናግረዋል፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ወንጀል ሲፈጽም በተለይም በድብቅ የተፈጸሙ ድርጊቶችን በቀላሉ ጥፋተኛን ለማጋለጥ እና ፈትሕን ለማስፈን ህብረተሰቡ እንደምጠቀምበት አመልክተዋል፡፡
የ‹‹ነሞ›› ባህላዊ ስርዓት ግጭቶች እንዳይከሰቱና የተከሰቱ ግጭቶችም ሳይባባሱ እልባት የሚስጥበት እና የማህበረሰብ ቀውስን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽ ማበርክቱን አቶ ከበዴ ጉዴያ አመልክተዋል፡፡ ብሄሰረቡ በሚገኙባቸው በተለይም ገጠራማ አካባቢዎች ስርዓቱ በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡
የሺናሻ ህዝብ ታሪክ የሚል መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት የብሔረሰቡ ተወላጅ አቶ አዲሱ አዳሜ በ‹‹ነሞ›› ስርዓት ውስጥ ከሚገኙት አራት ከሚደርሱት ደረጃዎች ማለትም ‹‹ቡሮ፣ነሞ፣ቴራ እና ፋላ ከተባሉት መካከል ሶስቱ ባሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ በነሞ ሰርዓት መሰረት የተከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ውሳኔ የሚሰጡ ከአንድ ሽማግሌ እስከ ሶሰት የሚደርሱ የሀገር ሽማግሌዎች በኩል መፍትሄ የሚያገኙ ሲሆን አብዛኛው የሚከሰቱ አለመግባባቶች ወደ ፍርድ ቤት ሳይደርሱ እልባት የሚያገኙ ናቸው ብሏል፡፡
‹‹ፋላ›› የመጨረሻ የዳኝነት ሥርዓት
በዚሁ ስርዓት በተለያየ ቡድንም ሆነ ግለሰብ መካከል የተከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ጥፋተኛ የተባለ አካል ካሳ መክፈል እና ሌሎች ቅጣቶችን መቀበል የሚጠበቅበት ሲሆን ተበዳይ ውሳኔውን ካልተቀበለው የመጨረሻ ውሳኔ የተባለውን ‹‹ፋላ›› ወደ ተባለው የዳኝነት ስርዓት ጉዳዮን በማቅረብ ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋል ብሏል፡፡ ይህ ስርዓት አሁን በተለያዩ ቦታዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ለሚገኙት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትም የራሱን ሚና ማበርከቱን አክለዋል፡፡
የሺናሻ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቱ ከጥንት ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየና አሁን ላለው ትውልድ የተላለፈ መሆኑን የተናገሩት የብሔረሰረቡ ተወላጆች ታሪኩ በስነ ጽሑፍ ደረጃ በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናት እና ምርመር ስራዎች አነስኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሺናሻ ብሔረሰብ በየዓመቱ የሚከበር የራሱን ‹‹ጋሪ ዎሮ›› የተባለ የዘመን መለወጫ ባህልም አለው፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ