1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሽከርካሪዎች እና የሾፌሮቻቸው መታገትና መጠቃት እየጨመረ ነዉ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2016

በኦሮሚያ ክልል ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መቃጠላቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ነበር። ይህ ክስተት በትናንትናው እለትም ቀጥሎ ከመተሃራ ከተማ ወጣ ብሎ በዋና መንገድ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ታጣቂዎች አራት ተሽከርካሪዎችን ማንደዳቸውን የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ለዶቼ ቬለ በስልክ አስታውቀዋል።

የእርዳታ እሕል የጫኑ ከባድ መኪኖች በኢትዮጵያ አዉራጎዳ ላይ
የሐገር አቋራጭ ከባድ መኪኖችና ሾፌሮቻቸዉ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ጥቃት ይደርስባቸዋልምስል Alemnew Mekonnen/DW

አዲስ አበባን ከምሥራቅ፣ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያና ከጁቡቲ ጋር በሚያገናኘዉ አዉራ መንገድ በሚጓዙ መንገደኞችና ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለዉ አደጋ እየተደጋገመ ነዉ።የዛሬ 10 ቀን ግድም የቁልቢ ገብርኤልን ተሳልመዉ የሚመለሱ መንገደኞች በታጣቂዎች ተገድለዉ ነበር።ትናንት ደግሞ ምሥራቅ ሸዋ መተሐራና ወለንጪቲ መሐል ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት አራት የጭነት መኪኖች መቃጠላቸው ነግራል።የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የትናንቱን ጥቃት በአሽከርካሪዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈፀም ግድያ፣ እገታና የቤዛ  ጥየቃ አካል ብሎታል።የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ለጥቃቱ የኢትዮጵያ መንግስት ኦነግ ሸኔ በሚል ስያሜ በአሸባሪነት የፈረጀዉን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊቲን ተጠያቂ ያደርጋል።

አዲስ አበባን ከምስራቅ፣ ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያና ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘዉ አዉራ መንገድምስል DW/Y. Geberegzihaber

መፍትሔ ያልተገኘለት የተሽከርካሪዎች እና ሾፌሮቻቸው ጥቃት 

 

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መቃጠላቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ነበር። ይህ ክስተት በትናንትናው እለትም ቀጥሎ ከመተሃራ ከተማ ወጣ ብሎ በዋና መንገድ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ታጣቂዎች አራት ተሽከርካሪዎችን ማንደዳቸውን የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ለዶቼ ቬለ በስልክ አስታውቀዋል።

ከፌዴራል ፖሊስ ባገኘነው መረጃ  ኦነግ ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን "ሕዝብን መፈናፈኛ ለማሳጣት ፣ ነዳጅ፣ ሸቀጥ ከውጭ እንዳይገባና ወደ ውጭም የሚላክ ምርት እንዳይጓጓዝ ለማድረግ አቅዶ" ይህንን አድርጓል።  
አሽከርካሪዎቹ የሚደርስባቸውን ችግር ለመገናኛ ብዙኃን በማሳወቃቸው እና ድምፃቸውን በማሰማታቸው ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን ከዚህ በፊት ተናግረዋል።
ከከባድ ሀገር አቋራጭ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች መካከል አንዱ አቶ ዳመነ ተሾመ ትናንት ተከሰተ የተበለውን ጉዳት ተጠንቶ የተደረገ በሚል ገልፀውታል።

ይህ ማሕበር ከዚህ በፊትም ችግሩ በመደጋገሙ ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ኤጀንሲ እና ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበራት ኮንፌደሬሽን ጋር መፍትሔ ፍለጋ ውይይት አድርጓል፣ ለሚመለከተውም አቤት ብሏል።

ከአዲስ አበባ ወደ ጁቡቲ የሚያመራዉ አዉራ መንገድ ሾፎሮችና መኪኖቻቸዉ ይጠቁበታልምስል DW/Y. Gebregziabher

እገታ እና ቤዛ ጥየቃ፣  አልፎም  ማቃጠል

 

የኢትዮጵያ የገቢ ምርትና ሸቀጦች ማጓጓዣ ዋነኛ መሥመር በሆነውና ኢትዮጵያን ከጅቡቲ በሚያስተሳስረው አውራ መንገድ ላይ በአገር አቋራጭ መኪኖች አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ፣ ዝርፊያና እንግልት አለመቆሙና በየጊዜው የማገርሸቱ ነገር  አሽከርካሪዎችን አሳስቧል።
በጉዳዩ ላይ ከወራት በፊት በሠራነው ዘገባ ስምንት የአገር አቋራጭ መኪኖች አሽከርካሪዎች በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ውስጥ በታጣቂዎች እንደተገደሉ እና ሌሎች ሰባት ባልደረቦቻቸው ደግሞ በተፈፀመባቸው ጥቃት የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጾ ነበር።
ይህ ችግር መልኩን ቀይሮ ወደ እገታ እና ቤዛ ወይም ማስለቀቂያ ገንዘብ ጥየቃ ከመሻገሩ አልፎ አሁን ተሽከርካሪዎችን እና የጫኑትን ንብረት ወደማቃጠል በመገባቱ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት በደብዳቤ ዛሬ ማሳወቃቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር ደረቅና ፈሳሽ ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ከ25- 30 ሺህ የሚደርሱ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችን በሥሩ ማቀፉን ከማሕበሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW