1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች የመመለስ ዕቅድ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2016

በትግራይ የሚገኙ አንድ ሚልዮን ገደማ የጦርነቱ ተፈናቃዮች መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ። የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች በቅርቡ ወደቀያቸው እንዲመለሱ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጿል። ይህ የተያዘው ተፈናቃዮች የመመለስ እቅድ ለበርካቶች ተስፋ ቢፈጥርም በጥርጣሬ የሚመለከቱትም አልጠፉም።

አንዲት ተፈናቃይ እናት ልብስ ሲያጥቡ
የትግራይ ጊያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጋር በተደረሰ ስምምነት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ቀን መቆረጡን ተናግረዋል። ምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች የመመለስ ዕቅድ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ የሚገኙ አንድ ሚልዮን ገደማ የጦርነቱ ተፈናቃዮች መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ። የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች በቅርቡ ወደቀያቸው ሊመለሱ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባባት ላይ መደረሱ ይገልፃል። ይህ የተያዘው ተፈናቃዮች የመመለስ እቅድ በርካቶች ላይ ተስፋ ቢፈጥርም ሌሎች በጥርጣሬ የሚመለከቱትም አልጠፉም።

ለሁለት ዓመታት በፌደራል መንግስት እና የትግራይ ሀይሎች መካከል የተደረገው ጦርነት ተከትሎ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚገመቱ ተፈናቃዮች አሁንም ኑሮአቸው በግዚያዊ መጠልያ ጣብያዎች ሆኖ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 የትግራይ ተፈናቃዮች እስከሰኔ መጨረሻ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ተባለ

እነዚህ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው የመመለስ ተግባር በተለያዩ ምክንያቶች ሲደናቀፍ የቆየ ሲሆን፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በቅርቡ እንዳስታወቀው ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓመተምህረት ድረስ ሁሉም የጦርነቱ ተፈናቃዮች ወደቦታቸው እንደሚመለሱ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባባት ላይ መደረሱ ገልጿል። 

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ እንዳሉት ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጋር በተደረሰ ስምምነት ተፈናቃዮቹ ለመመለስ ቀን መቆረጡ ገልፀው ነበር።

የአማራና የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ውዝግብ ወዴት እየሄደ ነው?

ጀነራል ታደሰ "የተቀመጠው ግዜ፥ ራያ እና ፀለምቲ እስከ ግንቦት 30 ሊጠናቀቅ፣ ምዕራብ ትግራይ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ባለው ልናጠናቅቅ የሚል ነው። ይህ ሙሉ መግባባት የተደረሰበት ነው። በእኛ በኩል በተቀመጠው ሐሳብ እና አፈፃፀም ተግባብተን ጨርሰናል" ማለታቸው ይታወሳል። 

ለሁለት ዓመታት በፌደራል መንግስት እና የትግራይ ሀይሎች መካከል የተደረገው ጦርነት ተከትሎ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚገመቱ ተፈናቃዮች አሁንም ኑሮአቸው በግዚያዊ መጠልያ ጣብያዎች ሆኖ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ። ምስል Million Haileselassie/DW

ይህ ተፈናቃዮች ለመመለስ የተደረገ መግባባት፥ ላለፉት አራት ዓመታት ከባድ ሕይወት እየመሩ ላሉ ተፈናቃዮች ተስፋ የፈጠረ ሆንዋል። ከምዕራብ ትግራይ ዞን በ2013 ዓመተምህረት ተፈናቅለው ዓብይ ዓዲ በሚገኝ መጠልያ እየኖሩ ያሉ የቤተሰብ መሪ ተፈናቃይ አቶ ብርሃነ ታፈረ፥ ለመመለስ የተቆረጠው ቀን በእርሳቸው እና በበርካቶች ዘንድ ተስፋን የፈጠረ ሆንዋል ይላሉ።

 የትግራይ ጡረተኞች አቤቱታቸው መልስ ማግኘት ጀመረ

ሌላው ያነጋገርናቸው ከምዕራብ ትግራይ ዞን ፀገዴ ወረዳ የተፈናቀሉ አቶ ድምፁ ተስፋይ ተፈናቃዮች የመመለሱ እቅድ ሊፈፀም በተስፋ እየጠበቁ መሆኑ ያነሳሉ። 
አቶ ድምፁ "ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ እንዲሁ ትመለሳላችሁ እየተባለ ቃል ይገባ ስለነበረ እና የተባለው ሳይፈፀም በመቅረቱ ካለው ስጋት ውጭ፥ ሁሉም ተፈናቃይ በተባለው መሰረት ዘንድሮ ወደቤቱ ሊመለስ ነው እየጠበቀ ያለው። እቅዱ እንዳይደናቀፍ ነው የምንሰጋው። በርግጥ ካለፈው ለየት የሚያደርገው የመመለስ ተስፋ አሁን አለ" ብለዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ቆይተዋል። ምስል Million Haileselassie/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተፈናቃዮች ሲመለሱ የፀጥታ እና ድህንነት ሁኔታ የተጠበቀ እንዲሆን ሊሰራ የሚጠይቁት ተፈናቃዮች፥ ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆኑ ሕገወጥ ታጣቂዎች መንግስት ትጥቃቸውን ሊያስፈታቸው፣ በሀይል ከያዙት ግዛት እንዲያስወጣቸው እንደሚጠብቁ ያነሳሉ።

"ህዝቡ ተፈናቅልዋል። ንብረቱ የለም። ማቋቋሚያ ያስፈልገዋል። ከዚህ ውጭ ጦርነት የነበረበት አካባቢ እንደመሆኑ የጦርነቱ ቅሪት የሆኑ አደጋ የሚፈጥሩ ተተኳሾች እንዳይኖሩ በደንብ በጥንቃቄ መታየት አለበት ነው የምለው። ይህ ሁሉ ሳይረጋገጥ የምንገባበት ዕድል የለም" ብለዋል ተፈናቃዮ አቶ ድምፁ ተስፋይ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW