በትግራይ ተባብሷል የተባለው የፖለቲካ ቀውስና የማዕድን ምዝበራ
ሰኞ፣ ኅዳር 16 2017ከአራት ወራት ባነሰ ግዜ ውስጥ 28 ኩንታል ወርቅ ከትግራይ ለፌደራል መንግስቱ ገቢ መደረጉን የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። ከዚህ ለጎን በክልሉ ሕገወጥ የማዕድናት ምዝበራ እና ኮንትሮባንድ መበራከቱም ተገልጿል። በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ማብራሪያ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በወርቅ ማዕድን ምዝበራ ውስጥ በርካቶች እጃቸውን ማስገባታቸውን ጠቁመዋል።
በወቅታዊ የትግራይ ጉዳዮች ዙርያ ትላንት ለሚቆጣጠሩዋቸው ሚድያዎች ብቻ በትግርኛ ማብራሪያ የሰጡት የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ እየተባባሰ ወደ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል። የተደራጀ ወንጀሎች፣ ፖለቲካዊ አሻጥሮች እና መንግስት ስራውን እንዳይከናውን የማደናቀፍ ተግባራት መባባሳቸውን የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በተለይም በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን እና ማእከላዊ ዞን የተወሰኑ አካባቢዎች ሕገወጥ የማዕድን ምዝበራ በተፈጥሮ ሀብት ላይ አደጋ የፈጠረ መሆኑ ገልፀዋል። እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ፥ አራት ወራት በማይሞላ ግዜ ውስጥ 28 ኩንታል ወርቅ ለፌደራል መንግስት ገቢ መደረጉን ያነሱ ሲሆን፥ ይህም በከፍተኛ መጠን ይከናወናል ተብሎ ለሚታሰበው ሕገወጥ የወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት ምዝበራ ስፋት ማሳያ ሆኗል።በትግራይ ክልል እየተስፋፋ የመጣ ሕገወጥ የማዕድን እና መሬት ወረራ
አቶ ጌታቸው "በሰሜን ምዕራብ ሁሉም መሬት እየተቆፈረ፣ ሁሉም ተራራ እያፈረሰ በወርቅ ማውጣት የተሰማራ ሲቪል እና ሰራዊት መአት ነው። ዛሬ ባለኝ መረጃ ባለፉት ሶስት ወራት እና ሁለት ሳምንት 28 ኩንታል ወርቅ ወደ ፌደራል መንግስት ገብቷል። ይህ በኮንትሮባንድ የወጣውን አያካትትም። የክልሉ መንግስት ከዚህ ያገኘው አንድም ሳንቲም የለም" ብለዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ያነሱት ሌላ ጉዳይ በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ልዩነት ሲሆን፥ የፌደራል መንግስት የህወሓት አመራሮች ችግራቸውን እንዲፈቱ ግፊት እያደረገ መሆኑ ጠቅሰዋል።
"የፌደራል መንግስቱም ቢሆን በህወሓት መካከል ያለውን ችግር ፈትታችሁ፣ አንድ ሆናችሁ መጥታችሁ የሚያዋጣ ሀሳብ አቅርቡ ነው እያለ ያለው። ካልቻላችሁ ደግሞ ወይ ብልፅግና ይወስደዋል፥ ምክንያቱም የፕሪቶርያ ውልም ቢሆን ህወሓት ብቻ ሳይሆን ሁለቱም መንግስት ይመሰርታሉ ስለሚል፥ ህወሓት ስላልቻለ ብልፅግና ስልጣኑ ይይዘዋል ተብሎ ተነግሮአቸዋል" ሲሉ ጌታቸው ጨምረው ተናግረዋል።በትግራይ ክልል እየተስፋፋ የመጣ ሕገወጥ የማዕድን እና መሬት ወረራ
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በአጠቃላይ በትግራይ 274 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች መኖራቸው የገለፁ ሲሆን በቅርቡ የተጀመረው የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ማስገባት እና ወደ ሰላማዊ ህይወት የመመለስ ስራ በአዎንታዊነት የሚታይ ብለውታል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ