1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በቡሬ ወረዳ በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃት 3100 ሰዎች ወደ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ተፈናቀሉ

ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2016

​​​​​​​በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት የተፈናቀሉ ከሦስት ሺሕ በላይ ሰዎች በሖሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን መጠለላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ጥቅምት 30 ቀን 2016 በተፈመው ጥቃት አስራ አራት ሰዎች መገደላቸውን ከተፈናቃዮች አንዱ ገልጸዋል።

Karte Äthiopien Ethnien EN

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በተፈጸመ ግጭት ከሶስት ሺሕ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

This browser does not support the audio element.

በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ ባለፈው ሳምንት አርብ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃት የተፈናቀሉ  3,100 ሰዎች መመዝገባቸውን በአሙሩ ወረዳ ጆጅ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ የሖኑ አቶ ሲሳይ አበዋ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል። ያነጋገርናቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በመሸሽ በአሙሩ ወረዳ ጆጅ የሚባል ቀበሌ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

 በጥቃቱ የአስራ አራት  ሰዎች ህይወት ማለፉንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በሰው ህይወት ላይ ደርሷል ስተባለው  የጉዳት መጠን ከአካባቢው ባለስልጣናት ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በቡሬ ወረዳ በቆ ጣቦና ሶንቶም በሚባል ቀበሌ ከባለፈው ሳምንት ጥቅምት 30 ቀን 2016 ጀምሮ በተከተሰው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች መሸሻቸው ተገልጸዋል፡፡

የጥቃቱ መነሻና የደረሰ ጉዳት

በቡሬ ወረዳ በቆ ጣቦ ቀበሌ ነዋሪ መሆናቸውን የነገሩ አቶ ኢምሩ ሁንዴ  ባለፈው ሳምንት አርብ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአካባቢአቸው የደረሰውን ጥቃቱን በመሸሽ ባሁኑ ወቅት ከቡሬ ወረዳ አወሳኝ በሆነው ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ በቀበሌያቸው እህል በመጫን ላይ የነበሩ አርሶ አደሮችን በፋኖ ስም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች  ቀረጥ መክፍል አለባችሁ በማለት ተኩስ በመክፈት ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱም ከ10 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን  ገልጸዋል፡፡

አቶ ኢምሩ “በረሃ ውስጥ የሚሰሩ አርሶ አደሮች  በቆሉ ለመጫን ሄደው በቆ ጣቦ ላይ ቀረጥ መክፈል አለባችሁ በሚል ነው ተኩስ የከፈቱት፡፡ በጥቃቱ 12 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ሌሎች 14 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፈዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “ጥቃት ካደረሱ በኃላ ዝርፍያም  ፈጽመዋል፡፡  ምንም የተፈረ ንብረት የለም” የሚሉት አቶ እምሩ “ከበቆ ጣቦ ቀበሌና በቅርብ ርቀት ላይ በሚትገኘው ቁጭ ከተማ እንዲሁም ወደ ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩና በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ  በመሻገር ሀሮ ቀበሌና አዲስ ዓለም በሚባሉ ቦታዎች ላይ በመንቀሳቀስ ነው የተደራጀ ጥቃት የሚያደርሱት” በማለት አስረድተዋል።

ከቡሬ ወረዳ በቆ ጣቦ ቀበሌ ተፈናቅለው በአመሩ ወረዳ ጆጅ ቀበሌ በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ የነገሩን ነዋሪም በደረሰው ጥቃት አንድ የበተሰባቸው አባል ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡ በወረዳቸው በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ሲኖሩ እንደነበር የገለጹ ሲሆን  ባለፈው ሳምንት አርብ የደረሰው ጥቃት በመሸሽ  በጫካ ከ3 ቀን የእግር ጉዞ በኃላ ወደ አሙሩ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ቡሬ ወረዳ በተቀሰቀሰው ግጭት 7 ሰዎች መሞታቸውን ተሰማ

በጉዳዩ ላይ ከቡሬ ዙሪያ ወረዳ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘላዓለም ጋሹ ማብራሪያ ለማግኘት በስልክ ያደረኩት ጥርት አልተሳካም፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ በቡሬ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ስለደረሰው ጥቃት ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስና ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አመራር የሆኑት ኮማንደር ክንዴ ብርኔ ስለ ጉዳዩ መስማታቸውን፤ ነገር ግን  የተጣራ መረጃ እንደለላቸው ገልጸዋል፡፡

የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ጆጅ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሲሳይ አበዋ የተፈናቀሉ ሰዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም በየዕለቱ እጨመረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ባገረሸው ግጭት የተሰደዱ የአማራ ተወላጆች በጫካ ውስጥ ለችግር ተጋልጠዋል

አቶ ሲሳይ “የተፈናቀሉ ሰዎች ዛሬም እገቡ ነው፡፡ እስከ ዛሬው እለት 3100 ሰዎች ተመዝገበዋል፡፡ በጆጅ ቀበሌ 2 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው ሰዎች ተጠልለው የሚገኙት፡፡ ሶንቶማ ከሚባል ቀበሌ የተዘረፍ ንብረቶች በከፍል በሚሊሻ ሀይሎቸ ተይዘዋል፡፡ ለተፈናቀሉ ሰዎችም ከአጋምሳና ሌሎች ቦታዎች የዕለት ደራሽ ድጋፍም እየተሰባሰበ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ የፍኖ አባላት ሀሳብ ለማካተት በስልክ ያደረኩት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ እና ቡሬ  አዋሳኝ ስፍራዎች በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂዎች ጥቃት እንደሚደርሰ ሲገለጽ ቆይተዋል፡፡ ሁለቱን አካባቢዎች የሚያገናኙ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጠ ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆነም  ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW