በብሪታንያ ቀኝ ጽንፈኞች ያቀጣጠሉት ኹከትና ያሳደረው ተጽእኖ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7 2016በሰሜን ምዕራብ እንግሊዙ ሳውዝፖርት በተባለው ከተማ ውስጥ ሦስት ህጻናት በዳንስ ትምሕርት ላይ ሳሉ በስለት ተወግተው ከተገደሉና ሌሎች ከቆሰሉ በኋላ በብሪታንያ የተቀሰቀሰው ኹከት አሁንም አልበረደም። ነፍሰ ገዳዩ እዚያው ብሪታንያ ካርዲፍ ዌልስ በተባለችው የወደብ ከተማ ከሩዋንዳውያን የተወለደ አክስል ሩዳኩባና የተባለ የ17 ዓመት ወጣት ሆኖ ሳለ ቀኝ ጽንፈኞች ግለሰቡ በጀልባ ብሪታንያ የገባ ሙስሊም ስደተኛ ነው ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሰራጩት ሀሰተኛ መረጃ ነበር ኹከት የተቀሰቀሰው። በዚህ ብጥብጥ መስጊዶች የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች ፣መጠለያዎች ፣ሱቆች እና ሌሎችም ተቋማት የጥቃት ሰለባ ሆነዋል። በኹከቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ያረፉባቸው ሆቴሎች በእሳት ጋይተዋል፤የመንግሥት ህንጻዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ፖሊስ ጣቢያዎች ጭምብል ባጠለቁ ሰዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። የብሪታንያ መንግሥት ፖሊስ የነፍሰ ገዳዩን ማንንነት ይፋ እንዳያደርግ አግዶ ነበር ።ሆኖም ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ፕሮፌሰር ሮዛ ፍሪድማን ይህ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ቀኝ ጽንፈኞች ሁሌም በጠላትነት የሚፈርጇቸውን ሙስሊሞችን ለመወንጀል ይመቻቸው ነበር ብለዋል።
የብሪታንያ የጥንትና የአሁኖቹ ቀኝ ጽንፈኞች አብረው የልጁ ማንነት እንደተገለጸ ሕገ ወጥ የሚባል ስደተኛ እና ሙስሊምም ነው የሚል ወሬ በማኅበራዊ መገናና ብዙሀን ነዙ።ይህም ኹከቱን ሲያስነሳ ጎን ለጎን ደግሞ ፍራቻና ጥላቻን አጉልቶ አሳየ። በሙስሊሞች ና በስደተኞች ላያ ያነጣጠረው ይህ ጥቃት በሙስሊምና በውጭ ዜጎች ላይ ፍርሀት አሳድሯል። ብዙዎች ግጭቱ ታቅዶ የተፈጸመ ወይስ ድንገት ያለ እቅድ የተቀሰቀሰ ነው የሚል ጥያቄ ደጋግመው ያነሱ ነበር። ከሩዋንዳውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች በተወለደ በ17 ዓመት ወጣት በሦስት ህጻናት ላይ የተፈጸመው ግድያ በተለይ በዋነኛነት በሙስሊሞች ወዳነጣጠረ ኹከትና ጥቃት እንዴት ሊቀየር ቻለ የሚል ጥያቄም ማጫሩ አልቀረም። ከ40 ዓመታት በላይ ብሪታንያ የኖረው የለንደኑ ዘጋቢያችን ድልነሳ ጌታነህ ችግሩ ድንገት የፈነዳ ሳይሆን በፊትም ተዳፍኖ የኖረ ነው ብሏል።
ስለ ጥቃቱና አመጹ አስተያየታቸውን የሰጡት ተቃዋሚዎች ሁኔታዎች በፍጥነት መቀያየራቸውና መባባሳቸው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። በቅርቡ የቀኝ የጽንፈኞችን ኹከት በመቃወም በተካሄደ ሰልፍ ላይ ከተካፈሉት መካከል አቶል ቪንዳ የተባሉት እኚህ የሱቅ ባለቤት ይገኙበታል ። ብዙ ችግር ይደርስብኛል ብለው ባይጠብቁም ነገሮች ሊለዋወጡ ይችላሉ ብለው መስጋታቸው አልቀረም።
«ምንም ዓይነት ችግር ይደርሳል ብዬ አልጠብቅም። ሆኖም ነገሮች ሊለወጡ ይችላሉ። ይህ ጋጠወጥነትና በመንግሥትና በግለሰቦች ንብረት ላይ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ጥፋት ከነበረበት በጣም ከፍተኛ ደረጃ አሁን አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል። አስፈሪ ወቅት ነው።»
በሰልፉ ላይ« ስደተኞች እንኳን ደኅና መጣችሁ፤ ፋሹሽቶችን አባሩ» የሚል መፈክር ይዘው የወጡት እኚህ ተቃዋሚ ደግሞ «እንደሚመስለኝ እዚህ የመምጣታችን ዋነኛው ምክንያት ንዴትና ብስጭት ነው። በመሠረቱ የዚህ ሁሉ ብስጭት ምክንያት ደግሞ አለማወቅ ነው። » ሌላው ደግሞ በግድያው ያልተሳተፉ ሰዎች ያለ አበሳቸው የጥቃት ሰለባ መሆናቸው አሳዝኗቸዋል።
«ሦስት ልጆች በሞታቸው እኛም ይሰማናል።ሆኖም በጉዳዩ ባልተሳተፉ ሰዎች ላይ መነሳቱ አስፈላጊ አልነበረም።»
ስደተኞችን በመቃወም በተቀጣጠለው አመጽ ለንደን ማንቼስተር ሊቨርፑል ብሪስቶል ሊድስ ኖቲንግሀም ፕላይማውዝ እና ቤልፋስትን በመሳሰሉ ከተሞች እንዲሁም በሚድልስብሮ በቦልተን እና በሮተርሃም ሱቆች ተዘርፈዋል፤ፖሊሶች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። በዚህ የተነሳም በርካታ የንግድ መደብሮች ተዘግተዋል።በሁኹከቱ የተጠረጠሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል። በአሁኑ ጊዜ ኹከቱን ለመቆጣጠር በመላ ሀገሪቱ ከ6ሺህ በላይ ፖሊሶች ተሰማርተዋል።
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ