በትግራይ ክልል ኃይሎችና በቀድሞ አባላቱ መካከል የተካሄደ ግጭት
ሰኞ፣ ነሐሴ 5 2017
የትግራይ ክልል ኃይሎች ከፍተኛ አዛዦች ለአንድ የህወሓት ቡድን ያጋደለ ውሳኔ አስተላለፉ በማለት የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት በመያዝ እንዲሁም ከዋናው ኃይል በመለየት በአፋር ክልል ሲደራጁ የቆዩ ታጣቂዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ ወደ ትግራይ ዘልቀው በመግባት ጥቃቶች እየሰነዘሩ ነው በማለት የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ከሷል።
ቢሮው ባወጣው መግለጫ ማዕከላቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ፣ ቤተሰቦቻቸውን ውጭ ሀገር አስቀምጠው የትግራይን ወጣት ለአመፅ እየጠሩ ነው ሲል ወቅሷል። በተጋሩ መካከል የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት ጥረት እያደረገ እንዳለ የሚገልፀው የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፥ ይሁንና እነዚህ በስም ያልጠራቸው ይሁንና 'ወዶገብ፣ ነጭ ለባሽ' በሚሉ እና ሌሎች አገላለፃች ያስቀመጣቸው አካላት ተጋሩን እርስበርስ ለማዋጋት ፕሮጀክት በመያዝ አፋር ያሉ ታጣቂዎችን ተጠቅመውበትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ብሏል። ይህ ጥቃት ለሁለተኛ ግዜ የተሰነዘረ ነው ያለው ይህ መግለጫ፥ በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ የአንድ አባላቸው ህይወት ማለፉን አመልክቷል። ይህን ባደረጉት ላይም አስተማሪ እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል።
በእነዚህ ኃይሎች መካከል እየታዩ ያሉ ግጭቶች እንዲሁም ወቅታዊ የህወሓት እና የፌደራል መንግስት አለመግባባቶች በትግራይ፣ ህዝቡ ዘንድ ስጋት ፈጥሮ ይገኛል። ትናንት በነበረ መድረክ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ፥ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ሰላም ነው ሲሉ ተናግረው። ከኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘቶችን በሙሉእነት መፈፀም እንደሚጠበቅ የተናገሩት አቶ አማኑኤል ከዚህ በተፃራሪ፥ ይህ ሲባል ትግራይን በጦርነት ዝግጅት መወንጀል አይገባም ሲሉ አክለዋል።
አቶ አማኑኤል "የትግራይ ጥያቄዎች መሰረታዊ ነገሮች ናቸው። የትግራይ ህዝብ ሉአላዊነቱ ተወሮ፣ ከቆዬ ተፈናቅሎ፣ ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ ወድሞ፣ ሰላም አጥቶ፣ የነበረው አጥቶ እና ተክዶ ነው ያለው። አሁንም እየጠየቀ ያለው ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ነው" ብለዋል።
በፌደራሉ መንግስት እና ህወሓት መካከል ያለው መካረር ለመፍታት የሃይማኖት መሪዎች እና ሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ላይ መሆናቸው በቅርቡ ሲገልፁ ነበር።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ