1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባቢሌ ስርዓተ አምልኮ ተከልክለናል ያሉ የዋቀፈና ሃማኖት ተከታዮች

ሐሙስ፣ ሰኔ 27 2016

በኢትዮጵያ በሃይማኖት ተቋሚነት ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው የዋቀፈና ሃይማኖት ተቋም የመረጃና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ በዪ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ የሃማኖቱ ተከታዮች ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኋላ ነበር፡፡

Babile Elephant sanctuary Park
ምስል Mesay Teklu/DW

በባቢሌ ስርዓተ አምልኮ ተከልክለናል ያሉ የዋቀፈና ሃማኖት ተከታዮች

This browser does not support the audio element.

የዋቀፈና ሃይማኖት ተከታዮች ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በምስረቅ ሀራርጌ ዞን ባቢሌ ከተማ  ውስጥ በሚገኘው የሃይማኖቱ የማምለኪያ ቦታ በአምልኮ ስርዓታቸው ላይ እያሉ 79 የሃማኖቱ ተከታዮች በጸጥታ አካላት መታሰራቸውን ተከትሎ የሃይማኖት ተቋሙ ቅሬታ አሰምቶ ነበር፡፡ የዋቀፈና ሃይማኖት ተቋም የመረጃና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ በዪ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየታቸው፤ በእለቱ ከታሰሩት የሃይማኖቱ ተከታዮች መካከል በርካቶቹ ከአንድ ሳምንት እስራት በኋላ ብለቀቁም አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ ሀራርጌ ዞን ፖሊስ በበኩሉ በእለቱ የታሰሩት ግለሰቦች ከጸትታ ሁኔታ ስጋት ጋር ብሆንም ከተወሰኑት ውጪ አብዛኞቹ ተጣርቶ ተለቀዋል ይላል፡፡
በኢትዮጵያ በሃይማኖት ተቋሚነት ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው የዋቀፈና ሃይማኖት ተቋም የመረጃና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ በዪ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ የሃማኖቱ ተከታዮች ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኋላ ነበር፡፡  “ለግማሽ ዓመት የሃይማኖቱ ተከታዮች ስብሰባ በምሥራቅ ሀራርጌ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች አመራሮች እና የአከባቢው የሃይማኖቱ ተከታዮች ባጠቃላይም 82 ሰዎች ገደማ ስለሃማኖቱ ለመምከር በተሰበሰቡበት ነበር እስራቱ የተከሰተው፡፡ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በዚሁ በስርዓተ አምልኮ ላይ በነበሩበት ነው ምንም ሳይባል የታጠቀ የመንግስት ሃይል ገብቶ 54 የሚሆኑ የአከባቢው ተወላጆችን ለይተው ወደ ካምፕ ስወስዷቸው፤ ቀሪውን 25 ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ የእምነቱ ተከታይና አመራሮች ደግሞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስሯቸው ነበር፡፡

በዚህም ለጸጥታው ሁኔታ ሰግተን ነው በሚል ከፖለቲካ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል፡፡ በማግስቱ ግን ከዞኑ የመጡ የአቃቤ ህግ እና የወንጀል መከላከል ባለሙያዎች ምርመራ አካህደው ሊያሳስራቸው የሚችል ምንም ማስረጃ እንዳልተገኘባቸው አረጋግጠው ብሄዱም ሳምንት ያህል ያለምንም ጥያቄ አስሮአቸው ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓርብ ለቀቁዋቸው” ነው ያሉት፡፡ ቃል አቀባዩ ከነዚህ 79 ሰዎች በተጨማሪ የታሰሩትን ለመጠየቅ የሄዱም 3 ሰዎች ተጨምረው ታስረው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ከሳምንት በኋላ ከእስር የተለቀቁት የሃይማኖቱ ተከታዮች ከእስር በተለቀቁበት ኣርብ ሰኔ 21 ለመደበኛ የአምልኮ ስርዓት ወደ ስፍራው ብያቀኑም ከሌሊቱ 5 ሰኣት የጸጥታ ሃይሎች ከቦታው እንዲበተኑ እንዳረጉዋቸው ገልጸዋል፡፡ 

ፎቶ ከማኅደር፦ የባቢሌ መልክዓ ምድር በከፊል ምስል Mesay Teklu/DW

“በዚያው እለት እነሱ ተፈተናል ብለው ወደ ማምለኪያው በአዳራሽ ስገቡ ከምሽት 5 ሰዓት አከባቢ ለምን ወደዚህ ተመለሳችሁ በሚል ከከተማው ውጪ የመጡት ወደየአከባቢያቸው እንዲሄዱ የዚያው አከባቢ ተወላጆችም ወደየቀዬያቸው እንዲሄዱ በማድረግ 10 ሰዎችን መርጠው ወደ እስር መለሱአቸው፡፡ ከወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ ጠይቀን ምክንያቱን ለመረዳት ብንሞክርም ሃይማኖቱ ላይ ግፊትና ጥላቻ ከማድረግ ውጪ ምንም የተገኘባቸው ተጨባጭ ነገር አለመኖሩን ተረድተናል፡፡ እዚህ ማምለክ አትችሉም በሚል ከዚህ በፊት ቤት ያከራየንን ሰውም ሲያስፈራሩ ነበር፡፡  አሁንም ድረስ ያልተለቀቁ ስድሰት ሰዎች እስር ላይ ናቸው፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቅ አስቀድማችሁ የጸጽታ መዋቅርን አላሳወቃችሁም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠን፡፡ ከዚ በኋላም ግን ኣርብ ምሽትና እሁድ ቀን ላይ ያለውን መደበኛ መርሃግብራችን እንዳናካህድ ተደርገን አሁንም ድረስ ማስፈራሪያ መኖሩን ከአከባቢው የሃማኖቱ ተከታዮች መረጃ ይደርሰናል” ስሉም አስረድተዋል፡፡

በእለቱ ከታሰሩት መካከል አንዱ መሆናቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሃማኖቱ ተከታይም፤ “በባቢሌ የዋቀፈና እምነት ማዕከል በተደረገልን ጥሪ መሰረት ከሌላ ወረዳ እንደ ሃይማኖቱ አመራር ወደዚያው አቅንተን ነበር፡፡ በዚያው በግማሽ ዓመቱ ውይይት ላይ ሳለን ነበር የጸጥታ አካል መጥቶ የተቆጣጠረን፡፡ ከዚያን አዳዲስ ፊቶች አሉ፤ ሰው በዛ እያሉ አሰሩን፡፡ የተለያዩ ማስፈራሪያም ደርሶብን 25 የምንሆነውን ለይተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱንና አሰሩን፡፡ ከዚያን የተለያዩ ምርመራዎችን አካህደውብን ከ8 ቀን በኋላ ፈቱን፡፡ ከዚያን እለቱ ኣርብ መደበኛ ስርዓተ አምልኮ ስለነበር ወደ አራዳሹ ገብተን ሳለ ከምሽቱ 5 ሰኣት መጥተው የአከባቢው ተወላጆች ወደ ቀዬያቸው እንዲገቡና እኛ ደግሞ በዚያ ውድቅት ለሊት ከተማውን ለቀን እድንወጣ አዘዙን” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች “ፍቃድ ሳይጠይቁ ሳያሳውቁ በመሰብሰባቸው ነው” ያሉን የምስራቅ ሀራርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መከላከልና ፍትህ አሰጣጥ ኃላፊ ኦላና ኦብሳ በተቋቋመ ኮሚቴ በኩል የታሰሩትን ሰዎች በመመርመር መልቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ “ያለ ወረዳውና ዞን እውቅና እነዚያ ሰዎች በዚያ መሰባሰባቸው ስህተት ነው ብለን ሰዎቹ እንዲሰባሰቡ ያደረጉትን ብቻ መጠየቅ ተገቢ ነው ካልን ውጪ ሌሎቹ እንዲፈቱ ሆኗል፡፡ ይህ በወረዳውም ሆነ በዞን አመራር ሃይማኖት ላይ ጫና ለማድረስ ሳይሆን አሁን ካለው አገራዊ የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ምናልባት ሁከት የሚፈጥሩ የሚገኙበት ከሆነ ብለን ነው የማጣራት ስራውን የከወነው፡፡ አሁን በቀሪው ያልተፈቱ ሰዎች ጉዳይም እልባት እንዲያገኝ ደብዳቤ ጽፈናል” ነው ያሉት፡፡
የሃይማኖቱ ተከታዮች በስፍራው ሄደን እዳናመልክ ተከልክለናል የሚለውን በተመለከተም ኢንስፔክተር ኦላና “እኛ ጸጥታን ከማስከበር ውጪ የመፍቀድም ሆነ የመከልከል ሃላፊነት የለንም” በማለት የሃይማኖቱ ተከታዮች ስርዓተ አምልኮአቸውን እንደማይከለከሉ አስረድተዋል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW