1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ አደጋዎች፤ የአየር ንብረት ለውጥ

ማክሰኞ፣ መስከረም 8 2016

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤውን በዚህ ሳምንት ያካሂዳል። በጉባኤው ዋነኛ መነጋገሪያ ከሆኑት ርዕሰ ጉዳዮች ቀዳሚው የአየር ንብረት ቀውስ ነው። በተለያዩ ሃገራት የተፈጥሮ አደጋዎች መደጋገም የብዙዎች ስጋት ሆኗል። የተፈጥሮ አደጋዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ውጤቶች ወይስ የፈጣሪ ቁጣ መገለጫዎች? ተነጋገሩበት።

ፎቶ፤ ኒውዮርክ የተካሄደው ሰልፍ
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄድባት የአሜሪካኗ ኒውዮርክ ከተማ ከትናንት በስተያ እሑድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ የሚያስችል እርምጃ ባስቸኳይ እንዲወሰድ ለመጠየቅ ከ70 ሺህ በላይ የተገመተ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ድምፁን አሰምቷል። ፎቶ፤ ኒውዮርክ የተካሄደው ሰልፍምስል Eduardo Munoz/REUTERS

በተለያዩ ሃገራት የሚታየው የተፈጥሮ አደጋ የብዙዎች ስጋት ሆኗል።

This browser does not support the audio element.

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄድባት የአሜሪካኗ ኒውዮርክ ከተማ ከትናንት በስተያ እሑድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ የሚያስችል እርምጃ ባስቸኳይ እንዲወሰድ ለመጠየቅ ከ70 ሺህ በላይ የተገመተ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ድምፁን አሰምቷል። ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡት የሰልፉ ተሳታፊዎች ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ፌደራል መንግሥታት ለአየር ንብረት ለውጥ የሚታይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል። ኒውዮርክ ላይ ለሰልፍ ከወጡት አንዱ በተለይ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ያጋጠሙ የተፈጥሮ አደጋዎች በኅብረተሰቡ ላይ ያስከተሉትን ጉዳትን እና የከፋ ስጋት በማመልከት የሀገራቸው ፕሬዝደንት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

«ይኽ የበጋ ወቅት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የሙቀት መጠን የተመዘገበበት ወቅት ነው። በቅርቡ ሊቢያ ላይ የሆነውን ብንመለከት በ24 ሰዓታት ውስጥ በዘነበ 16 ኢንች ዝናብ 11 ሺህ ሰው ሞቷል፤ ጎርፉ፤ ሰደድ እሳቱ፣ ሁሉም ጉዳት አድርሷል። በአሳሳቢ የአየር ንብረት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ፕሬዝደንት ባይደን እውነቱን ማለትም በአየር ንብረት አስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ይፋ አድርገው፤ በዚሁ ልክ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል።»

 ልዩ ልዩ መፈክሮችን ያነገቡት ሰልፈኞች የባይደን አስተዳደር ከቅሪተ አጽም የሚገኘውን የነዳጅ ዘይትም ሆነ ጋዝ ማምረትን በሚያስፋፋት ሥራ መጠመዱን በመግለጽ ተቃውመዋል። በርካቶች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፉ በኒውዮርክ ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በዚህ ሳምንት የአየር ንብረትሳምንት ተብሎ በከተማዋ በይፋ ጉባኤ መጀመሩን ምክንያት ያደረገ ነው። ለአየር ንብረት ጥንቃቄ እንዲደረግ ድምፅ በተሰማበት ሰልፍ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በስፍራው የተገኙት በኒውዮርክ የዴሞክራት ፓርቲ ተጠሪ አሌክሳንድራ ኦካሲዮ ኮርቴዝ የሰልፈኞቹ ቁጥር መብዛት አስደስቷቸዋል።

ከቅሪተ አጽም የሚገኘውን የነዳጅ ዘይትም ሆነ ጋዝ ማምረት ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ የብሪታኒያ ነዳጅ ማጣሪያ ምስል blickwinkel/IMAGO

«ከእናንተ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፌ ዛሬ እዚህ በመገኘቴ ኩራት ተሰምቶኛል። ምክንያቱም እዚህ የተገኘነው ምድራችንን እና ሕዝቡን ለመጠበቅ፤ በመላው ዓለምም ከቅሪተ አጽም ነዳጅ ዘይት መጠቀም እንዲያበቃ ለማድረግ ለተመሳሳይ አላማ ነው። ወደዚህ ሰልፍ ይመጣል ብለን ያሰብነው ከአምስት እስከ 10 ሺህ ሰው ነበር፤ ሆኖም 50 እና 70 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወጡ። ያ ትርጉም አለው። ይኽ ጉዳይ የዘመናችን ትልቁ ጉዳይ ነው። በዚህም ምክንያት ብዛታችን ችላ ሊሉት የሚያዳግት መሆን ይኖርበታል።»

በሰልፉ ላይ የበርካቶች መገኘት

ባልተጠበቀ ሁኔታ በርካቶችን ወደ አደባባይ ያወጣው የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ስጋት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ተጠናክሮ መደጋገሙ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የተገለጸው። በዘንድሮው የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ተመዝግቧል። የሙቀት ማዕበሉን ተከትሎም ሰደድ እሳትን ጨምሮ ድንገተኛ ወጀብ የሚገፋው ከባድ ዝናብ በተለያዩ ሃገራት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። ከሰሞኑ ሊቢያ ላይ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ እና ያስከተለው ጉዳት የዓለምን ትኩረት እንደሳበ ነው። የሊቢያን ምሥራቃዊ ግዛት አካባቢ የመታው ከሜዲትራኒያን ባሕር የተነሳው ዳንኤል የሚል ስያሜ የተሰጠው ማዕበል ያስከተለው ኃይለኛ ዝናብ ዴርና በተባለችው ከተማ የሚገኘውን ግድብ የደረመሰ ጎርፍ አስከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል። ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች በአንዱ የሚገኙት ሊቢያዊው ኮሎኔል መሀመድ አብደል ዋህድ የደረሰውን ጥፋት ለመግለጽ አሁን አዳጋች ነው ይላሉ።

«እንዲህ ያለ እልቂት ያስከተለ አደጋ ሲያጋጥመን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ በጣም ከባድ ጥፋት ነው የደረሰው። ሰለባዎቹ….፣ የደረሰው የንብረት ውድመት….. ፤ በጣም ብዙ ሰዎች የገቡበት አልታወቀም። እዚህ…..፣ በዚህ ወረዳ ውስጥ ምስኪን ሰዎች እና ሊቢያውያን ሠራተኞች ናቸው ያሉት።»

የሊቢያን ምሥራቃዊ ግዛት አካባቢ የመታው ከሜዲትራኒያን ባሕር የተነሳው ዳንኤል የሚል ስያሜ የተሰጠው ማዕበል ያስከተለው ኃይለኛ ዝናብ ዴርና በተባለችው ከተማ የሚገኘውን ግድብ የደረመሰ ጎርፍ አስከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል። ፎቶ፤ በጎርፍ የተጎዳው የሊቢያ ግዛትምስል Hamza Turkia/Xinhua/IMAGO

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM በበኩሉ በምሥራቃዊ ሊቢያ ዴርና ግዛት ብቻ ከ38 ሺህ ሰዎች በላይ ቤታቸው በጎርፍ ተጠርጎ ሜዳ ላይ መቅረታቸውን አመልክቷል። የአየር ንብረት ባለሙያዎች አደጋውን ከዓለም የሙቀት መጨመር ውጤት ጋር ቢያይዙትም፤ የሊቢያ መሠረተ ልማት ማርጀትም ሌላው ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህ ሳምንት ኒውዮርክ ላይ በሚካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት 78ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የአየር ንብረት ቀውስ ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ነው። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ጠቅላላ ጉባኤው ከዓመታት በፊት አሳካቸዋለሁ ብሎ ላቀዳቸው ዘላቂ የልማት ግቦች የአየር ንብረት ለውጡ የጋረጠውን እንቅፋት በማመላከት ሃገራት አሁን የሚታየው የለውጡ ተጽዕኖ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ አስቀድሞ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል። ይኽን አስመልክቶ የተመድ ያዘጋጀው ዘገባ፤ እስካሁን ከታሰቡት ዘላቂ የልማት ግቦች 15 በመቶው ብቻ መስመር መያዛቸውን አመልክቷል። ዘላቂ የልማት ዕቅዶቹን ለማሳካት የታቀደው በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ነው። በ18 ድርጅቶች አስተዋጽኦ የተዘጋጀው የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ እንደሚለው ግን አሁን ባለው ደረጃ በተለይ የአየር ንብረትን በተመለከተ ግቡን ያሳካል ተብሎ አይታሰብም።

የአየር ንብረት ለውጡ ማሳያዎች

የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የዓለም የሙቀት መጨመር እንደማሳያ ከሚቀርብባቸው ክስተቶች አንዱ በአንታርክቲክ የሚገኘው ግግር በረዶ በፍጥነት መቅለጡ ነው። በተለይም በዘንድሮው ሙቀት ከመቼውም በበለጠ በረዶው እየቀለጠ ወደ ውኃነት መለወጡን በሳተላይት መረጃዎች መመዝገቡን በማመልከት ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን /ፍሬንድስ ኦፍ አርዝ /የመሬት ወዳጆች በመባል የሚታወቀው የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ ዓለም አቀፍ ተቋም ይፋ አድርጓል። የተቋሙ የሳይንስ፤ ፖሊሲ እና የምርምር ዳይሬክተር ማይክ ቺልድስ የአንታርክቲክ በረዶ መቅለጥ የአየር ንብረት ለውጡን መፋጠን አመላካች የማንቂያ ደወል ነው ይላሉ።

የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የዓለም የሙቀት መጨመር እንደማሳያ ከሚቀርብባቸው ክስተቶች አንዱ በአንታርክቲክ የሚገኘው ግግር በረዶ በፍጥነት መቅለጡ ነው። ፎቶ፤ በግሪንላንድ ደሴት የሚገኘው የበረዶ ተራራምስል Ulrik Pedersen/NurPhoto/picture alliance

«የአየር ንብረት ለውጡ እኛ ከምናስበው በተፋጠነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ይነግረናል። እንዲህ ያለው የማስጠንቀቂያ ደወል በመላው ዓለም እየተሰማ መሆኑን እያየን ነው። አንታርክቲካ ላይ የበረዶ ባሕር አግኝተናል፤ የካናዳን ሰደድ እሳትም ተመልክተናል፤ በበጋው ጊዜ በሙሉ ከመጠን ያለፈ ዝናብ፤ አንዳንዱም ሊቢያ ላይ እንዳየነው ያለ አስከፊ ሁኔታ ያጀበው አጋጥሞናል። በአብዛኛው አውሮጳ ውስጥ በዘንድሮው በጋ የሙቀት ማዕበል ተመዝግቧል። ማለቴ ይኽ ለመንግሥታት ጉዳዩን ከምር እንዲያስቡበት የሚያነሳሳ ሌላው የማንቂያ ደወል ነው፤ ብክለትን በመቀነስ ፈንታ፤ በእሳት ላይ ዘይት እንደመጨመር አይነት የአየር ንብረት ለውጥን ለማባባስ አዲስ የነዳጅ እና ጋዝ ፈቃድ መስጠትን እንዲያስቡበት የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም የባሕሩ በረዶ ሲቀልጥ፤ በመላው ዓለም የደረሰውን ከመጠን ያለፈ ክስተት ተመልክተናል፤ ገና ከዚህ የባሰ አደገኛ የአየር ጠባይ ብዙ ሰዎችን ሲጎዳ፤ ኤኮኖሚያችንን እና የምግብ ምርታችንን ሲያጠፋ መመልከታችን ይቀጥላል።»

ከጥቂት ዓመታት በፊት ክረምት ወቅቱን ጠብቆ በዝናብ መሬትን ሲያቀዘቅዝ፣ በአብዛኛውም የሚያነቃቃ ነፋሻ አየርን ሲያስከትል ይታወቃል። በበጋ ፀሐይ በአበቦች በታጀበችው ምድር ላይ አቅሟን ቆጥባ ውበት ታርከፈክፍ ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ክረምትና በጋ መስመራቸው ተደበላልቆ፣ ኃይላቸውንም አጠናክረው መከሰታቸው ምድርን ግራ እያጋባ ነው።

ክስተቱን ከአየር ንብረትለውጥ ጋር የሚያገናኙት እንዳሉ ሁሉ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚባል የለም በሚል ከፈጣሪ ቁጣ ጋር የሚያገናኙት ጥቂት አይደሉም። ዶቼ ቬለ ይኽን አስመልክቶ በፌስቡክ ያሰባሰበው አስተያየት ሁሉም በሚባል ደረጃ የፈጣሪ ቁጣ እና የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች አንደሆኑ የሚገልጹ ናቸው። ክስተቶቹን አስመልክተው አንድ ዘርፉ ተመራማሪ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ሳይሆኑ ክስተቶቹ በራሳቸው የአየር ንብረት ለውጥ ናቸው ብለዋል። የተፈጥሮ አደጋዎች፤ የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣቸውም ሆኑ የፈጣሪ ቁጣ በየዕለቱ የሚያደርሱት ጉዳት እየተጠናከረ መምጣቱ ግን የሚካድ አይደለም።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW