በብድር አቅርቦት እጥረት የተፈተነው የቤት ልማት ዘርፍ
ሰኞ፣ ሰኔ 9 2017
በብድር አቅርቦት እጥረት የተፈተነው የቤት ልማት ዘርፍ
ቤት ገንቢ ድርጅቶች ከግል ባንኮች በቂ ብድር እያገኙ አለመሆኑ መሠረታዊ ችግር እንደሆነበት የኢትዮጵያ የሪል እስቴት አልሚዎች ማሕበር አስታወቀ። በዚህ ወቅት በግል ዘርፉ ያለው የቤት ግንባታ እና ግብይት መቀዛቀዝ የታየበት ሲሆን የቤቶች ዋጋ መናር ለዚህ ምክንያት መሆኑን ማሕበሩ ገልጿል። መንግሥት ለዚህ ዘርፍ መሬት በጨረታ ያቀርብ የነበረ ሲሆን በአዲስ አበባ እስከ 2500 ቤቶችን በአንድ ጊዜ መገንባት ለሚችሉ ድርጅቶች "በድርድር" በማቅረብ ያለውን ከፍተኛ የቤት አቅርቦት ችግር ለማቃለል ማቀዱ ታውቋል።
ቤት ሳይገነቡ መሸጥ፣ በተባለው ጊዜ ቤቶችን ገንብቶ አለማስረከብ፣ የሕዝብን ገንዘብ ሰብስቦ ግንባታ አለመጀመር፣ በየጊዜው የመሸጫ ዋጋ መጨመር፣ ቤትን በውጭ ምንዛሪ አስልቶ በመሸጥ የሚወቀሰው ይህ ዘርፍ በብድር አቅርቦት እና በግንባታ መሬት እጦት መፈተኑ ይነገራል። የሪል እስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ምን ይዞ መጣ?
መንግሥት ከሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማር በግል የቤት ልማት ዘርፍ ዋና ዋና የሚበሉ ከ100 እስከ 150 የማይበልጡ የቤት አልሚዎች መኖራቸውን ከተቋቋመ ሁለት ወራት የሆኑት የኢትዮጵያ የሪል 'ስቴት አልሚዎች ማሕበር ገልጿል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ከተማ እንደሚሉት የዘርፉ ገበያ የተመጣጠነ አይደለም።
"ገበያው አልተመጣጠነም። ቤት ፈላጊው በጣም ብዙ ነው፣ ቤት ገንቢው በጣም ትንሽ ነው"
የብድር አቅርቦት ዋናው የቤት ልማት ዘርፍ ችግር መሆኑ ይነሳል። 1000 ቤቶችን እየገነቡ መሆኑን የሚጠቅሱ አንድ የድርጅት ባለቤት በባንኮች ላይ ያነሱት ቅሬታ ለዚህ ማሳያ ነው።
"ከኤክስፖርት የበለጠ ነው ሪል ስቴት፤ ገቢው። ከማኑፋክቸሪንግ የበለጠ ነው ገቢው። ከዚያ በላይ ደግሞ ለዜጎች ነው ከፍተኛ ድጋፍ የምናደርገው። የግል ባንኮች ብድር አይሰጡም በፍፁም። የ11.5 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይዤ 2 ቢሊዮን ብር የሚያበድረኝ ባንክ አጥቻለሁ"። ብለዋል።
መንግሥት በገበያው ውስጥ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ገደብ ማድረጉ ለዚህ አንዱ ምክንያት መሆኑን አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የገንዘብ ሚኒስትሩ የ2018ን የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ሲያቀርቡ አንስተውት ነበር። ይህ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በሚል በመንግሥት የተወሰደው 'ርምጃ የቤቶች ልማት ዘርፍን "ከጨዋታ ውጪ" ማድረጉንም ገልፀው ነበር።
"የዋጋ ንረት በከፍተኛ ኹኔታ በመናሩ ምክንያት ባንኮች እንዳያበድሩ በማድረግ አጠቃላይ የገንዘብ እጥረት እንዲከሰት ተደርጎ አንዳንድ ሴክተሮች ከጨዋታ ውጪ ተደርገዋል። ሪል 'ስቴት ዘርፉን ማንሳት ይቻላል"።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ መንግሥት እንደከዚህ ቀደሙ ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ እንዳሻው መበደር እንደማይችል በመግለጽ የብድር አቅርቦቱ ከዚህ መነሻ የመጣ እንደሚሆን ገልፀዋ። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰፊ የቤት ግንባታ ይታያል። ሽያጩም ቢሆን ከፍተኛ ነበር። አሁን ግን በቤትም ሆነ በመገንቢያ ቦታ ላይ ጉልህ የግብይት መቀዛቀዝ ይታያል። ለምን? አቶ አለማየሁ ከተማ መልሰዋል።«አክሰስ ሪል ኢስቴት» በደል አደረሰብን ያሉ ወገኖች ጉዳይ፣
"ዋጋው ምክንያታዊ ከሆነ ሰው ይገዛል። ዋጋው ስለበዛ ሰው የመግዛት አቅሙ ይቀንሳል"
በግል ቤት ግንባታ ዘርፍ የሕዝብ ሀብት ከተሰበበበ በኋላ እንዲሁ ሲቀር፣ መካሰስና መዋቀስ ሲበዛ፣ ቤቶች ሳይገነቡ መሸጣቸው፣ ቤትን በተባለው ጊዜ ሰርቶ አለማስረከብ በዘርፉ ላይ አሉታዊ ምልከታ እንዲያዝ አድርጓል የሚለው ይህ ማሕበር የመሬት አቅርቦት ችግር መኖሩ ቢታወቅም አልሚዎች ከእጥፍ በላይ ያተርፋሉ የሚል ቅሬታ መኖሩን በተመለከተ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።
"አይመስለኝም። የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም"
መንግሥት በኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ 4.4 ሚሊዮን ቤት የመሥራት ዕቅድ ይዟል። 80 በመቶው በግል ዘርፍ የሚገነባ ነው ተብሏል። ይህ ማለት በየአመቱ 486 ሺህ ቤቶችን መገንባት ያፈልጋል። መንግሥት ይህንን ለማሳካት ከዚህ በፊት በምደባ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በጨረታ ለግል አልሚዎች ከሚያደርገው የመሬት አቅርቦት ሥርዐት በተጨማሪ በድርድር ለማቅረብ ወስኗል። የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ሞሼ ይህንኑ ይገልጻሉ። የለገጣፎ ሪል ስቴት መንደር ኑዋሪዎች ሙግት
"ባለሃብቱ በድርድር ከመንግሥት ጋር ከሚገነባቸው ቤቶች ከ25 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ለመካከለኛ ገቢ [ያለው] የህብረተሰብ ክፍል የሚያቀርብ ከሆነ መንግሥት ከጨረታ ውጪ መሬት በድርድር ያቀርባል"። የከተማ ልማት ባለሙያው አቶ ፀጋዬ ዝርዝር ዕቅዱንም ቅዳሜ ዕለት በተደረገ የዘርፉ ውይይት ላይ አስረድተዋል።
"እንደ ከተሞቹ ኹኔታ ታይቶ ከ 250 እስከ 2500 ቤት የሚሰሩ ባለሃብቶች አዲስ አበባ ከተማ ላይ በአንድ ጊዜ 2500 እና ከዚያ በላይ ቤት የሚገነባ በድርድር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መሬት ሊያገኝ ይችላል"። ከ 1 ዓመት ተኩል ወዲህ በቤት ሽያጭ ዋጋ ላይ ጭማሪ አለመደረጉን፣ ይልቁንም የአልሚዎች ወጪ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የሪል 'ስቴት አልሚዎች ማሕበር ገልጿል። ለዘላቂው መፍትሔ ግን ዘርፉን በብቸኝነት ሊደግፉ የሚችሉ የገንዘብ ተቋማት ሊኖር እንደሚገባም ተጠይቋል።
"አንደኛ ትልቁ የብረት ፋብሪካን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያቋቁም [መንግሥት]። ትልቁ ችግር የብረት ነው። ቀጥሎ ስሚንቶ ፋብሪካዎች ያንሳሉ"። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት በቀየሰው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት 900 ሺህ ተመዝጋቢ ቢኖሩም እስካሁን የቤት ባለቤት መሆን የቻሉት 360 ሺህ ያህሉ ናቸው።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ