1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባሕር ዳር “ከሕግ ውጪ” የተፈጸሙ ግድያዎች “የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ” አምነስቲ

Eshete Bekele
ሰኞ፣ የካቲት 18 2016

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት በባሕር ዳር እስከ “የጦር ወንጀል” ሊደርሱ የሚችሉ “ብርቱ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰቶች” መፈጸማቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምርመራ ይፋ አደረገ። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በአማራ ክልል ከሕግ አግባብ ውጭ የሚፈጸሙ ግድያዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አስተላልፏል

ባሕር ዳር ከተማ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ምርመራ በነሐሴ 2015 እና መስከረም 2016 በባሕር ዳር ከተማ አስራ ሁለት ሰዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሕግ ውጪ መገደላቸውን ይፋ አድርጓል። ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

በባሕር ዳር “ከሕግ ውጪ” የተፈጸሙ ግድያዎች “የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ” አምነስቲ ኢንተርናሽናል

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት በባሕር ዳር ከተማ እስከ “የጦር ወንጀል” ሊደርሱ የሚችሉ “ብርቱ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰቶች” መፈጸማቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ውጤት ይፋ አደረገ።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በሁለት የተለያዩ ወቅቶች የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአማራ ክልል ዋና ከተማ በትንሹ ዐሥራ ሁለት ሰዎች “ከሕግ ውጪ” መግደላቸውን የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ዛሬ ሰኞ የካቲት 18 ቀን፣ 2016 ይፋ አድርጓል።

“ከእኛ ጋር ሳይሆን ሊፋለሟቸው ከመጡት አካላት ጋር የሚዋጉ መስሎን ነበር”

በመስከረም 2016 እና ነሐሴ 2015 ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችን የሠነደው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ውጤት “ከእኛ ጋር ሳይሆን ሊፋለሟቸው ከመጡት አካላት ጋር የሚዋጉ መስሎን ነበር” የሚል ርዕስ የተሰጠው ነው።

የድርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ጽህፈት ቤት ባልደረባ ሱዓድ ኑር “ይኸ ርዕስ የ20 ዓመት ወንድ ልጇ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ጭንቅላቱ ላይ ተመትቶ ከተገደለባት ለምለም ከተባለች እናት የወሰድንው ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ሱዓድ ኑር “እነዚህ ቃላት ከእርሷ ምስክርነት የተወሰዱ፣ ለዚህ ምርመራ ባነጋገርናቸው እና የማያውቁት ጦርነት ሰለባ የሆኑ በርካታ እማኞች የተደጋገሙ ናቸው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። 

በአምነስቲ የምርመራው ውጤት መሠረት ነሐሴ 2 ቀን፣ 2015 በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 ውስጥ በሚገኙት አቡነ ሀራ እና ልደታ የተባሉ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት “ከሕግ ውጪ” ከተገደሉ ስድስት ሰላማዊ ሰዎች መካከል ወይዘሮ ይታጠቁ አያሌው ይገኙበታል።

ከልደታ አቅራቢያ በሚገኝ የመኖሪያ ቤታቸው እንጀራ በመጋገር ላይ የነበሩት ይታጠቁ ወታደሮች ወደ ቅጥር ግቢያቸው በተኮሱት ጥይት ተመትተው መገደላቸውን ዘመዳቸው ቢኒያም የተባለ የዐይን እማኝ ለአምነስቲ አስረድቷል።

የባሕር ዳር ከተማ በነሐሴ 2015 የመጀመሪያ ሦስት ቀናት በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ብርቱ ግጭቶች አስተናግዳለች። ምስል Simon Montgomery/robertharding/picture alliance

በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የ55 ዓመቱ አዛውንት አየነው ደፍረሽ በተመሣሣይ ቀን ካሳሁን እና አብርሐም ከተባሉ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ከቤተ-ክርስቲያን በመመለስ ላይ ሳሉ እንደተገደሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ውጤት ያሳያል።

አንድ የጥይት ድምፅ የሰማ የቤተሰቡ አባል ለአቶ አየነው ስልክ ደወሎ ለማናገር ሲሞክር የመከላከያ ሰራዊት ወታደር ሳይሆን አይቀርም ብሎ የጠረጠረው አንድ ግለሰብ ስልኩን አንስቶ “የደረሰው አደጋ ትንሽ ነው” ብሎ እንደመለሰለት ለመርማሪዎቹ ተናግሯል።

የአየነው የቤተሰብ አባላት በስተመጨረሻ ሦስቱን አስከሬኖች ከጎዳና እንዳነሱ ሪፖርቱ ይጠቁማል። የዐይን እማኞች እና ቤተሰቦች እንደተናገሩት ሁሉም ሟቾች “ከቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት” መገደላቸውን ይኸው የምርመራ ውጤት አትቷል።

ግድያው በተፈጸመበት የነሐሴ ወር የመጀመሪያ ሦስት ቀናት የባሕር ዳር ከተማ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ብርቱ ውጊያ አስተናግዳለች። በባሕር ዳር በመከላከያ ሠራዊት “ከሕግ ውጪ” ተፈጸመ የተባለው ግድያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለይ በአማራ ክልል ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በደነገገ በጥቂት ቀናት ልዩነት የተከሰተ ነው።

በባሕር ዳር ዳግም ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት ሰባት አሚት በተባለ የከተማዋ ክፍል መስከረም 29 እና 30 ቀን፣ 2016 አምስት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት መገደላቸውን የአምነስቲ ምርመራ ይፋ አድርጓል። የምርመራው ውጤት እንደሚያሳየው ከሟቾቹ መካከል “በጤና ጣቢያ ውስጥ ከሕግ ውጪ የተገደለ ታካሚ ይገኝበታል።”

መስከረም 30 ቀን፣ 2016 ታደሰ መኮንን ወደተባሉ የ69 ዓመት አረጋዊ ቤት የገቡ ወታደሮች “ሦስት ወንድማማቾችን እና አንድ ጎረቤታቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ” መግደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በዚሁ የምርመራ ውጤት አስፍሯል። ጥቃቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ እና ለወታደሮቹ በር እንደከፈቱ የገለጹ የዐይን እማኝ “ወታደሮቹ ወንድ የቤተሰብ አባላትን በመለየት ከግቢው እንዳስወጧቸው” ለአምነስቲ ተናግረዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በአማራ ክልል ከሕግ አግባብ ውጭ የሚፈጸሙ ግድያዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አስተላልፏል

“ወታደሮቹ ሰዎቹን በዱላ እየደበደቡ ከግቢ ካስወጧቸው በኋላ ከመካከላቸው አንደኛው ወታደር ስልክ ካናገረ በኋላ ‘ማንንም እንዳትምሩ፣ ሁሉንም ግደሏቸው’ ሲል እንደሰሙት” አቶ ካሳ የተባሉት የዐይን እማኝ ተናግረዋል። እኚሁ የዐይን እማኝ እንዳሉት ወታደሮቹ በመከልከላቸው የሟቾች አስከሬን ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ቀኑ 10 ሰዓት መንገድ ላይ ቆይቷል። ቤተሰቦች የሟቾችን አስከሬን በደብራቸው ለመቅበር በመስጋታቸው ራቅ ወዳለ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ መቅበራቸውን አቶ ካሳ እንደተናገሩ አምነስቲ አስፍሯል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በምርመራው ውጤት የተሠነዱ “ብርቱ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰቶች እስከ የጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ናቸው” ብሏል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የአፍሪቃ ቀንድ ጽህፈት ቤት ባልደረባ ሱዓድ ኑር “በዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ በሕመም ወይም በጉዳት ከአውደ ውጊያ ውጪ የሆኑ ተዋጊዎችን ጨምሮ በግጭት ውስጥ በቀጥታ የማይሳተፉ ሰዎች መግደል የጦር ወንጀል ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሱዓድ “ከዚህ በተጨማሪ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች ሕይወትን በዘፈቀደ የመንጠቅ እና በዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ ጥበቃ የተሰጠው በሕይወት የመኖር መብት ጥሰት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይኸን ምርመራ ሲያጠናቅር ከዐይን እማኞች፣ የሰለቦች የቤተሰብ አባላት፣ ከጤና ባለሞያዎች፣ ከማኅበረሰብ እና ከሐይማኖት መሪዎች ጋር 32 ቃለ-መጠይቆች እንዳከናወነ ሱዓድ ኑር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወዲህ በአማራ ክልል ላለፉት ሰባት ገደማ ወራት ከፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ የገጠመው መከላከያ ሠራዊት በሰላማዊ ሰዎች ግድያ ሲወነጀል የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት በባሕር ዳር ከተማ “ከሕግ ውጪ” የፈጸሟቸው ግድያዎች “የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ” ብሏል። ምስል Solomon Muchie/DW

በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ ዞኖች በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል። ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ግን “ሕዝብ ላይ ድሮን አይተኮስም” ሲሉ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚቀርበውን ክስ ባለፈው ታኅሣስ አስተባብለው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ጥር 20 ቀን፣ 2016 በሰሜን ጎጃም ዞን በምትገኘው መርዓዊ ከተማ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ከተደረገ ውጊያ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች “ከሕግ ውጪ” ገድለዋል መባሉን አልተቀበለም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመርዓዊ “ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ‘ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል’ በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን” እንዳረጋገጠ ይፋ አድርጓል። የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ግን “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ማስተባበያ ሰጥተዋል።

ዶይቼ ቬለ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ውጤት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት እና ከመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣናት በኢሜይል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የኢትዮጵያ መንግሥትን ምላሽ ለማካተት ወደ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ እና የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ስልኮች ዶይቼ ቬለ ዛሬ ሰኞ ቢደውልም ምላሽ አላገኘም።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ የሆኑት ሱዓድ ኑር ምርመራው ሲከናወን ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው እማኞች የጥቃት ፈጻሚዎቹን ማንነት በአግባቡ መለየታቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

“አብዛኞቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ውጊያ ከመቀስቀሱ በፊት ለሦስት ወራት በባሕር ዳር ይገኙ እንደነበር እና የደንብ ልብሳቸውን ለይተው እንደሚያውቁ ተናግረዋል” ያሉት ሱዓድ ኑር “ከዚህ በተጨማሪ አብዛኞቹ ያነጋገርናቸው ሰዎች በአድማ በታኞች፣ የከተማዋ ፖሊሶች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ያለውን ልዩነት ከግጭቱ በፊት እንደሚያውቁ ገልጸዋል” በማለት አስረድተዋል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የሰለቦችን ቤተሰቦች ‘የጦር መሣሪያ አምጡ’ ‘ፋኖን ትደግፋላችሁ ወይ?’ እያሉ ይጠይቁ እንደነበር ተናግረዋል” ሲሉ የአምነስቲ ባልደረባ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በባሕር ዳር ተፈጽሟል የተባለው ግድያ የምርመራ ውጤት ይፋ የሆነው ከአራት ወራት በላይ ዘግይቶ ነው። ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃንን ጨምሮ ደም አፋሳሽ ውጊያዎች በተደረገባቸው የክልሉ ከተሞች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን በጥልቀት አልተመረመረም።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ የሆኑት ሱዓድ “የኢንተርኔት አገልግሎት በመዘጋቱ እና የስልክ ግንኙነት በከፊል በመገደቡ በአማራ ክልል ያለው ግጭት በሰብአዊ መብቶች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ይፋ ለመውጣት ዘግይቷል” ሲሉ ተናግረዋል። “ከጥቃት የተረፉ ሰዎች እና የዐይን እማኞች ባለባቸው የበቀል ሥጋት ሳቢያ” ግጭቱ ያስከተለውን ሰብአዊ ጉዳት መመርመር “በጣም ፈታኝ” እንደሆነም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል በግጭት በሚናጥበት ወቅት ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ይልቃል ከፋለ ተነስተው በአረጋ ከበደ ተተክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በክልሎች የሚታዘዙ የልዩ ኃይሎች አባላትን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች ለማስገባት ውሳኔ ሲያስተላልፍ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ቀውስ ዐሥራ አንደኛ ወሩን ሊደፍን ሲንደረደር እስካሁን ይኸ ነው የሚባል መፍትሔ አልተገኘም። ክልሉ በግጭት እየተናጠ ርዕሰ-መስተዳድር የነበሩት ይልቃል ከፋለ ተነስተው በአቶ አረጋ ከበደ ተተክተዋል።

አዲስ የተሾሙ የክልሉ ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ እና የፌዴራል መንግሥት ሹማምንት በተለያዩ ከተሞች ከአማራ ክልል ነዋሪዎች ውይይት ቢያደርጉም እስካሁን በተጨባጭ ግጭቱን አላቆሙም።

ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የማኅረሰብ ተወካዮች ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ለውይይት የጋበዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከግጭቱ ጀርባ “የውጭ” ኃይሎች እጅ አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቆም አድርገዋል። መንግሥት እና ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሣምንት በተሰራጨው ውይይት በእርግጥ መንግሥታቸው ግጭቱን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጧል።

“በየሠፈሩ አምጡና አወያዩ” ያሉት ዐቢይ “ይቅርታ ብለን፤ ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን እንታረቅ፣ እንስማማ” ብለው ነበር። “ሰላም ነው የምንፈልገው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንደዚያ ካላደረገ አማራ ለጥቃት ይጋለጣል” የሚል ማስጠንቀቂያ ጣል አድርገዋል። ዐቢይ “እንታረቅ” ቢሉም በቀጥታ ነፍጥ አንስተው መንግሥታቸውን ከሚዋጉ የፋኖ ታጣቂዎች ለመደራደር ፈቃደኛ ስለመሆናቸው ያሉት ነገር የለም።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን በተደረገ የሰላም ንግግር የተሳተፈችው አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፋኖ ታጣቂዎች ለመወያየት ፈቃደኛ ከሆነ ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን በአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑኳ አምባሳደር ማይክ ሐመር በኩል ዐስታውቃለች።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ባለፉት ወራት ወደ አዲስ አበባ ባደረጓቸው ጉዞዎች ካነገቧቸው ዓላማዎች አንዱ ለአማራ ክልል ቀውስ በንግግር መፍትሔ እንዲበጅ ግፊት ማሳደር ነበር። አምባሳደር ማይክ ሐመርም ሆኑ አዲስ አበባ የሚመላለሱ ዲፕሎማቶች የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት በአፈ-ሙዝ ሊፈታ አይችልም የሚል ዕምነት አላቸው።

ከአማራ ክልል የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት “በየሠፈሩ አምጡና አወያዩ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ይቅርታ ብለን፤ ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን እንታረቅ፣ እንስማማ” ሲሉ ተደምጠዋል። ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ለአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ደርሰው ሲመለሱ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ዐቢይ ቀውሶቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የገቡትን ቃል ማክበር እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የገጠሟትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል” ያሉት ሞሊ ፊ “በዚያ ቁርጠኝነታቸው ላይ ተግባራዊ ርምጃ እንዲወስዱ እናበረታታቸዋለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ለደፈጣ እና የወንጀል ጥቃቶች የፀጥታ አስከባሪዎች ምላሽ በሚሰጡበት መንገድ ላይ የተሰማንን ሥጋት በአደባባይ እና በግል ገልጸናል” ያሉት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ “የተወሳሰበ የፀጥታ ፈተና እንደሆነ ዕናውቃለን። ቢሆንም የሰላማዊ ሰዎችን መብቶች ለመጠበቅ የበለጠ ሥራ መሠራት አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ባለፉት ወራት ወደ አዲስ አበባ ሲመላለሱ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የበረታው ግጭት በውይይት እንዲፈታ ግፊት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቆ ነበር። ምስል Facebook

በባሕር ዳር ከተማ እና በአጠቃላይ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት “ገለልተኛ ውጤታማ ምርመራ” ሊጀምር እንደሚገባ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪቃ ቀጠና ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታሕ ጥሪ አቅርበዋል። “በቂ ማስረጃ ባለበት ጥሰት በመፈጸም የተጠረጠሩ ዓለም አቀፍ የፍትኃዊ ዳኝነት መስፈርቶች ባሟሉ ችሎቶች ሊከሰሱ ይገባል” ያሉት ቲገረ ቻጉታሕ ቅጣቱ የሞት ፍርድ ሊጨምር እንደማይገባ አሳስበዋል።

እንዲህ አይነት ጥሪዎች ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉት የአሜሪካ፣ የብሪታኒያ እና የካናዳ ኤምባሲዎች ቢቀርቡም ከኢትዮጵያ መንግሥት ወገን አዎንታዊ ተቀባይነት አላገኙም።

የአምነስቲዋ ሱዓድ ኑር “በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ተብለው የተለዩ ወንጀሎች የሚፈጽሙ አጥፊዎችን የሚያደፋፍር እና ሁሉንም ኅብረተሰብ ለአደጋ የሚያጋልጥ ስልታዊ የተጠያቂነት እጦት አለ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“እንዳለመታደል ሆኖ ለእነዚህ እና ትግራይን ጨምሮ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ይፋ ላደረጋቸው ወንጀሎች ተዓማኒ ፍትኅ እና ተጠያቂነት ከሌለ ሰላማዊ ሰዎች የጥቃት ዒላማ መሆናቸው ይቀጥላል፤ ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ መብቶቻቸው በዚህ ግጭት አሉታዊ ተጽዕኖ እየደረሰበት ይቀጥላል” ሲሉ ሱዓድ አስጠንቅቀዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ካበቃ ከአንድ ዓመት በኋላም በሌላ የትጥቅ ግጭት የመከላከያ ሠራዊት “ወታደሮች ሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋት መጣሳቸውን ቀጥለዋል” ሲል ተችቷል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትን ጨምሮ የኢትዮጵያ አጋሮች ምርመራ ለመጀመር “አፋጣኝ ርምጃ” መውሰድ እንደሚገባቸውም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቅርቧል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW