1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ለ2004 የሕግ ታራሚዎች «ይቅርታ» ተደረገ

ዓርብ፣ ሰኔ 14 2011

በትግራይ ክልል፦ ኤርትራውያንን ጨምሮ ለ2004 የሕግ ታራሚዎች «ይቅርታ» መደረጉ ዛሬ ተገለጠ። 13 ኤርትራውያንን ጨምሮ ከሁለት ሺህ በላይ ለኾኑት የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገው በክልሉ በነገው እለት የሚከበረውን የሰማእታት ቀን በማሰብ መኾኑ ተገልጧል። ታራሚዎቹ ከነገ ጀምሮ በነጻ እንደሚለቀቁም ተገልጧል።

Äthiopien Tigray Region Tekiu Mitiku
ምስል DW/M. Hailesillassie

ትግራይ፦ከሁለት ሺህ በላይ ታራሚዎች ሊፈቱ ነው፤ 13ቱ ኤርትራውያን ናቸው

This browser does not support the audio element.

13 ኤርትራውያንን ጨምሮ ለ2004 የሕግ ታራሚዎች «ይቅርታ» መደረጉን የትግራይ ክልል መንግሥት ዐስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግስት ፀጥታና አስተዳደር ጽ/ቤት እንደገለፀው ለሕግ ታራሚዎቹ ይቅርታ የተደረገው የትግራይ ሰማእታት ቀንን አስመልክቶ ነው፡፡ በነገው ዕለት የሚከበረውን 31ኛውየትግራይ ሰማእታት ቀን አስመልክቶ በትግራይ ክልል ካቢኔ የተሰጠው ይህንኑ የይቅርታ ዕድል 51 ሴት ታራሚዎችን ጨምሮ 2004 እስረኞች በነጻ እንደሚለቀቁ ተገልጧል።፡ ዛሬ ይቅርታ ከተደረገላቸው በትግራይ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ከነበሩ እስረኞች አብላጫዎቹ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች እንደሆኑ ከክልሉ መንግሥት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ለእስረኞቹ ከተደረገው ይቅርታ ጋር ተያይዞ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ተኪኡ መተኩ በይቅርታ የሚለቀቁት 13 ኤርትራውያን ጨምሮ 2004 እስረኞች በነበራቸው የማረሚ ቤት ቆይታ በስነ ምግባርና ሞያ በተሻለ ሁኔታ የታነፁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ የነበራቸው እንዲሁም በአንድ ድርጊት ተደራራቢ ወንጀል የፈፀሙትን ጨምሮ አስገድዶ መድፈር፣ «ሀንግ» ተብሎ በሚታወቅ ጎሮሮን በማነቅ የሚፈጸም የዝርፍያ ተግባር የተሳተፉ ወንጀለኞች በተደረገው ይቅርታ እንዳልተካተቱ ተጠቅሷል፡፡ በይቅርታው የተካተቱ ኤርትራውያን በሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ዝርፍያ ወንጀሎች ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑን የትግራይ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተኪኡ መተኩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ «ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ታሰሩ፣ የይቅርታ ዕድሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት አያካትትም» የሚል ወቀሳ ተቀባይነት የለውም ያሉት ኃላፊው ይቅርታው የፖለቲካ አመለካከት፣ የብሔር ማንነት ሳይለይ የተሰጠ ነው ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልል ፀጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ካለፈው ዓመት ወርሃ ግንቦት ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ የክልሉ መንግሥት ለ7538 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል። ከነዚህ መካከል 98 በመቶዎቹ ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተመለሱ ሲሆን፤ 180 ሰዎች ግን ዳግም ወንጀል ፈፅመው ወደ ማረሚያ ቤት መመለሳቸው ተጠቁሟል፡፡

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW