በሰሞኑ ግርዶሽ ጨረቃ ለምን ደም ለበሰች ?
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
ያለፈው እሁድ በጎርጎሪያኑ መስከረም 7 ቀን 2025 ዓ/ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ/ም አመሻሽ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ፣ የአውሮጳ ፣ የእስያ ፣ የአውስትራሊያ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አስደናቂ የሆነ ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ታይቷል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ መሰሉ ተፈጥሯዊ ክስተት ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት የተለያየ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ ትርጉም ይሰጠዋል። የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት እና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ምንስቴር የኢኖቬሽን አማካሪ የሆኑት ፤የሥነፈለክ ሳይንቲስቱ ዶክተር ሶሎሞን በላይ እንደሚሉት ክስተቱ ሳይንሳዊ ነው።
የጨረቃ ግርዶሽ እንዴት ይከሰታል ?
እንደ ሥነፈለክ ሳይንቲስቱ ዶክተር ሶሎሞን የጨረቃ ግርዶሽ የሚከሰተው ፀሀይ፣ መሬት እና ጨረቃ በአንድ ረድፍ ላይ ሲሆኑ እና መሬት በፀሀይ እና በጨረቃ መካከል ሆና የፀሀይ ብርሃንን ስትጋርድ እና ጥላዋን ጨረቃ ላይ ስታሳርፍ ነው።
ተመራማሪዎቹ እንደሚገልፁት የመሬት ጥላ ሁለት አይነት ሲሆን፤የመጀመሪው የመሬት ድብዘዝ ያለ ጥላ (Penumbra) ሲሆን፣ ሁለተኛው እና ዋናው ደግሞ ጥቁር የመሬት ጥላ (Umbra) ነው። ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ የሚፈጠረው ታዲያ ፤ ጨረቃ ሙሉ በሙሉ «አምብራ» ተብሎ በሚጠራው በዚህ ጥቁር የመሬት ጥላ ውስጥ ስትገባ ነው። ጨረቃ ከምድር በአማካኝ 383,000 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝበት ጊዜ ፤ ይህ ግርዶሽ በዲያሜትር ወደ 9,334 ኪሎ ሜትር ይደርሳል። የጨረቃ አጠቃላይ ዲያሜትር ደግሞ 3,540 ኪሎ ሜትር በመሆኑ፤ ይህ የመሬት ጥቁር ጥላ ጨረቃን ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው።
የጨረቃ ግርዶሾች መቼ ይከሰታሉ?
የጨረቃ ግርዶሽ ሊከሰት የሚችለውጨረቃ ሙሉ በምትሆንበት ጊዜ እና በምድራችን በቀጥታ ከፀሀይ ተቃራኒ አቅጣጫ በምትሆንበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ይህ ክስተት በየወሩ ማለትም በእያንዳንዱ ሙሉ ጨረቃ የሚከሰት አይለም። ምክንያቱም ፡ የጨረቃ ምህዋር በ5 ዲግሪ ከምድር ምህዋር ያዘነበለ በመሆኑ፤ ብዙውን ጊዜ ሙሉ ጨረቃ ከምድር ጥላ በላይ ወይም በታች ልታልፍ ትችላለች። ይሁን እንጂ ፀሀይ፣ ምድር እና ጨረቃ በአንድ ረድፍ ሆነው ጨረቃ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በምድር ጥላ ስር በመግባት እንዲህ እንደ ሰሞኑ ያለ የጨረቃ ግርዶሽ የሚፈጠርበት ጊዜ አለ።
በጨረቃ ግርዶሽ እና በፀሐይ ግርዶሽ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
ለመሆኑ በጨረቃ ግርዶሽ እና በፀሐይ ግርዶሽ መካከል ያለው ልዩነትምንድን ነው? በአጠቃላይ የፀሐይ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ የፀሐይን ብርሃን በመከለል በምድር ላይ ጥላ ስትጥል ነው። የጨረቃ ግርዶሽ የሚከሰተው ደግሞ ፤ምድር የፀሐይ ብርሃንን በመጋረድ እና በጨረቃ ላይ ጥላ ስትጥል ነው።የጨረቃ እና የፀሐይ ግርዶሾች በዓመት ሁለት ጊዜ በእኩል ድግግሞሽ ይከሰታሉ። ሁለቱም አስደናቂ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ግርዶሽን ለማየት ሀገር አቋርጠው ይጓዛሉ።ነገር ግን ሰዎች የጨረቃ ግርዶሾችን ሊያዩአቸው የሚችሉት በምሽት በመሆኑ የጨረቃ ግርዶሾች ዝቅተኛ የምዕናብ ደረጃ ያላቸው ሲሆን፤አብዛኛውን ጊዜ የፀሐይ ግርዶሽ ብዙ ሰዎችን ይስባሉ። ነገር ግን ፀሐይን በቀጥታ ማየት ስለማይቻል አጋዥ መነፅር ያስፈልጋል። የጨረቃ ግርዶሽን ግን እንዲሁ ማየት ይቻላል። በተጨማሪም ቀይ የጨረቃ ግርዶሽን ለ 65 ደቂቃዎች ማየት የሚቻል ሲሆን፤ አጠቃላይ ግርዶሹ ከአምስት እስከ ስድስት ሰዓታት ይቆያል። ይህምለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ከሚቆየው ከፀሀይ ግርዶሽ ጋር ሲነፃጸር የበለጠ ጊዜ ነው።
በግርዶሽ ወቅት ጨረቃ ለምን ቀይ ትሆናለች?
ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት በሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ወቅት ፤ጨረቃ በመሬት ሙሉ ጥላ ውስጥ ስታልፍ ደማቅ ቀይ ቀለም የምትይዝ ከሆነ ቀይ ጨረቃ " (Blood Moon) በመባል ይታወቃል።ይህ ደም መሳይ የጨረቃ ገጽታ የፀሐይ ብርሃን ከምድር ከባቢ አየር ጋር በመገናኘቱ የተከሰተ ነው።የፀሀይ ብርሀን ወደ ምድር ሲያርፍ ከባቢ አየር ብርሃንን በተለያዩ የሞገድ ርዝመቶች በታትኖ ያጣራል። በዚህም መሰረት እንደ ሰማያዊ ብርሃን ያሉ አጠር ያሉ የሞገድ ርዝመቶች ወደ ውጭ ይበታተናሉ። እንደ ቀይ ያሉ ረዣዥም ሞገዶች ደግሞ ወደ ምድር ጥላ ውስጥ ታጥፈው ይገባሉ።በሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ወቅት ጨረቃ «ኡምብራ» ተብሎ በሚጠራው የምድር ጥላ ውስጠኛ ክፍል ውስጥ ተሸፍናለች።ነገር ግን የተወሰነው የፀሀይ ብርሀን ክፍል አሁንም የምድርን ከባቢ አየር አልፎ ወደ ምድር ከባቢ አየር በመድረስ እንደ ቀይ እና ብርቱካናማ ያሉ ቀለማትን ይይዛሉ።እንደ ሰማያዊ እና ቫዮሌት ያሉ አጭር የሞገድ ርዝመቶች ያላቸው ሌሎች ቀለሞች የመበታተን አዝማሚያ ስለሚኖራቸው በምድር ከባቢ አየር ውስጥ የማለፍ ዕድላቸው አነስተኛ ነው። ቀይ እና ብርቱካንማ ብርሃን ግን ረጅም የሞገድ ርዝመት ስላላቸው በቀላሉ አይበታተኑም።
በሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ወቅት፤ ጨረቃ በምድር ጥላ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ ታዲያ፤ ይህ ቀይ ብርሃን የጨረቃ ገጽታ ላይ በማንፀባረቅ ለጨረቃ ደም የመሰለ ቀይ ገጽታን እንደሚያላብስ የስነፈለክ ተመራማሪው ገልፀዋል።
የናሳ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ደግሞ በአጠቃላይ በጨረቃ ግርዶሽ ወቅት የሚታየው ወርቃማ፣ ብርቱካንማ ወይም ቀይ ቀለም ክስተት በከባቢ አየር ውስጥ ባሚገኝ የአቧራ፣ ውሃ እና ሌሎች ቅንጣቶች መጠን ላይ የሚወሰን ነው። እንደ ናሳ ሊቃውንት እንደ ሙቀት እና እርጥበት ያሉ ሌሎች የከባቢ አየር ሁኔታዎችም በጨረቃ ግርዶሽ ወቅት በሚታየው የጨረቃ ገጽታ ላይ ተፅዕኖ አላቸው።በሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ወቅት ጨረቃ ቀይ ወይም ብርቱካናማ ቀለም ሲኖራት፤ በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ አቧራ እና ደመናንም ያሳያል።የግርዶሹ አተያይ ልዩነትም ከቦታ እና ከአቅጣጫ ጋር እንደሚያያዝ ዶክተር ሰለሞን ገልፀዋል።
የጨረቃ ግርዶሽ በየስንት ጊዜ ሊከሰት ይችላል?
የጨረቃ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ ሙሉ በምትሆንበት እና ፀሀይ፣ ምድር እና ጨረቃ በትይዩ ረድፍ በሚደረደሩበት ጊዜ ብቻ ነው። እንደ ሊቃውንቱ ገለፃ ጨረቃ ምድርን ለመዞር እና ከሙሉ ጨረቃ ወደ ሌላ ሙሉ ጨረቃነት የምታደርገው ዑደት 29 ተኩል ቀናትን ይፈጃል። ያም ሆኖ፤ የጨረቃ ግርዶሽ በየወሩ ሳይሆን በዓመት በአማካይ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የሚከሰተው።
ይህ መሰሉ ክስተት በጎርጎሪያኑ ያለፈው መጋቢት 14 ቀን 2025 የተከሰተ ሲሆን የጨረቃ ቀለም ብርቱካናማ ነበር።ለመጨረሻ ጊዜ ደም የመሰለች ጨረቃ የታየችው በጎርጎሪያኑ ህዳር 8 ቀን 2022 ዓ/ም ነበር።በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በእስያ እና በአውስትራሊያ በጎርጎሪያኑ መስከረም 7፣ 2025 ዓ/ም የተከሰተውን የሰሞኑን ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ የማየት እድል ላላገኙ፤ ከ2030 ዓ/ም በፊት ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽን ለማየት አራት እድሎች እንዳሉ የዘርፉ ሊቃውንት ተንብየዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ማን ተጋፍቶት ስለሺ