በባሕር ዳር ከተማ የሰዓት እላፊ ገደብ በከፊል መነሳት
ዓርብ፣ ሐምሌ 11 2017
በባሕር ዳር ከተማ የሰዓት ገደብ በከፊል መነሳት
ከፀጥታ ጋር በተያያዘ በባሕር ዳር ከተማ የሰዓት ገደብ ተጥሎባቸው የነበሩ አንዳንድ የእንቅስቃሴና የንግድ ሥራዎች እገዳው እንደተነሳላቸው የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው እንቅስቃሴዎቹ ቀድሞውንም ቢሆን የቆሙት በነበረው የእንቅስቃሴ ገደቡ ብቻ ሳይሆን ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ህብርተሰቡ ራሱ ከምሽት እንቅስቃሴ በመታቀቡ ነው ብለዋል፡፡በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ
ባል 4 እግር ተሽከርካሪዎች 24 ሰዓት እንዲንቀሳቅሱ ተፈቅዷል” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ
በአማራ ክልል ካለፉት 2 ዓመታት ጀምሮ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካክል በተፈጠርው ጦርነት ምክንያት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እክል ገጥሟቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በክልሉ አንዳንድ ከተሞች የምሽት እንቅስቃሴዎች የሰዓት ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ የሰዓት ገደብ ተጥሎባቸው ከነበሩ ከተሞች መካከል ባሕር ዳር ከተማ አንዷ ስትሆን፣ ከትናንት ጀምሮ ገደቡ በከፊል ተነስቶላታል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዛሬ በተለይ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት በከተማዋ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ለአንድ ዓምት ያክል የምሽት እንቅስቃሴ ክልከላ በከተማዋ ተጥሎ ቆይቷል፣ ባለ 4 እግር ተሽከርካሪዎችና የንግድ እንቅስቃሴ ሥራዎች ከትናንት ጀምሮ እገዳው እንዲንሳላቸው የከተማዋ አስተዳደርና ፀጥታ ምክር ቤት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ የሠዎች የሰዓት ገደብ እንቅስቃሴም እንዲሁ መነሳቱን ኮማንደር ዋለልኝ ገልጠዋል፡፡
“አሁን ባለው ሁኔታ የከተማዋ ፀጥታ በአንፃራዊነት ሠላም ነው፣ በዚህም ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ምክር ቤት ተሰብስቦ የ24 ሰዓት የእግረኛና የባለ አራት እገር ተሽከርካሪ እግዳውን አንስቷል” ብለዋል፡፡ ባለሁለት እግር ሞተር በስክሌቶች አሁንም የ24 ስዓትየእንቅስቃሴ ገደብ እንዳልተነሳ ያብራሩት ኃላፊው፣ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ደግሞ የምሽት እንቅስቃሴያቸው እንዳልተነሳ ገልጠዋል፡፡ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም ለ24 ሰዓት ክፍት ሆነው እንዲሰሩ መወሰኑንም አመልክተዋል።
የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት ዕላፊ ገደብና የዕለቱ እንቅስቃሴ
“የመኪናዎች የሰዓት ገደብ መነሳቱ ለታካሚዎች መልካም ዜና ነው” አስተያየት ሰጪዎች
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በተለይ የመኪኖች እንቅስቃሴ ገድብ መነሳቱ ታምመው ወደ ህክምና ተቋማት ለሚሄዱ ሠዎች መልካም ዜና ቢሆንም በከተማው ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ግን አሁንም አስተማማኝ ነው ማለት እንደማይቻል አንድ ድምፃቸው እንዲቅየር የፈለጉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ በዋናነት ነዋሪውን እንዳይንቀሳቀስ ያደረገው ያለው የፀጥታ ችግር እንጂ ክልከላው አይደለምም ብለዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ካለው የፀጥታ ችግር አኳያ የመንደርመተላልፊያ መንገዶቹንና የመኖሪያ ቤቶች አካባቢዎችን በብረት አጥሮ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በርካታ ባለሀብቶችም ያለውን የፀጥታ ችግር በመፍራት ከተማዋን እየለቀቁ ሥራቸውን በወኪል እንደሚያሰሩ አስረድተዋል፡፡
የምሽት የሰዓት ገደቡ በባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ አለመነሳቱ ተቀጥረው በሚሰሩትም ሆነ በባለንብረቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር እንደሚያስከትልባችው አንድ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች የሥራ ጊዜያቸው ምሽት በመሆኑ ጉዳቱ ያይልባቸዋል ነው ያሉት፡፡
“ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ሥራ አለመጀመር ብዙ ችግሮችን አስከትሏል” ተጠቃሚዎች
በባለሁለት እግር ተሽከርካሪ እየተዞዟሩ የሰሩ የነበሩ አስተያይት ሰጪ፣ የሞተር እንቅስቃሴው እስከነአካቴው በመቆሙ በተፈለገው ፍጥነት ሥራ እየሰሩ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ከባለቤታቸው ጋር ወደ ሥራ ከዚህ በፊት በሞተር ብስክሌት ይመላለሱ እንደነበር የነገሩን ሌላ አስተያየት ሰጪ፣ አሁን ታክሲን እንደአማራጭ ቢወስዱም ለወጪ መዳረጋቸውንና በሰዓትም ቢሮ መድረስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡በባህርዳር የሰዓት እላፊ ተነሳ
አስተያየት ሰጪው አክለውም ሞተር ብስክሌቶቹ ሥራ በማቆማቸው፣ በሞተር ብስክሌት ጥገና ላይ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ወጣቶችም ሥራ አጥ ሆነዋል ብለዋል፡፡ የሞተር ብስክሌቶቹና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች የሰዓት ጊዜ ገደብ ለምን እንዳልተነሳ የጠየቅናቸው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ፣ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት አልፈለጉም፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ