በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላዊያን እስራኤል የገቡበት ዘመቻ ሰሎሞን ሲታወስ
ዓርብ፣ ግንቦት 22 2017
15 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወይም ቤተ እስራኤላዊያን በ36 ሰዓታት ውስጥ ከአዲስ አበባ እስራኤል የገቡበት ዘመቻ ሰሎሞን 34 ዓመት ሞላው።
ከእስራኤል ኤምባሲ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በአውቶቡስ፣ ከዚያም በቀጥታ ቴላቪቭ 48 አውሮፕላኖች 35 በረራዎችን በማድረግ እስራኤል የገቡት ቤተ እስራኤላዊያን ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ እና እስራኤል ግንኙነት ላይ በጎ ድልድይ ሆነው እንደሚኖሩም ተገልጿል።
ከዘመቻ ሰሎሞን በፊትም ሆነ በኋላበርካታ ቤተ እስራኤላዊያንከኢትዮጵያ የወጡ ሲሆን አሁን እስራኤል ውስጥ 180 ሺህ ከኢትዮጵያ የሄዱ ቤተ እስራኤላዊያን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በጦር ሠራዊትና በደህንነት እንዲሁም በሌሎች መስኮች ከሌሎች አይሁዶች ጋር ተዋህደው እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው የሚያገለግሉት አምባሳደር አብራሃም ንጉሴ ከ34 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ከአዲስ አበባ በቀጥታ እስራኤል እንዲጓጓዙ ከተደረጉት ቤተ እስራኤላዊያን መካከል አንዱ ነበሩ። የዘመቻ ሰሎሞንን የጉዞ ሁኔታ በመግለጽ ታሪኩን እንዲህ ያስታውሳሉ።
"በ36 ሰዓት ውስጥ በ48 አውሮፕላን ከ14 ሺህ እስከ 15 ሺህ የማያንሱ ወገኖቻችንን [ቤተ እስራኤላዊያንን] ወደ እስራኤል ማስገባት ተችሏል።"
ከዘመቻ ሰሎሞን በፊት በ 1977 በሱዳን በኩል ዘመቻ ሙሴ በተባለው የጉዞ እቅድ ስምንት ሺህ ያህል ቤተ እስራኤላዊያን ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ሲወጡ አራት ሺህ ያህሉ ግን በልዩ ልዩ ምክንያት በበርሃ ሞተው ቀርተዋል።
ቤተ እስራኤላዊያኑ እንደሌሎች ከ100 ሀገራት በጽዮናዊነት ንቅናቄ ወደ እስራኤል እንደተሰባሰቡት አይሁዶች ሁሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራ ዕድል ሲያገኙ ቆይተዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የዘረኝነት፣ የመገለል፣ በወጣቶችና በፖሊሶች መካከል መጋጨት በስፋት ይስተዋሉ እንደነበር ይታወቃል።
"በዙህ ሂደት ላይ ችግር የለም ማለት አልችልም። ነበሩ ችግሮች። እነዚያ ችግሮች ተወግደዋል። አሁንም አንዳንድ ችግሮች በሀገሪቱ ሕግ ይፈታል።"
ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የተጓዙት ቤተ እስራኤላዊያን በሀገሪቱ ፖለቲካ፣ በፓርላማ፣ በጦር ሠራዊት፣ በደህንነት፣ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ዘርፎች ገብተው እየተሰማሩ መሆኑን የያኔው የዘመቻ ሰሎሞን ተጓዥ፣ የዛሬው በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደርና የሀገሪቱ የቀድሞ የፓርላማ አባል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ ገልፀዋል።
አማርኛ የሚናገሩት አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ ቤተ እስራኤላዊያን ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት "ሕያው ድልድይ ናቸው" በማለት ትንሿ ኢትዮጵያ እስራኤል ውስጥ ትገኛለች ሲሉም ትናግረዋል።
"የመንግሥት መለወጥ የማይሽራቸው፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ቢኖር ባይኖር የማይሽራቸው፣ ሁለት ምሰሶዎች አሉ" ብለዋል። እነዚህም ብዙ ቤተ እስራኤላዊያን መኖር እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያናት አብያተ ክርስትያናት ናቸው።
ከንግሥት ሳባ እና ከጠቢቡ ሰሎሞን የሚመዘዘው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአየር ትራንስፖርት፣ በንግድ፣ በግብርና ፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በባሕልና በሃይማኖት ረገድ እያደገ የመጣቱም ይነገራል።
ሰለሞን ሙጨ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ