1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተፈናቃይ መጠለያ የአዲስ ዓመት አከባበር ይዞታ

ማክሰኞ፣ መስከረም 1 2016

በተለያዩ ግጭቶች ምክኒያት ኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አከባቢዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ያሉት ተፈናቃዮች አዲሱን ዓመትን እንዴት እያከበሩት ይሆን? ተፈናቃዮቹ ተስፋ ባደረጉት አዲስ ዓመት ቢገጥመን ያሉትን መልካም ምኞታቸውንም ሲያስተላልፉ ከምንም በላይ ሰላም እንዲመጣ ተመኝተዋል፡፡

Äthiopien Kiremu
ምስል Privat

ሰይድ አበባው በ2013 ዓ.ም. ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ተፈናቅለው ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ደጋን ተፈናቃዮች መጠለያ ከገቡ አሁን ሶስተኛውን የአዲስ ዓመት መለወጫ በዓልን እሳቸውን ከመሰሉ በርካታ ተፈናቃዮች ጋር በማሳለፍ ላይ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉን በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በአከባቢያቸው የተስፋፋው ግጭት ለበርካቶች እልቂት ምክኒያት ሆኖ ለስዴት ሲዳርጋቸው ችግሩ በቶሎ ተፈቶ ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ተስፋን እንደሰነቁ ነበር፡፡ አቶ ሰይድ ዛሬ በተፈናቃዮች ካምፕ እያሉ፤ የአዲስ ዓመት ልዩ የበዓል አከባበርን በትዝታ ብቻ እየናፈቁ የአይቅርብን የበዓሉ አከባበር ላይ መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የወለጋ ተፈናቃዮችምስል Alemnew Mekonnen/DW

“ያው የተፈናቃይ ነገር ብዙም ደስ አይልም በዓሉ፤ ግን እንደነገሩ ውለናል” ይላሉ በተከፋ ድምጽ፡፡ “እንደወትሮ ጎረቤት ተጠራርተን ቤት ሞልቶ ባይሆንም ባለን መጠለያ ካምፕ ቡና አፍልተን ቄጠማ ጎዝጉዘን መልካሙን እየተመኘን እያሳለፍን ነው” ብለዋልም፡፡ ተፈናቃዩ ከፊል ወገኖቻቸው በየተፈናቃዮች ካምፕ ሌላውም ባልተረጋጋ ሰላም በቀዬው እያሳለፈ ያለው በዓል ሙሉ ደስታ ያለበት አለመሆኑንም አውስተዋል፡፡የወለጋው ግጭት ያፈናቀላቸው ወገኖች የእርዳታ ጥሪ

ሌላው የበዓሉን ውሎ ልንጠይቃቸው የደወልንባቸው ተፈናቃይ ደግሞ ከዚያው ከወደ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ነው፡፡ ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን የሰጡን የኪረሙ ተፈናቃይ ከሚወዱት ግብርና ተለያይተው ኑሮያቸውን ተሰናብተው በከተማው መጠለያ ማዕከል ህይወትን መግፋት ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመታቸው እየመጣ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እንደው በዓል እንዴት እያሳለፉ ነው አልኳቸው፡፡ በሳቅ መለሱ! የፌዝ ሳቅ!፡፡ “ያው ባለንበት ቦታ በዓሉን በዓል ለማስመሰል እየጣርን ነው፡፡ ዶሮም አርደን ቅርጫም ገብተናል፡፡ ብያንስ እኛ መጠለያ አለን፡፡ ከእኛም የከፋ ህይወት የሚገፉ አሉና እነሱን እያሰብን ያዘጋጀነውም አልበላ ይለናል” ይለኛል ሲሉም ያሉበትን ህይወት አሳዛን ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የወለጋ ተፈናቃዮችምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከወደ ጉጂ ጎሮዶላ ወረዳ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከዞን መዋቅር ጋር ተያይዞ በተነሳው ቅሬታ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ከቀዬያቸው መፈናቀላቸውን የሚያነሱት ነዋሪም አስተያየታቸውን አከሉ፡፡ በዓልን እያከበሩ ነው አልኳቸው፡፡ “አይደለም! አይደለም!” ሲሉ መለሱ፡፡ በርካቶች ታስረው በተፈጠረው አለመረጋጋት ከቄዬያቸውም የተፈናቀሉ ብዙ ናቸውና በዓሉ እኛ ጋ በዓልም አይመስልም ሲሉ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፡፡የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ለተፈናቃዮች ያሰባሰቡት ርዳታ

እንዲያም ሆኖ ተፈናቃዮቹ አዲሱ 2016 ዓ.ም. የተሻለውን ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ግን ደግሞ ሊገጥም ይችላል የሚሉት ተግዳሮትም ይታያቸዋል፡፡ “አሁን ካለው ፈተና ክብደት አንጻር እንደው ነገሮች በቶሎ ይስተካከላሉ ብለን ባናስብም ተስፋ ማድረጋችንን አናቋርጥም” ይላሉ፡፡

ተፈናቃዮቹ ተስፋ ባደረጉት አዲስ ዓመት ቢገጥመን ያሉትን መልካም ምኞታቸውንም ሲያስተላልፉ  ከምንም በላይ ሰላም አጉልተው አንስተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW