በኦሮሚያ የቀጠለው የፀጥታ ፈተና
ሐሙስ፣ ሐምሌ 6 2015በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ መቻራ ከተማ ሐምሌ 04 ቀን 2015 ዓ.ም. በአከባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከመንግስት የፀጥታ ኃይል ጋር ባካሄዱት የተኩስ ልውውጥ የሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል፡፡አንድ የአይን እማኝ፤ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ 4፡00 ሰዓት ገደማ በተካሄደው የከተማ ውስጥ ውጊያ ሰባት ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።በወቅቱ የነዋሪዎች ንብረት መዘረፉንና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል። የኦሮሚያው የፀጥታ ችግሩ በጉጂ ዞንም መቀጠሉ ተነግሯል፡፡ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ታጣቂዎች በቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ መቻራ ከተማ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን የሚገልጹት የአይን እማኝ ፣ ታጣቂዎቹ በእለቱ በብዙ አቅጣጫ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ነዋሪዎች ሸሽተው ወደ ጫካ አምልጠው ነበር ይላሉ፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ አስቀድሞም በአከባቢው የፀጥታ ስጋት እንደነበር አስረድተው በእለቱ በከተማዋ ውስጥ ለሰዓትት የቆየ የተኩስ ልውውጥ በሸማቂዎች እና የመንግስት ሰራዊት መካከል መደረጉንም ገልጸዋል፡፡“ታጣቂዎቹ በብዛት የገቡት መቻራ ከተማን ነው፡፡ ታጣቂዎቹ በገቡበት ሰዓት ባንክና የተለያዩ ንብረቶችም ዘርፈዋል፡፡ በእለቱ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ሰባት ናቸው፡፡ በተሉም መንደር 10 እና 15 የሚባለው ላይ ከፍተኛ ዘረፋ ተፈጽሟል፡፡”
እንደ ነዋሪው አስተያየት ሞተው አስከሬናቸው በአከባቢው ማህበረሰብ ከተቀበሩ ሲቪል ዜጎች በተጨማሪ በእለቱ በመንግስት እና በሸማቂ ቡድኑ ታጣቂዎች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥም በርካታ ሰው መሞታቸው ቢረጋገጥም ቁጥሩን ግን በውል ለመግለጽ አዳጋች ነው፡፡ “ከሁለቱም አካል የተጎዳ አካል አለ፡፡ ማንም ስለማያስጠጋ በርግጥ ቁጥሩን ይህን ያህል ነው ብሎ ለመግለጽ ለኛ አዳጋች ነው፡፡ የሸማቂ ቡድኑ ታጣቂዎች በሺዎች ስለሆነ ወደ ከተማው የገቡት በኋላ የመከላከያ ኃይል ተጨምሮ ነው ከከተማው ያስወጡዋቸው፡፡”
እንደ የአይን እማኙ የከተማዋ ነዋሪ መረጃ አሁንም በአከባቢው የጸጥታ ስጋቱ እንዳንዣበበ በመሆኑ መንግስት ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል እንዲመድም ነዋሪዎች ይጠባበቃሉ፡፡ በዚው ሃዋ ገላን በሚባል ወረዳ ከዚህ በፊት አምና ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. መንደር 20 እና 21 በሚባሉ የሰፈራ ቦታ ታጣቂዎች በሌሊት አደረሱ በተባለ ጥቃት ብያንስ 97 ሰዎች ገደማ በጅምላ መገደላቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ስለ ማክሰኞው ክስተትና አሁናዊ ሁኔታው ለማጣራት የአከባቢውን ባለስልጣናት ለማናገር የተደረገ ጥረት አልሰመረም፡፡ በተለይም የቄሌም ወለጋ ዞን የፀጥታ እና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተሰማ ዋሪዮ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ በመደወልና የጽሁፍ መልእክትም በመላክ መረጃውን ለማግኘት ሰፊ ጥረት ብናደርግም ምንም መልስ ባለመስጠታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
ስለዚህ ጥቃት በመንግስት በኩል የተሰማ ይፋዊ መግለጫም አልተሰማም፡፡ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኩልም ስለዚህ ጉዳይ የተባለ ነገር የለም፡፡ ይሁንና የታጣቂ ቡድኑ ዓለማቀፍ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኦዳ ተርቢ በትዊተር እንደጻፉት “ሰራዊታቸው በቀሌም ወለጋ ዞን በሶስት ወታደራዊ ካምፕ ላይ አነጣጥሮ ባካሄደው ኦፐሬሽን ድል ቀንቶታል፡፡” አቶ ኦዳ ኦፐሬሽን ስላሉት ጥቃት የሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ ግን የለም፡፡ከምዕራብ ኦሮሚያ በተጨማሪ በጉጂ ዞንም ተመሳሳይ የጸጥታ ችግሩ እያየለ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ስማቸውንና ድምጻቸውን እንዳንጠቀም ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን የጉጂ ዞን አጋ ወዩ ወረዳ ነዋሪ ሰሞኑን በወረዳው የጸጥታው መደፍረስ ተባብሷል ይላሉ፡፡ሰሞኑን በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ አንድ የአከባቢው ተወካይም በጉጂ ዞን ታጣቂዎች በወርቅ ማዕድን ንግድ ላይ ከመሳተፍ እስከ በእስካቫተር የተደገፈ የወርቅ ማውጣት ስራ መድረሳቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡በኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ኦሮሚያ በተጨማሪ በተለያዩ አከባቢዎች እገታ እና ልዩ ልዩ የፀጥታ ችግሮች እንደሚፈጸሙ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ይገልጻሉም፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ግን ከዚህ አንጻር በተደጋጋሚ የሚቀርብበትን ክስ ያስተባብላል፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ከወራት በፊት በታንዛኒያ የተካሄደው የሰላም ውይይት ያለተጨባጭ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በኦሮሚያ በተለዬ ሁኔታ የሰላም እጦትና አለመረጋጋቱ ማገርሸቱንም ነዋሪዎች ያማርራሉ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን በጨፌ ጉባኤ ከዚህ የከፋው የፀጥታ ይዞታ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ መንግስታቸው አሁንም በሰላማዊ መንገድ ለሚደረግ መፍትሄ ዝግጁ መሆኑን አስረድተው ነበር፡፡ “ከጦርነቱ የሚጠቀም አንድም አካል የለም፡፡ ከኦነግ ሸነ ጋር ደጋግመን መክረናል፡፡ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ለሰላም ነው፡፡ ደግመን ደጋግመን በኦሮሞ ህዝብ እና በዚህ በተከበረው ጨፌ ስም በሰላም ግቡ፣ ነገራችሁን በውይይትና እርቅ ፍቱ የሚል ጥሪ እናቀርብላቸዋለን፡፡ በግል ይሁን በቡድን በሰላም እስከመጣ ድረስ መንግስት መሄድ ከሚገባውም በላይ ለመሄድ ዝግጁ ነው፡፡ ምክንያት ብትሉ በዚህ ግጭት ህዝባችን ተጎዳ እንጂ ማንም አልተጠቀመም፡፡ በርግጥ ጠላቶቻችን ተጠቅመውበት ይሆናል፡፡ የክልላችን መንግስት ግን ከዚህ ሊጠቀም አይችልም፡፡ ይህን ነገር በሰላም ቋጭተን የፈለገ ልዩነት እንኳ ብኖረን ለቀጣይ ትግል መስራት አለብን፡፡ በሃይል የሚፈታ ችግር የለም፡፡ ባለፈው ጥሪ ካቀረብን በኋላ የሄድንበት መልካም ውይይቶች ነበሩ አሁንም እሱ እንዲቀጥል ነው የምናበረታታው፡፡ መንግስታችን ለዚህ ዝግጁ ነው፡፡ ለሰላም በራችን አይዘጋም፡፡ ህዝባችንም በጫካ ያሉ ልጆች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡ ማበረታታት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሰው ወጥቶ መግባት አለበት፡፡ በመሆኑም ጎን ለጎን የጸጥታ ማስከበር ስራው በየደረጃው የሚሰራ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ” ነበር ያሉት አቶ ሽመልስ በማብራሪያቸው፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ