1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች «ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ» የተባለ ጥምረት መሰረቱ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2016

የትግራይ ነጻነት ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) ኪዳን ለሥር ነቀል ለውጥ የተባለ ጥምረት መሰረቱ። የአራቱ ፓርቲ ሹማምንት የትግራይ ክልልን የሚመሩ ባለሥልጣናትን በብረታ ብረት እና የእርዳታ እህል ዝርፊያ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሰማርተዋል ሲሉ ይወነጅላሉ።

የትግራይ ነጻነት ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) አመራሮች
ኪዳን ለሥር ነቀል ለውጥን የመሠረቱት የትግራይ ነጻነት ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) ትግራይን በሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት ላይ ብርቱ ውንጀላ ያቀርባሉምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች "ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ" የተባለ ጥምረት መሰረቱ

This browser does not support the audio element.

"ኪዳን፥ ለስር ነቀል ለውጥ" በሚል የተደራጁ በትግራይ የሚገኙ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግራይ አስተዳደር አካላት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባራት ተጠምደው ይገኛሉ ሲሉ ገለፁ። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ ባይቶና በጋራ በሰጡት መግለጫ ገዢው ህወሓት ለረሃቡ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በስልጣን ሽኩቻ ተጠምደው ከ35 በላይ ቀናት ስብሰባ ላይ ይገኛሉ ብለዋል። 

በኪዳን ስም በጋራ መንቀሳቀስ የጀመሩት የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ ባይቶና በጋራ በሰጡት መግለጫ ትግራይ በከፋ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀውስ ላይ እንደምትገኝ የገለፁ ሲሆን ክልሉ እየመራ ያለው ሐይል ደግሞ ችግሮች ለመፍታት ከመጣር ይልቅ በቡድናዊ የስልጣን ሽኩቻ እና የተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተሰማርቶ እንዳለ አንስተዋል።

አረና ትግራይ ለረሐብ አደጋው ሕወሓት ትኩረት አልሰጠም ሲል ወቀሰ

የትግራይ ነፃነት ፖርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ፥ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ቅሪት ብረታብረቶች ሕገወጥ ዝርፍያና ሽያጭ እንዲሁም የእርዳታ ስንዴ ስርቆት ላይ ቆዩ ያልዋቸው የትግራይ ባለስልጣናት፥ አሁን ደግሞ የትግራይ ተወላጆች እና ኤርትራውያን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ ሲሉ ከሰዋል።

በትግራይ ክልል በምትገኘው አጽቢ ወረዳ ብቻ ከመቶ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Million Haileselassie Brhane/DW

ዶክተር ደጀን መዝገበ "ከብረታብረት እና የእርዳታ ስንዴ መዝረፍ እና መሸጥ አልፎ፥ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ስራ ተጠምደው ያሉት የመንግስት አካላት ናቸው። ይህ ወንጀል ጣራ ላይ ደርሶ፣ ባለስልጣናት የሚበለፅጉበት፣ህዝባችን ይሁን ከኤርትራ የሚመጣ ሰው እየተሸጠ የሚውልበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ ወንጀል ግለሰቦች የሚፈፅሙት አይደለም። እንደ ተቋም እንደ ስርዓት ነው እየተፈፀመ ያለው" ብለዋል።

በትግራይ ክልል አጽቢ ወረዳ በሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሐብ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገጹ

"ኪዳን፥ ለስር ነቀል ለውጥ" በሚል ከተደራጁ በትግራይ ያሉ አራት ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሆነው ዓረና ትግራይ በበኩሉ፥ በትግራይ ከመቼውም ግዜ በላይ የከፋ ያለው ድርቅና ረሃብ መከሰቱ ባደረገው ቅኝት ማረጋገጡ አስታውቋል። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ በትግራይ ያለው ረሃብ ከፍቶ በሚገኝበት የህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ይህ ችላ በማለት ከወር በላይ ሰብሰባ ተቀምጠዋል ይላሉ።

በትግራይ "ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ" የተባለ ጥምረት የመሠረቱት አራቱ ፓርቲዎች ብርቱ ወቀሳ የሚሰነዝሩባቸው የክልሉ ባለሥልጣናት ከአንድ ወር በላይ ስብሰባ ተቀምጠዋል። ምስል Million Hailesilassie/DW

አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ"ወታደራዊ አመራሩ፣ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ፣ ነባር የህወሓት መሪነት ድርቁ፣ ረሃቡ እና ሞቱ ችላ ብለው ከ35 በላይ ቀናት፥ በግል፣ በስልጣንና ጥቅማቸው ጉዳይ ቤት ዘግተው እየተነታረኩ ነው። የዘንድሮው ድርቅና ረሃብ መጥፎ እና አደገኛ የሚያደርገው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ችላ ብለውት ያለ በመሆኑ ነው" ይላሉ።

የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ያቀረቡት ጥሪ

በኪዳኑ የታቀፉ የአራቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ ያሉ ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ አቅርበዋል። የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አሉላ ሀይሉ "ትግራይ ውስጥ ያሉ ችግሮች የሚፈታው፣ ብሔራዊ አንድነት ሊያመጣ የሚችለው ይህ ስርዓት አይደለም። ከዚህ ስርዓት ውጭ፥ ሁሉም የትግራይ የፖለቲካ ሐይሎች የሚያቅፍ የጋራ ወይም የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት ብለን በተደጋጋሚ እየጠየቅን ነው፤ አሁንም መፍትሄው እሱ መሆኑ በግልፅ እየታየ መጥቷል" ብለዋል።

በጋራ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የተሰባሰቡት እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይም ሕጋዊና ሰላማዊ ትግላቸው እንደሚቀጥሉ፥ በአገዛዙ ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል። የባይቶና ሊቀመንበር አቶ ክብሮም በርሃ"በአጭር ግዜ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ፥ መጀመርያ ላይ ከህዝባችን ጋር እንመካከራለን፣ ባለው ችግር ዙርያ ከህዝባችን ጋር መግባባት እንፈጥራለን፣ ቀጥሎ የተለያዩ የትግል መንገዶች ተጠቅመን ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ እንደምንወስድ በዚህ አጋጣሚ ማሳወቅ እንፈልጋለን" ሲሉ አክለዋል።
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባቀረብዋቸው ክሶች ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተገልፆ አልተሳካም።


ሚሊዮን ኃይለስላሴ
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW