1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስ

በተንቀሳቃሽ ስልክ የኢትዮጵያ መፃህፍትን ለንባብ የሚያበቃው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 2 2014

በኢትዮጵያ የንባብ ባህል ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፤ ባህሉ አለመዳበሩ በተለያዩ መድረኮች ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል።ለዚህም የመፅሀፍት እና የቤተመፃህፍት እጥረት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይህንን ችግር በመገንዘብ ይመስላል ሶስት ኢትዮጵያዉያን የሶፍትዌር ባለሙያዎች «አፍሮሪድ» የተባለ የንባብ መተግበሪያ ሰርተዋል።

AfroRead Hörbuch
ምስል፦ AfroRead

መተግበሪያው መፃህፍትን በድምፅ በመተረክም ያሰደምጣል

This browser does not support the audio element.


አቶ ዳዊት ተገኜ ዓለሙ መኖሪያቸውን አውሮፓ ሲዊዘርላንድ ካደረጉ ዓመታት ተቆጥረዋል። በሚኖሩበት አውሮፓ የንባብ መፅሀፍት እና ቤተመፃህፍት የተትረፈረፈ ቢሆንም የሀገራቸውን መፃህፍት በተለይ ለልጆች የሚሆኑ መጽሀፍትን ማግኘት ግን ትልቁ ችግራቸው ነበር። ይህንን ችግራቸውን አሜሪካን ሀገር ለሚኖሩ ሁለት ጓደኞቻቸው  ሲያማክሩ ችግሩ ተመሳሳይ መሆኑን ተረዱ።
ችግሩ በሀገር ቤት ሌላ መልክ ይኖረው እንደሁ ለመገንዘብ እና በወጉ ለማጤን ኢትዮጵያ በመምጣት ሀገር ቤት ከሚኖሩ ደራሲያን ጋር ተወያዩ።በአንባቢያን በኩል የመፅሀፍት እና የቤተመፃህፍት እጥረት በደራሲያን በኩል ደግሞ  የህትመት ችግር መኖሩን እና ጉዳዩ በሀገር ውስጥም አንገብጋቢ ችግር መሆኑን ተገነዘቡ።ምንም እንኳ ችግሩ በአንድ ጀንበር የሚፈታ ባይሆንም የሶፍትዌር ምህንድስና ሙያቸውን ተጠቅመው የድርሻቸውን ለመወጣት ወሰኑ።

ምስል፦ Privat

እሳቸውም ሆኑ አሜሪካን ሀገር የሚኖሩት ጓደኞቻቸው አቶ ብዙነህ ብርሃን እና ነብዩ ሀይለስላሴ የሶፍትዌር ባለሙያዎች በመሆናቸው  አውጥተው አውርደው ሙያቸውን በመጠቀም ችግሩን ለመቅርፍ  አንድ መላ ዘየዱ።

በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም ግዙፍ ዲጂታል ሰርቪስ የተባለ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ በጋራ መሰረቱ። አቶ ዳዊት ዋና የቴክኒክ ሀላፊ ሆነው የሚመሩት ይህ ኩባንያ በ2021 ዓ/ም ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልኮች እና በታብሌት መፃህፍትን በድምፅ እና በንባብ ለአንባቢያን የሚያደርስ አፍሮሪድ/ Afroread /የተባለ መተግበሪያን ይፋ አደረገ። 

ምስል፦ Privat
ምስል፦ Privat

የሶፍትዌር ምህንድስና ባለሙያው አቶ ዳዊት እንደሚሉት መተግበሪያውን ለማውረድ  አነስተኛ የበይነመረብ ግንኙነት የሚፈልግ ሲሆን የተገዙ መፃህፍት ግን ያለበይነመረብ ግንኙነት ማንበብ ወይም ማዳመጥ ይቻላል።ከዚህ በተሻለ መንገድ የበይነመረብ ችግርን እና የስማርት ስልኮች እጥረትን ሊፈታ የሚችል እና ሰፊውን ማህበረሰብ ተደራሽ የሚያደርግ ሌሎች የቴክኖሎጅ አማራጮችን በማየት ላይ መሆናቸውንም አቶ ዳዊት ገልፀዋል። መጽሃፎችን በድምጽ እና በንባብ መልክ ቦታ ሳይገድበው በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ  አንባቢያን በኦን ላይን  የሚያቀርበውን AfroRead  ከጎግል እና ከአፕ ስቶር በነፃ ማውረድ ይቻላል።
አፍሮሪድ /AfroRead/ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰራ መተግበሪያ ሲሆን ለወደፊቱ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን  ለማካተት አስበዋል።በመተግበሪያው የሚጫኑ መፃህፍት በተለያዩ ቋንቋዎች የተፃፉ እና በይዘት ደረጃም ጥላቻን የማይሰብኩ ፣ አግላይ እና የማህበረሰብን እሴት የማይነኩ  እስከሆኑ ድር,ስ በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፉ መፃህፍትን በዲጅታል መድረኩ ያስተናግዳሉ። እንደ አቶ ዳዊት መነሻቸው መፅሀፍቱ መነበብ አለባቸው  የሚል እንጅ ተሽጦ ምን ያህል ገንዘብ ያወጣል የሚል ባለመሆኑ ፤ በብዙ ፈተናዎች ለተሞላው የኢትዮጵያ የመጻሕፍት ህትመት  ኢንዱስትሪ መፍትሄ የሚሰጥ ነው። ጀማሪ እና ወጣት ደራሲያንን ከአንባቢ ጋር ለማገናኘት እና ስራዎቻቸውን ተደራሽ ለማድረግም እድል ይሰጣል። ይላሉ አራት መጻህፍቶቻቸውን በዚሁ መተግበሪያ ለአንባቢያን ያበቁት እና ለኩባንያው  የይዘት ፕሮዳክሽንና የግብይት ባለሙያ ሆነው የሚሰሩት አቶ ደሳለኝ ማስሬ።

ምስል፦ Ato Dedalegn Masrie

እሳቸው እንደሚሉት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ደራሲያንም ቢሆኑ በገንዘብ እጥረት የተነሳ በአንድ እትም ከ5000 በላይ ቅጂዎችን አያሳትሙም። ይህም ብዙ አንባቢያን ዘንድ የመድረስ አቅምን ሲገድብ ቆይቷል።  ግዙፍ ዲጅታል አሳታሚ ከፀሐፊዎች ጋር እኩል የሆነ የገቢ መጋራት ስምምነት በማድረግ  መፃህፍትን በነጻ ለዲጅታል ህትመት የሚያበቃ በመሆኑ ፣ እንደ አቶ ደሳለኝ ለመፅሃፍ ህትመት  እንዲሁም ለተወካይ እና ለአከፋፋይ የሚከፈሉ ወጪዎችን በማስቀረት ለፀሃፊዎች እፎይታ ይሰጣል። 
ለአንባቢያንም ቢሆን መፃህፍትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል ይላሉ።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የንባብ ባህል ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፤ ባህሉ አለመዳበሩ በተለያዩ መድረኮች ተደጋግሞ ሲነገር  ይሰማል።ለዚህም  የመፅሀፍት  እና የቤተመፃህፍት እጥረት  በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከዚህ አኳያ መፃህፍቱ ወጣቱ በሚያዘወትረው የተንቀሳቃሽ ስልክ መቅረባቸው በቀላሉ ወደ  ንባብ እንዲሳብ ሊያደርግ ይችላል።
በአሁኑ ወቅት ከ5000 በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት አፍሮሪድ የኢትዮጵያን ስነጽሁፍ  ዲጂታል ለማድረግ እና ማዳመጥ ለሚፈልጉ ሰዎች ፤የመጻሕፍቱን የድምጽ ቅጂ በራሱ ስቱዲዮ ያዘጋጃል። ደረጃውን የጠበቀ እና ዘላቂ ስራ ለመስራት የመፅሃፍቱ ትረካ በባለሙያዎች ይከናወናል።ስራው ከሚኖሩበት አውሮፓና አሜሪካ ሆኖ በሩቅ የሚሰራ አይደለምና  በሀገር ቤት ቢሮ በመክፈት እና የአርትኦት ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በመቅጠር እየተሰራ ይገኛል።
መድረኩ በዚህ መልኩ  ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ እንዳለጌታ ከበደ፣ አለም ፀሀይ ወዳጆን፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ይስማከ ወርቁ እና ህይወት ታደሰን ጨምሮ የ46 አንጋፋ እና ወጣት ደራሲዎችን መፃህፍት ስአሳትሟል። 

ምስል፦ AfroRead

ባለሙያው እንደሚሉት በውጭ ሀገር ያሉ አንባቢያን እንደ ቪዛ፣ ማስተርካርድ እና ፔይፓል ያሉ ዓለምአቀፍ የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም መጽሐፍትን መግዛት ይችላሉ። የሀገር ውስጥ አንባቢዎች ደግሞ ቴሌ ብር የተባለውን የክፍያ ዘዴ መጠቀም ይችላሉ። AfroRead ለእያንዳንዱ ዲጅታል  እና የድምፅ መጽሐፍት ግዥ ደረሰኝ በኢሜል ይልካል። 
 በሌላ በኩል ተጠቃሚዎች መጻህፍትን ማድመጥ ወይም ማንበብ የሚችሉት  በግዥ ወቅት ጥቅም ላይ በሚውለው መለያ ብቻ በመሆኑ፤ መፃህፍቱ ለሌላ ተጠቃሚ ሊጋሩ ወይም ሊተላለፉ አይችሉም።በዚህም የመፃህፍቱ የቅጂ መብት የተጠበቀ መሆኑን አቶ ዳዊት አመልክተዋል።
ይህ መተግበሪያ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መፃህፍትን ዲጅታል በማድረግ  ላይ ያተኮረ ይሁን እንጅ ለወደፊቱ ግን መተግበሪያውን በአፍሪቃ ደረጃ የማሳደግ ዕቅድ እንዳለ አቶ ደሳለኝ ገልፀዋል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW