1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በብር እና በዩዋን የመገበያየት ስምምነት

ሐሙስ፣ መስከረም 2 2017

ኢትዮጵያ ከቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ ጎን ለጎን 17 የመግባቢያ ሰነዶች ስለመፈራረሟ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። ከእነዚህ ስምምነቶች መካከል አንዱ ሁለቱ ሀገራት በየሀገሮቻቸው ገንዘብ መገበያየት የሚችሉበትን ስምምነት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ
ኢትዮጵያ ከቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ ጎን ለጎን 17 የመግባቢያ ሰነዶች ስለመፈራረሟ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።ምስል Yin Bogu/Xinhua/IMAGO

በብር እና በዩዋን የመገበያየት ስምምነት

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ከቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ ጎን ለጎን 17 የመግባቢያ ሰነዶች ስለመፈራረሟ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። ከእነዚህ ስምምነቶች መካከል አንዱ ሁለቱ ሀገራት በየሀገሮቻቸው ገንዘብ መገበያየት የሚችሉበትን ስምምነት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ማድረጓ በንግድና ግብይት ሂደት ውስጥ የሚገጥማትን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እጥረት ከማቃለል ባለፈ የቻይናኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖራቸው ብር ቀጥታ ወደ ኢንቨስትመንት እንደሰማሩ ሊያበረታታቸው ይችላል ሲሉ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ይህንን መሳዩን ስምምነት ከዚህ ቀደም ብሎ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋርም አድርጋለች።

ይመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ምንነትና ልምዱ

የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ሁለት ስምምነት ፈፃሚዎች ተመጣጣኝ የገንዘብ ምንዛሪዎችን በየሀገራቱ ገንዘብ የሚለዋወጡት አሠራር ሲሆን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በተለይም የአሜሪካ ዶላር ተጋላጭነትን የሚያስቀር ስለመሆኑ ይነገርለታል። ይህንን ስምምነት ሰሞኑን ኢትዮጵያ እና ቻይና ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና ከተፈራረሟቸው ሥምምነቶች መካከል በየሀገሮቻቸው ገንዘብ መገበያየት የሚችሉበት እንደሚገኙበት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስታውቀዋል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አሠራሩ ተስማሚ አካላት ተመጣጣኝ መጠን ያላቸውን ሁለት የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች የሚለዋወጡበት እና በኋላም በተወሰነ ቀን ገደብ ውስጥ ግብይት የሚፈጽሙበት መሆኑን የሚጠቅሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ የፋይናንስ ተቋማት አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ልውውጥ የሚያካሂዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የቻይና እና የአፍሪቃ ትብብር

የምንዛሪ ተመን መለዋወጥ ሥጋትን ለመከላከል፣ የምንዛሪ ወቅታዊ እንቅስቃሴን ለመገመት እና በዝቅተኛ ወለድ የውጭ ምንዛሪ ለመበደር ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ያሉት ባለሙያው ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰቷ እንዲጨምር ሊረዳት ይችላልም ብለዋል።

የገንዘብ ልውውጥ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ኩባንያዎች መካከል የተለመደ አሠራር መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው ቻይና ለንግድ ግብይቷ ዩዋንን በአሜሪካ ባንኮች በማስቀመጥ፣ በምትኩ ከአሜሪካ 100 ቢሊየን ዶላር ስለመግዛቷ አብራርተዋል።

ዘጠነኛው የቻይናና ዓፍሪካ የትብብር ጉባኤ በቤጂንግ

የኢትዮጵያ እና የቻይና ብሔራዊ ባንኮች ምን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ እና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚለዋወጡ በግልጽ የተባለ ነገር ባይኖርም ስምምነቱ ግን በተለይ ኢትዮጵያ የሚገጥማትን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እጥረት በሌላ መልክ በማቃለል ረገድ እንደሚያግዛት ይታመናል።

ኢትዮጵያ ከቻይና በተጨማሪ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር ከአንድ ወር በፊት መሰል ስምምነት ያደረገች ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ባንኮች የሦስት ቢሊዮን ድርሃም እና የ46 ቢሊዮን ብር ልውውጥ በማድረግ በየሀገራቱ ብሔራዊ ባንኮች ተቀማጭ እንዲሆንላቸው ተስማምተው ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW