1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«በትግራይ ባለሥልጣናት የግዴታ ዉትድርና እየተፈፀመ ነዉ» ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 2 2018

የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት የ15 ዓመት አዳጊዎችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎችን እያፈኑ በግዳጅ ለውትድርና እያስገደዱ እንደሚገኙ ዓለምአቀፉ ሰብአዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት ሒውማን ራይት ዎች ወነጀለ። ድርጅቱ የአፍሪቃ ህብረት፣ የተመድ እና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ አጋሮች በትግራይ ያሉ ባለስልጣናት ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ፎቶ ከማህደር፤ የትግራይ ክልል የጦር ሰራዊት
ፎቶ ከማህደር፤ የትግራይ ክልል የጦር ሰራዊት ምስል፦ YASUYOSHI CHIBA/AFP

«በትግራይ ባለሥልጣናት የግዴታ ዉትድርና እየተፈፀመ ነዉ» ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

This browser does not support the audio element.

የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት የ15 ዓመት አዳጊዎችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎችን እያፈኑ በግዳጅ ለውትድርና በመመልመል ላይ እንደሚገኙ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት ሒውማን ራይት ዎች በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ ወንጅሏል።  የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደር፤ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ የአፍሪቃ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ አጋሮች በትግራይ ያሉ ባለስልጣናት የግዳጅ ቅጥርን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ህገወጥ በሆነ መንገድ የተቀጠሩ ህጻናትን እና ሌሎች ሲቪሎችን እንዲለቁ በይፋ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።  

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት የትግራይ ባለሥልጣናት በክልሉ እየፈፀሙት ያሉት የግዳጅ ዉትድርና ዓለምአቀፉ ማህብረሰብ ጫና ሊያደርግና ሊያስቆም ይገባል ሲል መግለጫ ያወጣዉ በሳምንቱ መጀመርያ ሰኞ እለት ነበር። እንደ ሒዉማን ራይትስ ዎች፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የትግራይ ጸጥታ ኃይል እና ባለሥልጣናት፤ የ15 ዓመት አዳጊዎችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎችን እያፈኑ በግዳጅ ለውትድርና በማስገደድ  ላይ ናቸዉ ሲል ወንጅሏል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ፤ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት የሒዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደር  እንዳሉት በትግራይ ክልል የሚገኙት ባለሥልጣናት፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን፣ ጎልማሶችና አዳጊ ልጆችን ከቢሮዎች እና ከወርቅ ማውጫ ቦታዎች በምሽት በሚካሔድ የቤት ለቤት አሰሳ ጭምር እንደሚያፍኑ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መግለፃቸዉን  ተናግረዋል። 

«የአካባቢው ባለስልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች ብዙውን ጊዜ ለሊት ለሊት ከቤት -ቤት አሰሳ ያካሂዳሉ፣ በትላልቅ ከተሞች ግን ወጣት እና ህጻናቱን የሚያፍሷቸዉ ከመንገድ ላይ እንዲሁም ወጣቶች ሊኖሩባቸው ከሚችሉባቸው የመዝናኛ ቦታዎች ወይም እንደ ክበቦች እና መጫወቻ ካሉ ቦታዎች እንደሆነ ያነጋገርናቸዉ የማኅበረሰቡ አባላት ነግረዉናል።»

ከሚያዝያ ወር በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባለሥልጣናት በሕዝባዊ ውይይቶች፣ ደብዳቤ በመጻፍና ስልክ በመደወል የቀድሞ የትግራይ የጸጥታ ኃይል አባላት ወደ ወደ ምድባቸው እንዲመለሱ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸዉን፤ በሚያዝያ ወር ግን በጎዳናዎች፣ በገበያዎች፣ የወርቅ ማውጫ ቦታዎች አፈሳው መጠናከሩን ላትሪሽያ ባደር ፤ ከአካባቢዉ ለድርጅቱ የደረሰዉን መረጃ ጠቅሰዉ ተናግረዋል። 

የትግራይ ባለስልጣናት ወንድ ጎልማሳ እና ታዳጊ ልጆችን በኃይል ወደ ጦራቸው ለመመልመል የሚያደርጉት ዘመቻ በክልሉ ውስጥ የፍርሃት ድባብ እየፈጠረ መሆኑን የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደር አክለዉ ተናግረዋል። ባለስልጣናቱ ለዉትድርና አፈሳን የጀመሩት ባለፈዉ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ከመንገዶች፣ ከገበያዎች እና ከወርቅ ማዕድን ማውጫ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ አፈሳ መፈፀሙ መጠናከሩን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዉ ድርጅት ያወጣዉ መግለጫ ያመለክታል። ድርጅቱ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸዉ የዓይን እማኞች የአካባቢው ባለስልጣናት የአካባቢ መረጃ ሰጭዎችን ተጠቅመዉ ምልምል ሊሆኑ የሚችሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን የስም ዝርዝር መዝግበዉ መያዛቸን ተናግረዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የህወሓት ወታደሮች - 2021ምስል፦ Ben Curtis/AP/picture alliance

«በቃለ ምልልሶቻችን ላይ በእርግጥ የሰማነው ይህ ዘመቻ በትግራይ ውስጥ ሰፊ ፍርሃት እደፈጠረ እና ቤተሰቦችን እንደገና እየለያየ መሆኑን ነው። ቤተሰቦች የሚወዱት ሰው ለዉትድርና ይመለመላል የሚል ስጋት፣ ምልመላዉን መቃወም እንኳ ከፍተኛ ፍርሃት እንዳለ ገልፀዋል። ስለዚህ አንዳንድ ቤተሰቦች የዉትድርና ምልመላ አደጋ ላይ ያሉ ወዳጅ ቤተሰቦቻቸዉ ተደብቀው እንዲቆዩ ኣልያም ወደ አዲስ አበባ ጨምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲሸሹ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ዉትድርና ምልመላን በመፍራት ወደ መኖርያ ቤታቸዉ ያልተመለሱ የተደበቁ ሰዎችንም አነጋግረናል»

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ድርጅት ስድስት የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ጉዳዮችን ለመሰነድ ተቋሙ 18 እማኞች እንዳነጋገረ ባወጣዉ ዘለግ ያለ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።  በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን አንድ ወጣት በግዳጅ ለውትድርና ሊመለምሉት ወደ ቤቱ የመጡት ሦስት የትግራይ ጸጥታ ኃይል አባላት መሆናቸዉን ለሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ተናግሯል። ሌሎች 17 ሰዎችም ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን እና ከተወሰዱት መካከል አምስት የሚሆኑት ዕድሜያቸው 16 ወይም 17 እንደሚሆን አስረድቷል። ምስክርነታቸዉን ለድርጅቱ የሰጡ አንድበትግራይ ክልል የአዲ ጉደም ነዋሪ በበኩላቸው በሰኔ ወር ፖሊሶችና፣ ሚሊሺያዎችና የትግራይ የጸጥታ ኃይል አባላት ወታደሮች የቀን ሠራተኞችና ገበሬዎችን አፍሰው እንደወሰዱ ተናግረዋል። በ1949 የጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀጽ 3 መሠረት መንግሥታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ቡድኖች ሰብአዊነት የጎደላቸው ድርጊቶች እንዲፈጽሙ ሙሉ በሙሉ የተከለከሉበት ሕጋዊ ማዕቀፍ  መሆኑን፤ የሂዩማን ራይትስ ዎች ይፋ ባደረገዉ መግለጫ  ጠቁሟል። 

«በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት፣ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በታጠቁ ቡድኖች መመልመልና መጠቀም የተከለከለ ነው፤ ከዚህም በላይ፣ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን መመልመል የጦር ወንጀል ክስን ይመሰርታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ፣ በተለይም ቁልፍ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማጽደቋ ምክንያት፣ ህጻናት እንዳይመለመሉ የመከላከልና ጥበቃቸውን የማረጋገጥ ግልጽ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ግዴታዎች አለባት።»

ላቲሽያ ባደር፤ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት የሒዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ምክትል ዳይሬክተር ምስል፦ Human Rights Watch

በትግራይ በግዳጅ የሚካሔደው ወታደራዊ ምልመላ “በመላ ክልሉ ፍርሐት” እንደፈጠረ የገለፁት የሒውማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ክፍል ምክትል ኃላፊ ላቴሺያ ባድር የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ቱ ምልመላውን በፍጥነት እንዲያቆሙ እና በግዳጅ የተመለመሉ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪቃ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

«የአፍሪቃ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እና የኢትዮጵያ አለም አቀፍ እና ክልላዊ አጋሮች በትግራይ ያሉ ባለስልጣናት የግዳጅ ቅጥርን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ህገወጥ በሆነ መንገድ የተቀጠሩ ህጻናትን እና ሌሎች ሲቪሎችን እንዲለቁ በይፋ ጫና ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም አለም አቀፍ ተዋናዮች ሁኔታውን ገለልተኛ ክትትል ማድረግ አለባቸው። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮበትግራይ ክልል እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ስለተፈጸሙት እነዚህ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በይፋ ሪፖርት እንዲያደርግ ለረጅም ጊዜ አጥብቀን አሳስበናል።» በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት የተሰየመዉን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ባለፈዉ ሚያዝያ ወር  ተቆጣጥሮ ክልሉን እያስተዳደረ ያለዉ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የህወሓት ባለሥልጣናት በበኩላቸዉ  በክልሉ በግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሔደ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW