1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በትግራይ «ሕግ ማስከበር» ዘመቻ መጀመሩ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 2016

በትግራይ «ሕግ ማስከበር» ያለው ዘመቻ መጀመሩን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ። በዚህ ዘመቻ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የማዕድናት ምዝበራ፣ መሬት ወረራ እና ሌሎች ወንጀሎች ተሳትፎ ያላቸው አካላት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ የአስተዳደደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።

መቀለ ከተማ
መቀለ ከተማ ምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ «ሕግ ማስከበር» ዘመቻ መጀመሩ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ በተለይም በጦርነቱ እና ከጦርነቱ በኋላ ባለው ጊዜ የወንጀል ተግባራት እየተበራከቱመምጣታቸው በነዋሪዎች እና ሌሎች አካላት ይገለፃል። ጦርነቱ የፈጠረው የሕግ አውጪና አስፈፃሚ አካላት መፍረስ አልያም መዳከም ለወንጀሎች መበራከት፣ ለኅብረተሰብ ሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆኑ የሚገለፅ ሲሆን፥ በዚሁ ክፍተት ደግሞ ታጣቂዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ባለሀብቶችን ጨምሮ ሌሎች በሕገወጥ ተግባራት እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሎ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ሲቪክ እና የፖለቲካ ተቋማት ወቀሳ ይቀርባል። በተለይም በክልሉ ሰሜን ምዕራብ ዞን በሕገወጥ መንገድ የሚካሄደው የወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናት ቁፋሮ፣ ከኤርትራ በትግራይ በኩል እስከ አዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች የተዘረጋ፤ በሕገወጥ መንገድ ሰዎች የማዘዋወር ድርጊት፣ በጦርነቱ ጊዜ የወደሙ ተሽከርካሪዎች እና ብረታ ብረት ዝርፍያ እና ሌሎች ወንጀሎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚያነሳው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በእነዚህ ተግባራት ላይ የተሳተፉ አካላትን ለማደን የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን፥ ይህ ዘመቻም መቐለን ማእከል አድርጎ እየተከወነ መሆኑ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረዳ ትናንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ እና የማዕድናት ምዝበራ ዋነኛ እና አሳሳቢ ወንጀሎች መሆናቸውን ያነሱት ጀነራል ታደሰ፥ ይህን የሚመለከት ግብረ ሀይል መቋቋሙንም ተናግረዋል።

ጀነራል ታደሰ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከወቅታዊው በትግራይ ካለው ፖለቲካዊ መሳሳብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው፥ ሕግ የማስከበር እርምጃ መሆኑ ገልፀዋል። ጀነራል ታደሰ ወረደ «ይህ ዋነኛ አለማው የትግራይን ሰላም እና ፀጥታ፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይሆናል። ይህን ካላደረግን ሌሎች ወንጀሎችንም ማስቆም አይቻልም። ይህን በማድረግ በትግራይ በመደበኛ ፖሊስ ሕግ የማስከበር ተግባር የሚቀጥልበትን ደረጃ ለመፍጠር እንሠራለን» ብለዋል።

ሳምንት ባለፈው ሕግ የማስከበር የተባለ ዘመቻ እነማን፣ ምን ያክል ተጠርጣሪዎች ተያዙ የሚለውን ከመግለፅ የተቆጠቡት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና በአስፈላጊ ጊዜ ዝርዝር መረጃ ለሕዝብ እንደሚገለጽ ተናግረዋል። እየተወሰደ ነው ከተባለው እርምጃ ጋር በቀጥታ ስለመገናኘቱ ማረጋገጥ ባይቻልም ፥ የትግራይ ፖሊስ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነሮች ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን እንዲሁም በርካቶች በተጠርጣሪነት መያዛቸውን ከምንጮች ሰምተናል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW