1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በትግራይና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን ስለመፍታት የምሁራን አስተያየት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2016

በትግራይና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንዳለባቸው ምሁራን አመለከቱ።

Äthiopien Southern Tigray, Alamata
የአላማጣ መንገድ ምስል Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

በትግራይና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች

This browser does not support the audio element.

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ሰብአዊ መብቶች ተመራማሪ ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ የትግራ ኃይሎች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መዳኘት እንዳለባቸው ሲያመለክቱ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የግጭትና ግጭት አፈታት ተመራማሪ ዶ/ር ገብረ ኢየሱስ ተክሉ ባህታ ደግሞ በሀገሪቱ ላሉ የጎሳ ግጭቶች መነሻው ፌደራላዊው አወቃቀሩ በመሆኑ እንደገና መዋቀር አለበት ይላሉ።

ሰሞኑን በራያ አላማጣና አካባቢው በተቀሰቀሰው ግጭት በርካቶች ሲፈናቀሉ በመንገድ ላይ ሕይወታቸው ያለፈም እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ሰብአዊ መብቶች ተመራማሪና መምህር ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ የህወሓት ኃይሎች የፈጸሙት ድርጊት ትክክል ባለመሆኑ የአማራን ህዝብና መንግሥት ይቅርታ ጠይቀው ሰሞኑን በኃይል ከያዟቸው አካባቢዎች መውጣት እንዳለባቸው ነው የሚናገሩት። እንደ ዶ/ር ሲሳይ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ችግሮች መፈታት ያለባቸው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ብቻ መሆን ይኖርበታል።

ሁሉም ነገር ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ እንዳለበት የሚያምኑት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የግጭትና ግጭት አፈታት ተመራማሪና መምህር ዶ/ር ገብረ ኢየሱስ ተክሉ ባህታ ደግሞ በየቦታው የሚነሱ የጎሳ ግጭቶችን ለዘለቄታ ማስወገድ ክልሎቹ እንደገና መዋቀር አለባቸው ይላሉ።

«... ለኦሮሚያ ትልቅና ሰፊ ክልል ሰጥቶ፣ ለሀረሪ ጠባብ ክልል አይሰራም፣ የክልሎች አደረጃጀት ራሱ ለጎሳ ግጭት አመቺ ነው፣ ስለዚህ ዋናው ያሉትን የጎሳ ግጭቶች በዘላቂነት የሚገላግለን ፌደራል ስርኣቱን አፈራርሶ ወደ 50ና 60 ክልሎች ማድረግ፣ ወይም በአቅጣጫ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብሎ መከለል ነው።  ቢያንስ ይህ አጠቃላይ በአገሪቱ የሚታዩ የጎሳ ግጭቶችን ያስወግዳል።» ነው የሚሉት። ይህን ዓይነት አወቃቀር በመዘርጋት ብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ከጎሳ ግጭት አርፈዋል ነው ያሉት ናይጀሪያን እንደ አብነት በመውስድ።

የትግራይ ኃይሎች ሰሞኑን ከያዟቸው አንዳንድ አካባቢዎች በተወሰነ ደረጃ ወደ ኋላ እያፈገፈጉ እንደሆነ መረጃ መስማታቸውን ዶ/ር ሲሳይ ቢገልፁም፣ አንድ የራያ አላማጣ ነዋሪ ግን አላማጣ ከተማን ታጣቂዎቹ መክበባቸውን አመልክተዋል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW