በቴክኒክ ችግር ለወራት ተንሳፈው የቆዩት ጠፈርተኞች ወደ ምድር ተመለሱ
ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2017
አሜሪካዊያኑ ጠፈርተኞች ባሪ ዊልሞር እና ሱኒታ ዊሊያምስ ከአስቸጋሪ ቆይታ በኋላ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ዛሬ ወደምድር ተመልሰዋል። ሁለቱ ጠፈርተኞች በዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዘጠኝ ወራት በላይ ቆይተዋል ። ጠፈርተኖቹ ባሪ ዊልሞር እና ሱኒታ ዊሊያምስ ወደ ዓለምአቀፍ የጠፈር ጣቢያ የሄዱት ናሳ እና ቦይንግ በሰሩት የስታርላይነር የጠፈር መንኮራኩር በጎርጎሪያኑ ሰኔ 2024 ዓ/ም ሲሆን፤ ተልዕኳቸውም የስምንት ቀናት ብቻ ነበር።
የጠፈርተኞቹ ተልዕኮ ለምን ተራዘመ?
የጠፈርተኞቹ ተልዕኮ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ቆይታቸው ወደ ዘጠኝ ወር የተራዘመው የስታርላይነር መንኮራኩር በገጠመው የቴክኒክ ችግር ነበር። በዚህ ወቅት ታዲያ ናሳ በሁለት አማራጮችን መህል ወደቀ፤ አንደኛው ችግሮቹን በማስተካከል ጠፈርተኞች በስታርላይነርን ወደ ምድር እንዲመልሱ ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ስታርላይነርን መንኮራኩርን ከነችግሩ ያለ ሰው ወደ ምድር መመለስ ነበር ። የስታርላይነር መንኮራኩር በገጠሙት በርካታ የቴክኒክ ችግሮች ሳቢያ ጠፈርተኞቹን ወደ መሬት መመለስ በጣም አደገኛ በመሆኑ እነሱን እዚያው እንዲቆዩ በማድረግ ፤ናሳ ሁለተኛውን አማራጭ በመጠቀምን መረጠ። እናም ዊልሞርን እና ዊሊያምስን ከ ስፔስ ኤክስ ቡድን 9 /SpaceX's Crew-9/ ከሚባለው ተልዕኮ ጋር በመጋቢት 2025 ወደ ምድር እንዲመለሱ ተወሰነ።
ይህም ቆይታቸውን መጀመሪያ ከታቀደው ስምንት ቀናት ወደ ዘጠኝ ወር አራዝሞታል።ይህንንም ጠፈርተኛው ባሪ ዊልሞር ካለበት የጠፈር ጣቢያ ሆኖ ግልፅ አደረገ። «እንደ እኛ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙህ አንዳንድ ለውጦች መደረግ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው።»ብለዋል። ስታርላይነር የአሜሪካው የጠፈር ጣቢያ የናሳ የንግድ ፕሮግራም ቡድን አካል ሆኖ በቦይንግ የተሰራ የጠፈር መንኮራኩር ሲሆን፤ ይህ መርሃ ግብር የግል ኩባንያዎች ወደ አለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ለማድረስ የበረራ አገልግሎት ይሰጣል። ሁለቱን ጠፈርተኞች የመለሰው ተቀናቃኙ ስፔስ ኤክስም እንደዚህ አይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል። ያለፈው ሰኔ ሁለቱ ጠፈርተኞች የተጓዙትም ለዚህ መሰሉ አገልግሎት ሙከራ ነበር። በዚህ አገልግሎት ችግር የገጠመው የስታር ላይነር መንኮራኩር ባለፈው በመስከረም ወር መጀመሪያ ጠፈርተኞቼን እዚያው ትቶ ባዶውን ወደ ምድር እንዲመለስ ተደርጓል።
የ እስፔስ ኤክስ 9 ተልዕኮ በዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ ጠፈርተኞች ፣ ዊልያምስ እና ዊልሞር በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ምርምር የማድረግ እና በየትምህርት ቤቶቹ ስለጠፈር ጉዞዎች እና ስለ ህዋ ህይወት በቪዲዮ ህፃናትን የማስተማር ስራቸውን ቀጥለዋል። የገና ቀንን ጨምሮ ጠፈር ላይ ሆነው ብዙ ቃለመጠይቆችን ሰጥተዋል። በዚህ ወር መጀመሪያ ሱኒ ዊሊያምስ እንደተናገሩት መዘግየታቸው ከነሱ ይልቅ መድር ላይ ላሉ ቤተሰቦቻቸው ሁኔታው ከባድ ነው። «ታውቃላችሁ! እኛ እዚህ ተልዕኮ አለን። በየዕለቱ የምንሰራውን ስራ ነው እየሰራን ያለነው። ታውቃላችሁ፣ እያንዳንዱ ቀን አስደሳች ነው። ምክንያቱም በህዋ ላይ ስለምንገኝ ለኛ በጣም አስደሳች ነው። በጣም ከባዱ ነገር፣ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ፣ መሬት ላይ ያሉ ሰዎች መቼ እንደምንመለስ በትክክል አለማወቃቸው ነው ብዬ አስባለሁ።» በመስከረም ወር ችግር የገጠመው መንኮራኩር ባዶውን ወደ ምድር ሲመለስ ጠፈርተኖቹ ቡች እና ሱኒ ከሌላ ለስድስት ወር ተልዕኮ ከተሰጠው SpaceX 9 ከተባለ ቡድን ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ለአራት ጠፈርጠኞች መቀመጫ ያለው የ SpaceX 9 ተልዕኮ መንኮራኩር ፤ለቡች እና ለሱኒ መመለሻ ሁለት መቀመጫዎች ትቶ ነበር ከሁለት ጠፈርተኞች ጋር ያለፈው መስከረም ወደ ህዋ የተጓዘው።ያለፈው እሁድ ግን ይህ ተልዕኮ በመጠናቀቁ የ SpaceX ተልዕኮ 10 የተባለ ተተኪ ጠፈርተኞችን የያዘ ሌላ መንኮራኩር ወደ ህዋ አምርቷል።በዚህ ሁኔታ ፍሎሪዳ ከሚገኘው የኬኔዲ የጠፈር ጣቢያ ያለፈው አርብ የተነሳው የስፔስ ኤክስ ተልዕኮ 10 ቡድን በቦታው ደርሶ ከዘጠኝ ወራት በላይ የቆዩትን ጠፈርተኞች ተክቷቸዋል። ከናሳ ተልዕኮ ቁጥጥር ማዕከል ጠፈርተኛዋ ሱኒ ዊልያምስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዘጠኝ ወራት በላይ የቆየችበትን ዓለም አቀፉን የጠፈር ጣቢያ ለቃ ወደ ቤት እንድትመለስ የሚተካት ቡድን በቦታው ሲደርስ ምስጋናዋን ገለፃለች። «አመሰግናለሁ። በዚህ ጠዋት በመምጣታችሁ። በጣም ጥሩ እና ደስ የሚል ቀን ነው። ጓደኞቻችን ሲመጡ ማየት በጣም ጥሩ ነገር ነው። ስለዚህ በጣም አመሰግናለሁ።» ብላለች።
ከ286 ቀናት በላይ የቆዩት ሁለቱ የናሳ ጠፈርተኞች መመለስ
በዚህ ሁኔታ ከሰኔ 2024 ዓ/ም ጀምሮ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ከ286 ቀናት በላይ የቆዩት ሁለቱ የናሳ ጠፈርተኞች ሱኒ ዊሊያምስ እና ቡች ዊልሞር ፤ ናሳ እና ስፔስኤክስ ባደረጉት የጋራ ጥረት በሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ በኩል ፍሎሪዳ የባህር ዳርቻ በደህና ደርሰዋል።ቡች እና ሱኒ ከ17 ስዓት በረራ በኋላ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ወደ ምድር የተመለሱት፤ከናሳ ጠፈርተኛ ኒክ ሄግ እና ሩሲያዊው ኮስሞናዊት አሌክሳንደር ጎርቡኖቭ ጋር በመሆን ነው። ሄግ እና ጎርቡኖቭ ባለፈው መስከረም በስፔስ ኤክስ ደራጎን መንኮራኮር በ/ SpaceX Dragon capsule / ወደ ጠፈር ጣቢያው የደረሱ ጠፈርተኞች ሲሆኑ፤ ከቡች እና ሱኒም በዚህ ቡድን ውስጥ ተካተው አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል። ተልዕኮው «ስፔስ ክሪው 9» በመባል የሚታወቅ ነው። ይህ ጠፈር ጉዞ ለኮስሞናዊው አሌክሳንደር ጎርቡኖቭ የመጀመሪያ ሲሆን የናሳው ኒክ ሄግ በ2019 በጠፈር ጣቢያው 203 ቀናትን አሳልፏል።
ጠፈርተኞቹ ሱኒ ዊሊያምስ እና ቡች ዊልሞር እነማን ናቸው?
የ59 ዓመቷ ሱኒ ዊሊያምስ በጎርጎሪያኑ 1998 ዓ/ም በናሳ የጠፈር ተመራማሪ ሆና የተመረጠች ሲሆን፤ ከአሁኑ የዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ ተልዕኮ በፊት የሁለት የጠፈር ተልዕኮዎች ላይ ሰርታለች። ሱኒ በሞስኮ ከሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ጋር በመሆንም ለጠፈር ጣቢያው አስተዋፅዖ አድርጋለች። ከዚያም በሮቦቲክስ ክፍል ውስጥ ሰርታለች።ዊሊያምስ ቀደም ያሉትን ሁለት ተልእኮዎቿን ጨምሮ በአጠቃላይ 322 ቀናትን በጠፈር አሳልፋለች። ለዚህ አገልግሎቷም ክብረ ወሰኑን ለእሷ መስጠቱን በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የናሳ የኦፕሬሽን ኢንተግሬሽን ማናጄር የሆኑት ቢል ስፔች ዛሬ ገልፀዋል።
«286 ቀኖችን ህዋ ላይ በመቆየት እና ወደ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ለጉብኝት የሚሄዱ እና የሚመጡ ስምንት የተለያዩ መንኮራኮሮችን መርተዋል። ኒክ እና ቡቺ እያንዳንዳቸው አንድ የጠፈር ጎዞ ፤ሳኒ ደግሞ ሁለት የጠፈር ጎዞዎችን አድርጋለች። ስለዚህ ጠፈር ላይ ብዙ ጊዜ የሰራች ሴት በሚል ክብረ ወሰኑን ለሳኒ ሰጥቷል።» ሌላው ጠፈርተኛ ቡች ዋልሞር የሁለት የጠፈር በረራዎችን ያደረገ ሲሆን በጠፈር ውስጥ 178 ቀናትን አሳልፏል። በጎርጎሪያኑ ሀምሌ 2000 ዓ/ም በናሳ የጠፈር ተመራማሪነት የተቀጠረው የ62 ዓመቱ ጠፈርተኛ ጡረታ የወጣ የአሜሪካ የባህር ኃይል ካፒቴን ነው። በመጨረሻው ተልዕኮውም፣ ለኤክስፒዲሽን 41 የበረራ መሐንዲስ ሆነው አገልግሏል።ይህንን ተልዕኮ አጠናቆ እና ቦታውን ለኤክስፒዲሽን 42 ቡድን በማስረከብ ፤ በመጋቢት 2015 ዓ/ም ወደ ምድር የተመልሷል። በዚህ ተልዕኮ ለ167 ቀናት በጠፈር ውስጥ ቆይቷል።
ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የጤና ችግሮች
ሁለቱም ጠፈርተኞች ልምድ ያላቸው የጠፈር ተመራማሪዎች ሲሆኑ፤ ከአሁኑ ከተልዕኮ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀናትን በጠፈር አሳልፈዋል። በተለይ የስታርላይነር በረራ የመጀመሪያ እና የሙከራ ተልእኮ ስለነበር ለከፋ ሁኔታ ተዘጋጅተው የሰለጠኑ ናቸው። ያም ሆኖ የናሳ ጠፈርተኞች ባሪ “ቡች” ዊልሞር እና ሱኒታ “ሱኒ” ዊልያምስ ከታሰበው በላይ ጠፈር ላይ በመቆየታቸው ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ የጤና አደጋዎች ይኖራሉ። ካልተጠበቀው የዘጠኝ ወራት ቆይታ ሲመለሱ ጠፈርተኞቹ፤ ሰውነታቸው ከጨረር እና ከማይክሮግራቪቲ ጋር መለማመድ ይኖርበታል።የጨረር እና የማይክሮግራቪቲ ተጽእኖ ለእያንዳንዱ የጠፈር ተመራማሪ ከማቅለሽለሽ እስከ ፊት እብጠት የሚያስከትል ተመሳሳይ ችግር ይፈጥራል። ነገር ግን ይህ ተልዕኮ ለአንድ ሳምንት ብቻ እንዲቆይ ታስቦ የነበረ በመሆኑ ጉዳቱ በሱኒ እና በቡች ላይ የከፋ ይሆናል የሚል ስጋት አሳድሯል።
በመሆኑም ከአሜሪካውያኑን የጠፈር ተመራማሪዎች ኒክ ሄግ እና ሩሲያዊው አሌክሳንደር ጎርቡኖቭን ጨምሮ ጠፈርተኞቹ ለጤና ቁጥጥር ሂዩስተን ወደሚገኘው የናሳ የጠፈር ማእከል ተጉዘዋል። ይህ ያሳሰባቸው የናሳ የንግድ በረራ ፕሮግራም ክፍል ማኔጀር ስቲቭ ስቲች የጠፈርተኖቹን የአቀባበል በዓል ከማክበራችን በፊት ደህንነታቸው ቀዳሚ ነው ብለዋል። «ከአከባበርን በተመለከተ ያን ያህል የምንጓጓበት አይመስለኝም። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ለቡድን 9 አባላት ሠራተኞች መመለስ በጣም ጓጉተናል። ቡቸ እና ሱኒ ተመልሰው ሲመጡም ለማየት ጓጉተናል። እና ከዚያ ወዲያ የአቀባበል ስነስርዓት እናደርጋለን።ታውቃላችሁ፣ እነሱ ዝግጁ ሲሆኑ። እነሱን እንደገና ለማነቃቃት እና ወደ ጥሩ መንፈስ ለመመለስ ትንሽ ጊዜ ስለሚወስድ፤ ከዚያ በኋላ ነው ተገቢውን የአቀባበል በዓል የምናደርገው።» ሲሉ ገልፀዋል።
ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ